በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወላጆቼን ነቀፋ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የወላጆቼን ነቀፋ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 21

የወላጆቼን ነቀፋ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“እናቴ ፖሊስ ይመስል ሁልጊዜ በእኔ ላይ ስህተት ትፈላልጋለች። የቤት ውስጥ ሥራዬን እስክጨርስ ፋታ አትሰጠኝም፤ ገና ሳልጨርስ ምን እንደተሳሳትኩ ለማየት ምርመራ ትጀምራለች።”​—ካሌብ

“ወላጆቼ አንድ ነገር ካዩ አይለቁኝም። ምንም ነገር በትክክል መሥራት እንደምችል ሆኖ አይሰማቸውም። በትምህርት ቤትም ይሁን በቤት ወይም በጉባኤ ውስጥ ምንም ላድርግ ምን እኔን የሚቆጡበት ነገር አያጡም።”​—ጄምስ

ምንም ነገር ብታደርግ ወላጆችህ እንደማይጥማቸው ይሰማሃል? ወላጆችህ እያንዳንዱን እንቅስቃሴህን በማጉያ መነፅር እንደሚከታተሉና መቼም ቢሆን ከእነሱ እይታ ውጪ መሆን እንደማትችል ሆኖ ይሰማሃል? በሌላ አባባል ሁልጊዜ እንደሚገመግሙህ ሆኖም አንድም ቀን ፈተናውን ማለፍ እንደማትችል አድርገህ ታስባለህ?

ከታች ከቀረቡት መካከል አብዛኛውን ጊዜ ወላጆችህ ሲናገሩ የምትሰማው የትኛውን ነው?

□ ክፍልህ ሁልጊዜ እንደተዝረከረከ ነው!

□ መቼም ቴሌቪዥን ላይ ከተተከልክ አትነሳም!

□ ኧረ ባክህ በጊዜ ተኛ!

□ መቼስ ከአልጋ መነሳት ሞትህ ነው!

ወላጆችህ ከሚናገሩህ ነገሮች መካከል ይበልጥ የሚያበሳጭህን ከታች ባለው መስመር ላይ ጻፍ።

․․․․․

ወላጆችህ የሚያወጡት መመሪያና የሚሰነዝሩት ነቀፋ ሊያበሳጭህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም ነገሩን ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው፦ ወላጆችህ ምንም ዓይነት ምክር ወይም ተግሣጽ የማይሰጡህ ቢሆን አንተን መውደዳቸው አያጠራጥርህም? (ዕብራውያን 12:8) በእርግጥም ተግሣጽ ወላጆችህ እንደሚወዱህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አባት “ደስ የሚሰኝበትን ልጁን” እንደሚገሥጽ ይናገራል።​—ምሳሌ 3:12

እንግዲያው ወላጆችህ ተግሣጽ እንዲሰጡህ የሚያነሳሳቸው ለአንተ ያላቸው ፍቅር በመሆኑ ለሚሰጡህ እርማት አመስጋኝ ልትሆን ይገባል! ደግሞም ገና በዕድሜ ስላልበሰልክ የወላጆችህን ያህል ብዙ ተሞክሮ የለህም። በመሆኑም እርማት ማግኘትህ የማይቀር ነገር ነው። መመሪያ ካላገኘህ “ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው [በሚመጡ] ምኞቶች” በቀላሉ ልትሸነፍ ትችላለህ።​—2 ጢሞቴዎስ 2:22

ግን እኮ ደስ አይልም!

እርግጥ ነው፣ “ማንኛውም ተግሣጽ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት አይመስልም።” (ዕብራውያን 12:11) በተለይ ደግሞ ወጣት ከሆንክ ተግሣጽ ሲሰጥህ ይበልጥ ይከፋህ ይሆናል። ይህ የሚያስገርም አይደለም! ወጣትነት ማንነትህ የሚቀረጽበት ወቅት ነው። ያለህበት ዕድሜ እድገት የምታደርግበትና ማንነትህን የምታውቅበት ጊዜ ነው። በመሆኑም በሚገባ የታሰበበትና በደግነት የተሰጠ እርማት እንኳ ሊያስከፋህ ይችላል።

