በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሙዚቃ ያለኝ ፍቅር ገደቡን እንዳያልፍ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ለሙዚቃ ያለኝ ፍቅር ገደቡን እንዳያልፍ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 31

ለሙዚቃ ያለኝ ፍቅር ገደቡን እንዳያልፍ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ለሙዚቃ የምትሰጠው ቦታ ምን ያህል ነው?

□ ባልሰማ ምንም አይመስለኝም።

□ ያለ ሙዚቃ መኖር አልችልም።

ሙዚቃ የምታዳምጠው መቼ መቼ ነው?

□ በምጓዝበት ጊዜ

□ በማጠናበት ጊዜ

□ በማንኛውም ጊዜ

የምትወደው ሙዚቃ ምን ዓይነት ነው? ለምንስ? ․․․․․

በሙዚቃ መደሰት አብሮን የተፈጠረ ነገር ይመስላል። ብዙ ወጣቶች ሙዚቃ ሕይወታቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል። “ያለ ሙዚቃ መኖር አልችልም” በማለት የ21 ዓመቷ ሚልካ ትናገራለች። “ሙዚቃ የማላዳምጥበት ጊዜ የለም ማለት እችላለሁ፤ ሌላው ቀርቶ ቤት ሳጸዳ፣ ምግብ ሳበስል፣ ተልኬ ስወጣ ወይም ሳጠና እንኳ ሙዚቃ አዳምጣለሁ።”

የሙዚቃ ምት በሒሳብ ስሌት የሚዘጋጅ ሊሆን ይችላል፤ ሙዚቃው ወደ ጆሮ ሲንቆረቆር ግን በአእምሮ የሚሠራ የሒሳብ ስሌት ከመሆን አልፎ ስሜትን ይኮረኩራል። የአምላክ ቃል ‘በወቅቱ የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው!’ ይላል፤ ሙዚቃም በትክክለኛው ጊዜ ሲደመጥ ምንኛ ያጽናናል! (ምሳሌ 15:23) “ስሜቴን የሚረዳልኝ አንድም ሰው እንደሌለ የሚሰማኝ ጊዜ አለ” በማለት የ16 ዓመቷ ጄሲካ ትናገራለች፤ “የምወደውን ዘፈን ስሰማ ግን የሐዘን ስሜት የሚሰማኝ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ እረዳለሁ።”

ያጋጫችኋል ወይስ ያስማማችኋል?

አንተ ሙዚቃ ብትወድም ወላጆችህ ግን ምርጫቸው ከአንተ የተለየ ሊሆን ይችላል። “አባቴ ‘እስቲ ይሄን ጫጫታህን ዝጋልኝ! ሊያደነቁረኝ እኮ ነው!’ ይለኛል” በማለት አንድ ወጣት ይናገራል። አንተም በዚህ ርዕስ ዙሪያ የሚነሳው ጭቅጭቅ ስልችት ሊልህ ብሎም ወላጆችህ ትንሹን ነገር እያካበዱት እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አንዲት ወጣት “እነሱ ራሳቸው ወጣት የነበሩበትን ጊዜ ለምን አያስታውሱም?” ብላለች፤ “ወላጆቻቸው እነሱ የሚያዳምጡትን ሙዚቃ ይጠሉት እንደነበር ረሱት እንዴ?” ኢንግሬድ የተባለች የ16 ዓመት ወጣትም እንዲህ በማለት ቅሬታዋን ገልጻለች፦ “ትልልቅ ሰዎች ከድሮው ዘመን ጋር መላቀቅ የሚፈልጉ አይመስሉም። የእኛ ዘመን ሙዚቃም የራሱ ለዛ እንዳለው ቢገነዘቡ ጥሩ ነበር!”

