በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሁሉ የተሻለ ምክር ማግኘት የምችለው ከየት ነው?

ከሁሉ የተሻለ ምክር ማግኘት የምችለው ከየት ነው?

መቅድም

ከሁሉ የተሻለ ምክር ማግኘት የምችለው ከየት ነው?

ለሴቶች

በቅርቡ ወደ ትምህርት ቤታችሁ ስለ መጣው ቆንጆ ልጅ ማሰብሽን ማቆም አልቻልሽም! ‘እሱ እንደሆነ ከነመፈጠሬም አያውቀኝ! ታዲያ ስለ እሱ ባስብ ምን ችግር አለው?’ በማለት ከራስሽ ጋር ትሟገቻለሽ። በዚህ ላይ ደግሞ ስለ እሱ የምታስቢው አንቺ ብቻ አይደለሽም። ሴቶቹ ሁሉ ዓይናቸውን ጥለውበታል። ያለ እሱ ሌላ ወሬ የላቸውም።

ልጁ ወደ አንቺ ዞር ሲል ዓይን ለዓይን ተጋጫችሁ። ልብ የሚሰርቅ ፈገግታውን ስትመለከቺ ልብሽ ትርክክ አለ። አንቺም ፈገግ አለሽ። በዚህ ጊዜ ወደ አንቺ መጥቶ ፈራ ተባ እያለ

“ታዲያስ” አለሽ።

አንቺም “አለን” አልሽው።

“ዮናስ እባላለሁ።”

“አዲስ ገቢ ነህ አይደል?” በማለት ሳታስቢው ጠየቅሽው።

“ከቤተሰቤ ጋር ወደዚህ አካባቢ የመጣሁት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው” በማለት መለሰልሽ።

ከዮናስ ጋር እያወራሽ መሆንሽን ማመን አቅቶሻል!

“እ . . . ዛሬ ከትምህርት በኋላ እኛ ቤት ፓርቲ አዘጋጅቼ ነበር። መምጣት ትፈልጊያለሽ?”

ከዚያም ወደ አንቺ ጠጋ ይልና

“በነገራችን ላይ ወላጆቼ ቤት አይኖሩም፤ በዚያ ላይ መጠጥ እንደ ልብ ይኖራል። አሪፍ ጊዜ ስለምናሳልፍ እንዳያመልጥሽ! እንዴት ነው? ትመጫለሽ?”

ዮናስ መልስሽን እየጠበቀ ነው። ሌሎቹ ልጆች በአንቺ ቦታ ቢሆኑ ዓይናቸውን ሳያሹ እሺ እንደሚሉት የታወቀ ነው!

ምን ትይዋለሽ?

ለወንዶች

ሁለት የክፍልህ ልጆች ወደ አንተ እየመጡ ነው። ገና ስታያቸው ጭንቅ ይልሃል! እነዚህ ልጆች በዚህ ሳምንት ውስጥ ከአንዴም ሁለቴ ሲጋራ እንድታጨስ ለማድረግ ሞክረው ነበር። ይህ ሦስተኛቸው መሆኑ ነው።

አንደኛው ልጅ “ዛሬም ብቻህን ነህ? እስቲ አንድ ጓደኛ ላስተዋውቅህ” ይልሃል። “ጓደኛ” ሲልህ ምን ማለቱ እንደሆነ እንዲገባህ ጠቀስ ያደርግህና ከኪሱ የሆነ ነገር አውጥቶ እጁን ወደ አንተ ይዘረጋል።

ልጁ ሲጋራ የሚመስል ነገር በእጁ ይዟል። በእጁ የያዘው ነገር ምን እንደሆነ አውቀኸዋል፤ በመሆኑም ይባስ ጭንቅ አለህ።

“ይቅርታ አድርጉልኝ። ከዚህ በፊትም ነግሬአችኋለሁ፤ እኔ ሲጋራ . . .”

በዚህ ጊዜ ሁለተኛው ልጅ ንግግርህን አቋርጦ “በሃይማኖትህ ምክንያት ነው አይደል? በቃ በእናንተ ሃይማኖት መዝናናት ክልክል ነው?” ይልሃል።

የመጀመሪያው ልጅ ቀበል አድርጎ “ወይስ ፈርተህ ነው?” አለህ።

በዚህ ጊዜ የሞት ሞትህን “ፈርቼ አይደለም!” አልካቸው።

ከዚያም ሁለተኛው ልጅ አቀፍ አድርጎህ በለሰለሰ አንደበት “ታዲያ ለምን እምቢ ትላለህ? . . . ተቀበለው እንጂ!” አለህ።

የመጀመሪያው ልጅ ሲጋራውን ወደ አንተ እያስጠጋ በሹክሹክታ “ለማንም አንናገርም። ማንም ሰው አያውቅብህም” አለህ።

ምን ታደርጋለህ?

በመላው ዓለም የሚኖሩ ወጣቶች በየቀኑ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። አንዳንድ ወጣቶች እንዲህ ያሉ ፈተናዎችን ለመቋቋም በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ቢሆንም ሌሎች ግን ይህን ለማድረግ ዝግጁ አይደሉም። እንዲያጨስ ተጽዕኖ የሚደረግበት ወጣት ግፊቱ ሲበዛበት ‘ማጨስ ባልፈልግም የእነሱን ውትወታ መቋቋም ግን ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛል። “እንደማንኛውም ልጅ” መሆን እንደምችል ባሳያቸው ምን ችግር አለው?’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። የፍቅር ጓደኝነት እንድትመሠርት ጥያቄ የቀረበላት ወጣት ደግሞ ‘ጸዳ ያለ ልጅ ነው። እሱን እንኳ እሺ ብለው ምናለበት?’ ብላ ታስብ ይሆናል።

በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ወጣቶች ላመኑበት ነገር ጠንካራ አቋም እንዲይዙ የሚያስችላቸውን ሥልጠና አግኝተዋል። በመሆኑም መጥፎ ነገር እንዲፈጽሙ የሚደረግባቸው ጫና ብዙም አያስጨንቃቸውም፤ ይህ ሊያስገርምህ ቢችልም አንተም እንደነዚህ ወጣቶች መሆን ትችላለህ! * እንዴት?