ተግሣጽ ሲሰጥህ መከፋትህ የሚጠበቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ሌሎች ስለ አንተ የሚናገሩት ነገር ለራስህ ባለህ ግምት ላይ በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በተለይ ደግሞ ወላጆችህ የሚሰጡህ አስተያየት ለራስህ ባለህ አመለካከት ረገድ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በዚህም ምክንያት ወላጆችህ እርማት ሲሰጡህ ወይም አንድን ነገር ያከናወንክበት መንገድ እንዳልጣማቸው ሲገልጹ በጣም ትበሳጭ ይሆናል።

ታዲያ ወላጆችህ አንዳንድ ጥፋቶችህን ስለነገሩህ ብቻ ምንም ነገር ብታደርግ እነሱን ማስደሰት እንደማትችል ወይም አንድም ነገር በትክክል መሥራት እንደማትችል ሊሰማህ ይገባል? በፍጹም። ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም እንደሚባለው ሁሉም ሰው ጉድለት እንዳለው አትዘንጋ። (መክብብ 7:20) ደግሞም ከስህተት መማር የእድገት አንዱ ክፍል ነው። (ኢዮብ 6:24) ይሁንና ወላጆችህ አንድ ጥፋት ስትሠራ ብዙ የሚናገሩህ፣ ጥሩ ነገር ስትሠራ ግን ያን ያህል የማያመሰግኑህ ቢሆንስ? ይህ ስሜትህን ሊጎዳው ይችላል። ያም ቢሆን ግን ምንም ነገር በትክክል መሥራት አትችልም ማለት አይደለም።

መንስኤውን ለማወቅ ጣር

አንዳንድ ጊዜ ወላጆችህ ከሚገባው በላይ ነቃፊ የሚሆኑት አንተ የሠራኸው የተለየ ስህተት ኖሮ ሳይሆን እነሱ ራሳቸው በሆነ ምክንያት ጥሩ ስሜት ስላልተሰማቸው ሊሆን ይችላል። እናትህ ውሎዋ ጥሩ አልነበረም? አሊያም አሟት ይሆን? በዚህ ወቅት ክፍልህ በደንብ ካልጸዳና ሥርዓት ካልያዘ ከወትሮው በተለየ ቁጣ ቁጣ ሊላት ይችላል። አባትህ ቤተሰቡ የገጠመው የገንዘብ ችግር አበሳጭቶት ይሆን? በዚህ ጊዜ ‘በሰይፍ የመውጋት’ ያህል እንዳመጣለት ሊናገር ይችላል። (ምሳሌ 12:18) ባላጠፋኸው ነገር መወቀስህ ሊያበሳጭህ እንደሚችል ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ይህን እያሰብክ መብሰልሰልህ ይበልጥ እንድትበሳጭ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር ስለሌለ የወላጆችህን ጥፋት ለማለፍ ሞክር። “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው . . . ፍጹም ሰው ነው” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ።​—ያዕቆብ 3:2

ወላጆችም ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በመሆናቸው ነገሮችን በትክክል ማከናወን እንደማይችሉ ሊሰማቸው ይችላል። እንዲያውም የአንተ መሳሳት የእነሱ ጥፋት እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ለምሳሌ፣ አንዲት ልጅ በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ባለማምጣቷ እናቷ ትቆጣት ይሆናል። ሆኖም እናትየዋ እንዲህ እንድትናገር ያደረጋት የልጇ ውጤት ሳይሆን ‘ልጄ ጥሩ ውጤት እንድታመጣ ለመርዳት ማድረግ ያለብኝን ያህል አላደረግሁም’ የሚለው ስሜት ሊሆን ይችላል።

ከመበሳጨት ይልቅ ቀዝቀዝ በል

ወላጆችህ የተቆጡበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ‘ሁኔታውን መወጣት የምትችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቁጣ ገንፍለህ ምላሽ ከመስጠት ተቆጠብ። ምሳሌ 17:27 “ዐዋቂ ሰው ንግግሩ ቍጥብ ነው፤ አስተዋይም መንፈሱ የረጋ ነው” ይላል። ታዲያ ወላጆችህ በሚቆጡህ ወይም በሚነቅፉህ ጊዜ ‘የረጋ መንፈስ’ መያዝ የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር፦