ኢንግሬድ የተናገረችው ነገር ልብ ሊባል የሚገባው ነው። በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው ከግል ምርጫ ጋር በተያያዘ በቀድሞው ትውልድና በአዲሱ ትውልድ መካከል ግጭት መፈጠሩ ያለ ነገር ነው፤ አንተም ይህን ሳታስተውል አልቀረህም። ይሁንና እንደዚህ ዓይነት ልዩነት ስላለ ሙዚቃ ሁልጊዜ የግጭት መንስኤ ሊሆን ይገባል ማለት አይደለም። ዋናው ቁም ነገር ከወላጆችህ ጋር የሚያስማማችሁ ነጥብ ማግኘታችሁ ነው። ወላጆችህ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ካላቸው ይህ ለአንተ በጣም ጥሩ ነው። ለምን? ምክንያቱም የአምላክ ቃል አንተም ሆንክ ወላጆችህ፣ ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው ሙዚቃ የትኛው እንደሆነና ለግል ምርጫ የሚተወው የትኛው እንደሆነ ለመለየት እንድትችሉ ይረዳችኋል። ይህን ለማድረግ ሁለት ቁልፍ ነጥቦችን መመርመር ያስፈልግሃል፦ (1) የምታዳምጠው ሙዚቃ የሚያስተላልፈው መልእክት እንዲሁም (2) ሙዚቃ በማዳመጥ የምታሳልፈው ጊዜ። እስቲ በመጀመሪያ የሚከተለውን ጥያቄ እንመርምር፦

የማዳምጠው ሙዚቃ ምን መልእክት ያስተላልፋል?

ሙዚቃ እንደ ምግብ ነው። ጥሩ ምግብ በትክክለኛው መጠን ከተወሰደ ይጠቅማል። መጥፎ ምግብ ግን መጠኑ ምንም ይሁን ምን ጎጂ ነው። የሚያሳዝነው ነገር በሙዚቃ ረገድ አብዛኛውን ጊዜ የሰዎችን ቀልብ የሚስበው መጥፎ የሆነው ሙዚቃ ነው። ስምዖን የተባለ አንድ ወጣት “ጥሩ ዜማ ያላቸው ዘፈኖች ሁሉ ግጥማቸው መጥፎ የሚሆነው ለምን እንደሆነ አይገባኝም” በማለት ምሬቱን ገልጿል።

ዜማውን እስከወደድከው ድረስ መልእክቱ ያን ያህል ለውጥ ያመጣል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘አንድ ሰው መርዝ ሊያበላኝ ቢፈልግ እኔን ለማታለል ምን ያደርጋል? ኮምጣጤ ውስጥ ጨምሮ ያቀርብልኛል ወይስ ከጣፋጭ ነገር ጋር ቀላቅሎ ይሰጠኛል?’ ኢዮብ የተባለው ታማኝ ሰው “ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፣ ጆሮ ቃላትን አይለይምን?” በማለት ጠይቋል። (ኢዮብ 12:11) መርዝ ከጣፋጭ ነገር ጋር ተቀላቅሎ ስለቀረበ ብቻ እንደማትበላው ሁሉ አንድ ሙዚቃም ዜማው ደስ ስለሚል ብቻ ዝም ብለህ ማዳመጥ የለብህም፤ ከዚህ ይልቅ ርዕሱንና ግጥሙን በመገምገም ‘ቃላቱን ለመለየት’ ሞክር። እንዲህ ማድረግ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው? ምክንያቱም በሙዚቃው ውስጥ ያሉት ግጥሞች በአስተሳሰብህና በዝንባሌህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

በዛሬው ጊዜ የሚወጡት የሰዎችን ትኩረት የሚስቡ አብዛኞቹ ሙዚቃዎች የፆታ ብልግናን፣ ዓመፅንና አደንዛዥ ዕፅ መውሰድን የሚያበረታቱ ግጥሞች የያዙ መሆናቸው በጣም ያሳዝናል። እንደዚህ ዓይነት ግጥም ያላቸውን ሙዚቃዎች ማዳመጥ እንደማይጎዳህ የሚሰማህ ከሆነ “መርዙ” ሥራውን መሥራት ጀምሯል ማለት ነው።