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በልበ ሙሉነት እንድትቋቋም ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ስለሆነ ተወዳዳሪ የሌለው ምክር ይዟል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ሊረዱህ ይችላሉ? ከዚህ በታች የሰፈሩትን ርዕሰ ጉዳዮች ከተመለከትክ በኋላ በተለይ የአንተን ትኩረት በሳቡት ላይ ✔ አድርግ።

ከተቃራኒ ፆታ ጋር የሚኖረኝ ግንኙነት

በጉርምስና ዕድሜ በሰውነቴ ላይ የሚከሰቱ ለውጦች

ጓደኞች ማፍራት

በትምህርት ቤት የሚያጋጥሙ ተጽዕኖዎችን መቋቋም

የገንዘብ አያያዝ

ከወላጆቼ ጋር መግባባት

ስሜቴን መቆጣጠር

የመዝናኛ ምርጫ

መንፈሳዊነቴን ማሳደግ

በገጽ 4 እና 5 ላይ መመልከት እንደምትችለው ከላይ የተዘረዘሩት ርዕሰ ጉዳዮች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙት ዘጠኝ ክፍሎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ምልክት ያደረግኸው በየትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው? እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች የሚዳስሱትን ክፍሎች በመጀመሪያ ማንበብ ትፈልግ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ በሕይወትህ ውስጥ በሚያጋጥሙህ እንዲህ ባሉት ጉዳዮች ረገድ መመሪያ ሊሰጡህ ይችላሉ። ይህ መጽሐፍ፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚረዱህ እንዴት እንደሆነ ያብራራል። *

ይህ መጽሐፍ ሐሳብህን ለመግለጽ የሚያስችሉህ አጋጣሚዎችም ይሰጥሃል። ለምሳሌ ያህል፣ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ አካባቢ “ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ታገኛለህ። ይህ ሣጥን በምዕራፉ ላይ ያነበብከውን ነገር በተግባር ልታውለው ያሰብከው እንዴት እንደሆነ በጽሑፍ እንድታሰፍር ያበረታታሃል። በገጽ 132 እና 133 ላይ እንደሚገኘው “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” እንደሚለው ያሉ ሣጥኖች ደግሞ የሚያጋጥሙህን ፈታኝ ሁኔታዎች አስቀድመህ እንድታስብና እነዚህን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችሉህን መፍትሔዎች እንድታዘጋጅ ይረዱሃል። ከዚህም በተጨማሪ በእያንዳንዱ ክፍል መደምደሚያ ላይ በሚገኘው “የግል ማስታወሻ” በሚለው ገጽ ላይ አንድን ትምህርት በሕይወትህ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ለማድረግ እንዳሰብክ ማስፈር ትችላለህ። በመጽሐፉ ውስጥ “አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች” የሚል ርዕስ ያላቸው ዘጠኝ ገጾች አሉ። ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ የተዉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሰዎች ተሞክሮ በእነዚህ ገጾች ላይ ተጠቅሷል።

መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብን አግኛት፤ ማስተዋልን ያዛት” በማለት ያሳስብሃል። (ምሳሌ 4:5) “ጥበብ” እና “ማስተዋል” የሚሉት ቃላት ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር ለይቶ ከማወቅ የበለጠ ነገርን ያመለክታሉ። ከአንድ ጉዳይ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ መጥፎ ነገር ማድረግ የሚያስከትለውን መዘዝ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም ማወቅህ የእኩዮችህን ተጽዕኖ በልበ ሙሉነትና በድፍረት ለመቋቋም ያስችልሃል።

በአንድ ነገር እርግጠኛ ሁን፦ እያጋጠሙህ ያሉት ችግሮች የቱንም ያህል ከባድ ቢመስሉህ በአንተ ላይ ብቻ የሚደርሱ አይደሉም። ሌሎች ወጣቶችም እንደ አንተ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸው ሲሆን ስኬታማ በሆነ መንገድ ተወጥተዋቸዋል። አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ! ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ በሚገባ ተጠቀምበት። ይህን መጽሐፍ ስታነብ መጽሐፍ ቅዱስ ተወዳዳሪ የሌለው ምክር እንደያዘ ትገነዘባለህ!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.29 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረበው አብዛኛው ክፍል የተወሰደው “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው የንቁ! (በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጅ) መጽሔት ቋሚ ዓምድ ላይ ከወጡት ርዕሶች ነው። ቀደም ሲል በንቁ! መጽሔት ላይ ወጥተው የነበሩት አንዳንዶቹ ሐሳቦች የትርጉም ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል።

^ አን.40 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ወጣቶች ስንገልጽ በአብዛኛው የምንጠቀመው በተባዕታይ ፆታ ቢሆንም ትምህርቱ ለሁለቱም ፆታዎች እንደሚሠራ ግልጽ ነው።