በጥሞና አዳምጥ። ለድርጊትህ ምክንያት ለመደርደር ወይም እንዳልተሳሳትክ ለማሳመን ከመጣደፍ ይልቅ ስሜትህን ተቆጣጥረህ ወላጆችህ የሚሉህን አዳምጥ። አንድ ክርስቲያን “ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ” መሆን እንዳለበት ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ተናግሯል። (ያዕቆብ 1:19) ወላጆችህ ሲያናግሩህ አቋርጠሃቸው በቁጣ የምትመልስላቸው ከሆነ እያዳመጥካቸው እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ይህ ስለሚያበሳጫቸው ተጨማሪ ተግሣጽ እንዲሰጡህ ያደርጋቸዋል።

በነጥቡ ላይ አትኩር። አንዳንድ ጊዜ ወላጆችህ ምክሩን የሰጡህ ደግነት በጎደለው መንገድ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም በተናገሩበት መንገድ ላይ ሳይሆን ሊያስተላልፉት በፈለጉት ነጥብ ላይ ትኩረት አድርግ። እንዲህ በማለት ራስህን ጠይቅ፦ ‘ከተናገሩት ውስጥ ትክክል የሆነው ነጥብ የትኛው ነው? ወላጆቼ ከአሁን በፊት ስለዚህ ጉዳይ ምክር ሰጥተውኛል? ያሉኝን ባደርግ ምን ይጎዳኛል?’ በወቅቱ ባይመስልህም እንኳ ወላጆችህ ተግሣጽ የሚሰጡህ ስለሚወዱህ እንደሆነ አትዘንጋ። የሚጠሉህ ቢሆን ኖሮ እስከናካቴው እርማት አይሰጡህም ነበር።​—ምሳሌ 13:24

ጥፋትህን እመን። ጥፋትህን የምታምን ከሆነ ወላጆችህ የተናገሩት ነገር እንደገባህ ታሳያለህ። ለምሳሌ ወላጆችህ፣ “ክፍልህ ሁልጊዜ እንደተተራመሰ ነው፤ የማታስተካክለው ከሆነ ዋጋህን ታገኛለህ!” ይሉህ ይሆናል። ምናልባት አንተ ክፍልህን በሥርዓት እንደያዝክ ልታስብ ትችላለህ። ይሁን እንጂ ይህን ሐሳብህን ለወላጆችህ መናገርህ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። ጉዳዩን በእነሱ ቦታ ሆነህ ለማየት ሞክር። “እውነታችሁን ነው፣ እሺ አሁኑኑ አስተካክለዋለሁ” ብትላቸው የተሻለ ይሆናል። ወላጆችህ ያሳሰባቸውን ነገር እንደተረዳህላቸው ሲገነዘቡ ቁጣቸው ሊበርድ ይችላል። በእርግጥ በቃልህ መሠረት ወላጆችህ ያሉህን ማድረግ ይኖርብሃል።​—ኤፌሶን 6:1

ለመናገር አትቸኩል። መጀመሪያ ወላጆችህ የሚጠብቁብህን ነገር ፈጽም፤ ላደረግኸው ነገር ምክንያት መስጠቱን በኋላ ትደርስበታለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበቱን የሚገታ . . . ጠቢብ ነው” ይላል። (ምሳሌ 10:19) ወላጆችህ የተናገሩትን ነገር አዳምጠሃቸው እንደነበር ሲገነዘቡ የምትለውን ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኛ ይሆናሉ።

ከላይ ከተዘረዘሩት አራት ነጥቦች መካከል ይበልጥ ልትሠራበት እንደሚገባ የሚሰማህን በክፍት ቦታው ላይ ጻፍ። ․․․․․

ጥረት ማድረጉ የሚክስ ነው

ወርቅ ለማግኘት ስትል አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ፈቃደኛ ትሆናለህ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጥበብ ከማንኛውም ውድ ሀብት የበለጠ ዋጋ እንዳለው ይናገራል። (ምሳሌ 3:13, 14) ታዲያ ጥበበኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌ 19:20 “ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤ በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ” ይላል። ምክርና ተግሣጽ ሲሰጥህ በተወሰነ መጠን ሊከፋህ እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁንና የሚሰጥህ እርማት ምንም ይሁን ምን በውስጡ የሚገኘውን እንደ ውድ ማዕድን የሚቆጠር ጥበብ ለይተህ በማውጣት በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ የምታደርገው ከሆነ ከወርቅ የበለጠ ዋጋ ያለው ሀብት ይኖርሃል።