የራስህን ውሳኔ አድርግ

እኩዮችህ ወራዳ የሆነ ሙዚቃ እንድታዳምጥ ከፍተኛ ግፊት ያደርጉብህ ይሆናል። የሙዚቃው ኢንዱስትሪም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ሬዲዮ፣ ኢንተርኔትና ቴሌቪዥን ሙዚቃ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ትርፍ የሚያስገኝና ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ኢንዱስትሪ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል። የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ችሎታ ባላቸው የገበያ ጥናት ባለሙያዎች በመጠቀም በሙዚቃ ምርጫህ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደርና በራስህ ሳይሆን በብዙኃኑ ምርጫ እንድትመራ ለማድረግ ይጥራል።

ይሁንና እኩዮችህ ወይም የመገናኛ ብዙኃን የምታዳምጠውን ሙዚቃ እንዲመርጡልህ ከፈቀድህ በራስህ የመወሰን መብትህን ለሌሎች አሳልፈህ ትሰጣለህ። በራስህ አእምሮ የማትመራ የሌሎች ባሪያ ትሆናለህ። (ሮም 6:16) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዓለም እንደነዚህ ባሉ ጉዳዮች ረገድ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቋቋም እንዳለብህ አጥብቆ ያሳስባል። (ሮም 12:2) በመሆኑም ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንድትችል የማስተዋል ችሎታህን’ ማሠልጠንህ አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 5:14) የምታዳምጠውን ሙዚቃ በምትመርጥበት ወቅት በማስተዋል ችሎታህ መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ልብ በል፦

ሽፋኑን ተመልከት። ሙዚቃው በውስጡ የያዘውን መልእክት ለማወቅ አብዛኛውን ጊዜ ሽፋኑን ወይም ማስታወቂያውን ማየት ብቻ ይበቃል። ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው፣ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ወይም ከመናፍስታዊ ሥራዎች ጋር የተያያዙ ሥዕሎችን ሽፋኑ ወይም ማስታወቂያው ላይ ከተመለከትክ ይህ ሊያነቃህ ይገባል። ውጪው እንደዛ ከሆነ ውስጡም መጥፎ ሊሆን ይችላል።

የግጥሙን ይዘት ለማወቅ ሞክር። ሙዚቃው ስለ ምንድን ነው? የያዘው መልእክት ደጋግመህ ልታዳምጠው የምትችለው ዓይነት ነው? ወይም አብረኸው ብታዜም ምንም የማይጨንቅህ ዓይነት ነው? የሚያስተላልፈው ሐሳብ አንተ ከምታምንባቸው ነገሮችና ከክርስቲያናዊ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ነው? የውጭ አገርን ጨምሮ በሌላ ቋንቋ የተዘጋጀ ሙዚቃ የምታዳምጥ ከሆነ የግጥሙ ይዘት ከሥነ ምግባር አንጻር ተቀባይነት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት አድርግ።​—ኤፌሶን 5:3-5

የሚያሳድርብህን ስሜት አስተውል። “ከማዳምጣቸው ሙዚቃዎች መካከል የአብዛኞቹ ዜማና ግጥም በሐዘን ስሜት እንድዋጥ ያደርገኛል” በማለት ፊሊፕ የተባለ ወጣት ይናገራል። እርግጥ ነው፣ ሙዚቃ በሰዎች ላይ የሚያሳድረው ስሜት የተለያየ ነው። ታዲያ አንተ የምታዳምጠው ሙዚቃ ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥርብሃል? ራስህን እንደሚከተለው በማለት ጠይቅ፦ ‘ይህን ሙዚቃ ከሰማሁ በኋላ መጥፎ ሐሳቦች ይመጡብኛል? በሙዚቃው ውስጥ የሚገኙት አስጸያፊ ቃላት በንግግሬ ውስጥ መግባት ጀምረዋል?’​—1 ቆሮንቶስ 15:33

የሌሎችን ስሜት ከግምት አስገባ። ወላጆችህ ስለምታዳምጠው ሙዚቃ ምን ይሰማቸዋል? አስተያየት እንዲሰጡህ ጠይቃቸው። የእምነት ባልንጀሮችህ ስለ ሙዚቃው ምን እንደሚሰማቸውም አስብ። አንዳንዶች አንተ የምታዳምጠውን ሙዚቃ መስማት ሕሊናቸውን ይረብሸዋል? ለሌሎች ስሜት ስትል ባሕርይህን ማስተካከልህ የጉልምስና ምልክት ነው።​—ሮም 15:1, 2

ከላይ ያሉትን ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅህ መንፈስህን የሚያድስ ሆኖም መንፈሳዊነትህን የማይጎዳ ሙዚቃ ለመምረጥ ያስችልሃል። ይሁን እንጂ ልታጤነው የሚገባ ሌላም ነገር አለ።

በዛ የሚባለው መቼ ነው?

ጥሩ ሙዚቃ ልክ እንደ ጥሩ ምግብ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ጥበብ ያዘለ አንድ ምሳሌ “ማር ስታገኝ በልክ ብላ፤ ከበዛ ያስመልስሃል” ይላል። (ምሳሌ 25:16) ማር በመድኃኒትነቱ ይታወቃል። ያም ቢሆን ጥሩ ነገር እንኳ ከበዛ ጎጂ ሊሆን ይችላል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ጥሩ ነገርም ቢሆን የሚጠቅመው በልክ ሲሆን ነው።

አንዳንድ ወጣቶች ግን ሙዚቃ ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠረው ፈቅደዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጄሲካ እንዲህ ብላለች፦ “በማንኛውም ጊዜ ሌላው ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስ ሳጠናም እንኳ ሙዚቃ አዳምጣለሁ። እንዲህ ማድረጌ ትኩረቴን ለመሰብሰብ እንደሚረዳኝ ለወላጆቼ ብነግራቸውም ሊያምኑኝ አልቻሉም።” አንተም እንደ ጄሲካ ይሰማሃል?

ሙዚቃ በማዳመጥ የምታሳልፈው ጊዜ በዝቷል የሚባለው መቼ ነው? መልሱን ለማግኘት ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦

በየቀኑ ሙዚቃ በማዳመጥ ምን ያህል ጊዜ አሳልፋለሁ? ․․․․․

በየወሩ ለሙዚቃ ምን ያህል ገንዘብ አወጣለሁ? ․․․․․

ሙዚቃ ከቤተሰቤ ጋር ያለኝን ግንኙነት እየነካብኝ ነው? ከሆነ ይህንን ሁኔታ እንዴት ማስተካከል እንደምትችል ከዚህ በታች ጻፍ። ․․․․․

ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብህ ይሆን?

ሙዚቃ አብዛኛውን ጊዜህን እየተሻማብህ ከሆነ ገደብ ማበጀትህና ይበልጥ ሚዛናዊ መሆንህ የተሻለ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቀኑን ሙሉ ጆሮህ ላይ ማዳመጫ ሰክተህ የምትውል ከሆነ ወይም ቤት እንደገባህ የመጀመሪያ ሥራህ ሙዚቃ መክፈት ከሆነ ይህን ልማድህን ማስተካከል ይኖርብህ ይሆናል።

እንዲያውም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ጸጥታ በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ መሆንን ለምን አትማርም? እንዲህ ማድረግህ በጥናትህ ወቅትም ሊረዳህ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ስምዖን “ሙዚቃው ከጠፋ በተሻለ መንገድ ማጥናት ትችላለህ” ብሏል። ሙዚቃ ሳትከፍት ማጥናትህ ትኩረትህን ለማሰባሰብ ይረዳህ እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር።

የአምላክን ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ለማጥናትም ጊዜ መመደብ ያስፈልግሃል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጸለይና ለማሰላሰል ሲል ጸጥ ወዳለ ስፍራ የሄደባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ማርቆስ 1:35) አንተስ የምታጠናበት ቦታ ጸጥታ የሰፈነበትና ሰላማዊ ነው? ካልሆነ መንፈሳዊ እድገትህን እያቀጨጭከው ሊሆን ይችላል።