ልንክደው የማንችለው አንድ እውነታ አለ፦ ማንም ሰው ቢሆን ከእርምት ወይም ከነቀፋ ማምለጥ አይችልም። አሁን የወላጆችህንና የአስተማሪዎችህን እርማት ማስተናገድ ይኖርብሃል። ወደፊት ደግሞ ከአሠሪዎችህና ከሌሎች ሰዎች የሚሰነዘርብህን ነቀፋና ትችት መቀበል እንደሚኖርብህ ግልጽ ነው። ወላጆችህ እርማት ሲሰጡህ እንዴት መቀበል እንዳለብህ ካወቅህ ጥሩ ተማሪ እንዲሁም በአሠሪዎችህ ዘንድ የምትወደድ ሠራተኛ ትሆናለህ፤ በአጠቃላይ ይበልጥ በራስህ የምትተማመን ሰው ትሆናለህ። በእርግጥም እንደዚህ ዓይነት ውጤት ለማግኘት ስትል የሚሰነዘርብህን ነቀፋም ሆነ የሚሰጥህን እርማት ለመቀበል ጥረት ማድረግህ የሚክስ ነው!

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወላጆችህ ያወጧቸው መመሪያዎች መፈናፈኛ እንዳሳጡህ ይሰማሃል? አሁን ያለህን ነፃነት ማድነቅም ሆነ ተጨማሪ ነፃነት ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ከሚቀጥለው ምዕራፍ ትምህርት ታገኛለህ።

ቁልፍ ጥቅስ

“ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ።”​—ምሳሌ 1:5

ጠቃሚ ምክር

ወላጆችህ የሚሰጡህን እርማት ለመቀበል እንዲቀልህ የሚረዳህ ሐሳብ

በሚሰነዝሩት ነቀፋ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ በምንም መልኩ አድናቆታቸውን ከገለጹ ለዚህ አመስጋኝ ሁን።

ጥፋትህ ምን እንደሆነ ወይም ምን ማድረግ እንዳለብህ ግልጽ ካልሆነልህ በደንብ እንዲያብራሩልህ ጠይቃቸው።

ይህን ታውቅ ነበር?

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን በፍቅር መያዝ የሚከብዳቸው የእነሱም ወላጆች ተገቢውን ፍቅር ስላልሰጧቸውና ስሜታቸውን ስላልተረዱላቸው ሊሆን ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ወላጆቼ እርማት ሲሰጡኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ወላጆቼ ከመጠን በላይ ነቃፊ እንደሆኑ ከተሰማኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

የሚሰጥህን እርማት መቀበል የሚከብድህ ለምን ሊሆን ይችላል?

ወላጆችህ የምታደርገውን ነገር የሚነቅፉት ለምን ሊሆን ይችላል?

ከሚሰጥህ ከማንኛውም ምክር የላቀ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 177 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከእናቴ ጋር ነጋ ጠባ እንጨቃጨቅ ነበር። አሁን ግን ከአምላክ ቃል የተማርኩትን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ እጥራለሁ። ይህንንም ውጤታማ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እማማ አመለካከቷ እየተለወጠ ነው። እኔም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ማዋሌ የእሷን አስተሳሰብ ይበልጥ ለመረዳት አስችሎኛል። አሁን የተሻለ ግንኙነት አለን።”​—ማርሊን

[በገጽ 180 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚሰጥህ እርማት ምንም ይሁን ምን በውስጡ የሚገኘውን እንደ ውድ ማዕድን የሚቆጠር ጥበብ ለይተህ ካወጣኸው ከወርቅ የበለጠ ዋጋ ያለው ሀብት ይኖርሃል