ጥሩ ምርጫ አድርግ

ሙዚቃ ከአምላክ ያገኘነው ትልቅ ስጦታ ነው፤ ሆኖም ይህን ስጦታ አላግባብ እንዳትጠቀምበት መጠንቀቅ ያስፈልግሃል። “ያሉኝን አንዳንድ ሙዚቃዎች ማስወገድ እንደሚገባኝ ባውቅም በጣም ስለምወዳቸው አስቀምጫቸዋለሁ” በማለት እንደተናገረችው ማርሊን የተባለች ወጣት ልትሆን አይገባም። ይህች ወጣት መጥፎ የሆነ ነገር መስማቷ አእምሮዋንና ልቧን ምን ያህል እንደሚበርዘው አስብ! እንዲህ ካለው ወጥመድ ራስህን ጠብቅ። ሙዚቃ አስተሳሰብህን እንዳይበክለው ወይም ሕይወትህን እንዳይቆጣጠረው ተጠንቀቅ። የምታዳምጠውን ሙዚቃ ስትመርጥ ላቅ ያሉትን ክርስቲያናዊ መሥፈርቶች ለመከተል ጥረት አድርግ። አምላክ መመሪያና ድጋፍ እንዲሰጥህ ጸልይ። እንደ አንተ ዓይነት አቋም ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሥርት።

ሙዚቃ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና ዘና እንድትል ሊረዳህ ይችላል። የብቸኝነትን ስሜት ለማሸነፍም ይረዳህ ይሆናል። ሆኖም ሙዚቃው ሲያበቃ ችግሮቹ ባሉበት እንደሚጠብቁህ አትዘንጋ። ደግሞም ሙዚቃ የእውነተኛ ጓደኞች ምትክ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ሙዚቃ በሕይወትህ ውስጥ ትልቁን ቦታ እንዲይዝ ማድረግ የለብህም። ገደቡን እንዳያልፍ ተጠንቀቅ እንጂ በሙዚቃ መዝናናትህ ምንም ችግር የለውም።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

አልፎ አልፎ መዝናናት እንደሚያስፈልግህ የታወቀ ነው። ታዲያ በመዝናናት የምታሳልፈውን ጊዜ ይበልጥ በተሻለ መንገድ እንድትጠቀምበት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚረዱህ እንዴት ነው?

ቁልፍ ጥቅስ

ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፣ ጆሮ ቃላትን አይለይምን?”​ኢዮብ 12:11

ጠቃሚ ምክር

ወላጆችህ አንተ አንድን ሙዚቃ የወደድክበትን ምክንያት እንዲረዱልህ ከፈለግህ እነሱ የሚወዱትን ሙዚቃ አዳምጥ። እንዲህ ማድረግህ እነሱም የአንተን ስሜት ለመረዳት ያነሳሳቸው ይሆናል።

ይህን ታውቅ ነበር?

ወላጆችህ የምትወደውን ሙዚቃ እንዲሰሙ የማትፈልግ ከሆነ ይህ ሙዚቃው ችግር እንዳለው የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ለሙዚቃ የምሰጠው ቦታ ገደብ እንዲኖረው እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

እኩዮቼ መጥፎ ሙዚቃ እንዳዳምጥ ግፊት የሚያደርጉብኝ ከሆነ እንዲህ እላቸዋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

የሙዚቃ ምርጫህን በቁም ነገር ልትመለከተው የሚገባው ለምንድን ነው?

አንድ ዘፈን ተቀባይነት ያለው መሆንና አለመሆኑን መለየት የምትችለው እንዴት ነው?

የተለያዩ ዓይነት ሙዚቃዎችን ማጣጣምን ለመልመድ ምን ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 259 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ጥሩ እንዳልሆነ የማውቀውን ሙዚቃ ሳላስበው የማዳምጥበት ጊዜ አለ። መጥፎ መሆኑ ትዝ ሲለኝ ግን ሙዚቃውን ወዲያውኑ አጠፋዋለሁ። አለበለዚያ ሙዚቃውን ለማዳመጥ ሰበብ መፈላለግ እጀምራለሁ።”​—ካምረን

[በገጽ 258 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የተለያዩ ዓይነት ሙዚቃዎችን ማጣጣም ልመድ

የአምስት ዓመት ልጅ ከነበርክበት ጊዜ ይልቅ አሁን የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን መብላት ያስደስትሃል? አዎ ብለህ ከመለስክ ይህ የሆነው አዳዲስ የምግብ ዓይነቶችን ማጣጣም ስለለመድክ ነው። ከሙዚቃ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ዓይነት ሙዚቃ ብቻ ከማዳመጥ ይልቅ የተለያዩ ዓይነት ሙዚቃዎችን ማጣጣምን ልመድ።

ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወትን መማር ነው። እንዲህ ማድረግ ችሎታህን የሚፈታተንና የሚያስደስት ከመሆኑም ሌላ ገበያ ላይ ከሚቀርበው የተለመደ ሙዚቃ በተጨማሪ ሌላ ዓይነት ሙዚቃዎችን ለማዳመጥ አጋጣሚ ሊፈጥርልህ ይችላል። ለመማር የሚያስችል ጊዜ እንዴት ማግኘት ትችላለህ? ቴሌቪዥን በማየት ወይም የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን በመጫወት የምታሳልፈውን ጊዜ መቀነስ ትችላለህ። አንዳንድ ወጣቶች የተናገሩትን ሐሳብ ተመልከት።

“የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት በጣም አስደሳች ከመሆኑም ሌላ ስሜትህን ለመግለጽ የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው። አዳዲስ ዘፈኖችን መጫወት መማሬ የተለያዩ የሙዚቃ ዓይነቶችን እንድወድ አድርጎኛል።”​—ብራያን 18፤ ጊታር፣ ታምቡርና ፒያኖ ይጫወታል።

“አንድን የሙዚቃ መሣሪያ በደንብ መጫወት እንድትችል ልምምድ ማድረግ ያስፈልግሃል። እርግጥ ነው፣ ልምምድ ማድረግ ሁልጊዜ አስደሳች ላይሆን ይችላል። ይሁንና አንድን ዘፈን ጥሩ አድርገህ መጫወት ስትችል አንድ ነገር እንዳከናወንክ ስለሚሰማህ ደስ ይልሃል።”​—ጄድ 13፤ ቪዮላ የተባለ የሙዚቃ መሣሪያ ትጫወታለች።

“ውሎዬ ጥሩ በማይሆንበት ጊዜ ወይም ሲከፋኝ ጊታሬን መጫወት ዘና እንድል ያደርገኛል። ደስ የሚልና የሚያረጋጋ ሙዚቃ መጫወት ጥሩ ስሜት ይፈጥራል።”​—ቨኔሳ 20፤ ጊታር፣ ፒያኖና ክላርኔት ትጫወታለች።

“‘መቼም ቢሆን እንደ እገሌ ወይም እንደ እገሊት መጫወት የምችል አይመስለኝም’ ብዬ አስብ ነበር። ሆኖም ሥራዬ ብዬ ተለማመድኩ፤ አሁን አንድን ሙዚቃ ጥሩ አድርጌ ስጫወት ልዩ እርካታ ይሰማኛል። ከዚህም በተጨማሪ የሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወቱ ሰዎችን ስመለከት ችሎታቸውን ይበልጥ ማድነቅ ጀምሬያለሁ።”​—ያዕቆብ 20፤ ጊታር ይጫወታል።

[በገጽ 255 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙዚቃ እንደ ምግብ ነው። ጥሩ ምግብ በትክክለኛው መጠን ከተወሰደ ይጠቅማል። መጥፎ ምግብ ግን መጠኑ ምንም ይሁን ምን ጎጂ ነው