በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ አምላክ በድፍረት መናገር የምችለው እንዴት ነው?

ስለ አምላክ በድፍረት መናገር የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 36

ስለ አምላክ በድፍረት መናገር የምችለው እንዴት ነው?

ስለ እምነትህ ለክፍልህ ልጆች ከመናገር ወደኋላ የምትለው ለምን ሊሆን ይችላል?

□ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በደንብ ስለማላውቅ

□ እንዳይሾፍብኝ ስለምፈራ

□ ምን ብዬ እንደምጀምር ስለማላውቅ

ስለ እምነትህ ለመናገር የትኛውን መንገድ ትመርጣለህ?

□ ከአንድ ልጅ ጋር ለብቻ መወያየት

□ በክፍሌ ተማሪዎች ፊት መናገር

□ የጽሑፍ ሪፖርት ሳቀርብ ስለ እምነቴ መግለጽ

አንተ ውይይቱን ብትጀምር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመነጋገር ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል ብለህ የምታስበው ልጅ አለ? ካለ ስሙን ጻፍ። ․․․․․

አብረውህ የሚማሩት ልጆች ስለ ፈጣሪ አንስቶ መወያየት ብዙም አይማርካቸው ይሆናል። ከዚህ ሌላ ስለ ማንኛውም ርዕስ ለምሳሌ ስለ ስፖርት፣ ስለ ፋሽን ወይም ስለ ተቃራኒ ፆታ ቢነሳ የሞቀ ጨዋታ ሊጀመር ይችላል። ስለ አምላክ ማውራት ብትጀምር ግን ያን ያህል አይጥማቸው ይሆናል።

ይህ የሚሆነው እኩዮችህ በአምላክ ስለማያምኑ አይደለም፤ እንዲያውም ብዙ ወጣቶች በፈጣሪ መኖር ያምናሉ። ይሁንና አንዳንዶች ስለዚህ ርዕስ መወያየት ያሳፍራቸዋል። ‘ብዙም አይመችም’ ብለው ያስቡ ይሆናል።

አንተስ?

አብረውህ ለሚማሩት ልጆች ስለ አምላክ መናገር ቢከብድህ ምንም አያስገርምም። በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማጣት ደስ አይልም፤ መሳቂያ መሆን ደግሞ ከዚህም የባሰ ነው! ስለ እምነትህ ብትናገር እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥምህ ይችላል? አዎን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እኩዮችህ ያልጠበቅኸው ምላሽ ሊሰጡህ ይችላሉ። ብዙዎቹ እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይሻሉ፦ የዚህ ዓለም መጨረሻ ምን ይሆን? ዓለማችን በችግር የተሞላው ለምንድን ነው? እኩዮችህ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከትልቅ ሰው ይልቅ በዕድሜ ከሚመጥናቸው ሰው ጋር ቢወያዩ ይመርጣሉ።

ያም ቢሆን ስለ ሃይማኖት ከእኩዮችህ ጋር መነጋገር ዳገት ሊሆንብህ ይችላል። ምናልባትም የክፍልህ ልጆች አክራሪ እንደሆንክ አድርገው እንዳያዩህ ትፈራ ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ ‘መናገር ያለብኝን በትክክል ሳልናገር ብቀርስ’ የሚል ስጋት ያድርብህ ይሆናል። ስለ እምነትህ መናገር የሙዚቃ መሣሪያ ከመጫወት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ነው አይደል? ስትለምደው ግን እየቀለለህ የሚሄድ ከመሆኑም በላይ ጥረትህ ጥሩ ውጤት ያስገኝልሃል። ታዲያ ስለ እምነትህ ለመናገር እንዴት መጀመር ትችላለህ?

ብዙውን ጊዜ በቀላሉ ውይይት መክፈት የምትችልባቸው የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ወቅታዊ በሆነ አንድ ጉዳይ ላይ በትምህርት ቤት ውስጥ ውይይት ቢጀመር አንተም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ሐሳብህን መግለጽ ትችላለህ። ወይም አንድ የክፍልህን ልጅ በግል ልታነጋግረው ትችላለህ። ከዚህም የሚቀል አንድ ዘዴ አለ፦ አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች እንደሚያደርጉት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ጠረጴዛህ ላይ በማስቀመጥ ልጆቹ እንዲያዩት ማድረግ ትችላለህ። ብዙውን ጊዜ ጽሑፎቹ የልጆቹን ትኩረት ስለሚስቡ ውይይት መጀመር ቀላል ይሆንልሃል!

ከላይ ከተጠቀሱት ዘዴዎች መካከል አንተ የትኛውን ለመጠቀም መረጥክ? ․․․․․

አብሮህ ለሚማር ልጅ ስለ እምነትህ መናገር የምትችልበት ሌላ ዘዴ አለ? ያሰብከውን ከታች ጻፍ።

․․․․․

አንዳንድ ጊዜ በትምህርት ቤት የሚሰጥህ የቤት ሥራ ወይም ፕሮጀክት በራሱ ስለ እምነትህ ለመመሥከር አጋጣሚ ይከፍትልህ ይሆናል። ለምሳሌ ስለ ዝግመተ ለውጥ ቢነሳ ምን ማድረግ ትችላለህ? ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው?

ስለ ፍጥረት ማስረዳት

ራየን የተባለ ወጣት “በክፍል ውስጥ ስለ ዝግመተ ለውጥ ስንማር የቀረበው ሐሳብ ከዚያ ቀደም የተማርኩትን የሚያፈርስ ነበር። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የተረጋገጠ እውነት እንደሆነ ተደርጎ ስለቀረበ ከዚህ የተለየ ሐሳብ ማቅረቡ አስፈራኝ” በማለት ተናግሯል። ራኬብ የተባለች ወጣትም እንደዚህ ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የኅብረተሰብ ትምህርት መምህሬ በሚቀጥለው ክፍለ ጊዜ የምንማረው ስለ ዝግመተ ለውጥ መሆኑን ስትናገር በጣም ፈርቼ ነበር። በዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ ረገድ አቋሜን በክፍል ውስጥ ማስረዳት እንደሚጠበቅብኝ ታውቆኝ ነበር።”

አንተስ በክፍል ውስጥ የዝግመተ ለውጥ ርዕስ ሲነሳ ምን ይሰማሃል? አንተ የምታምነው ‘ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው’ አምላክ መሆኑን ነው። (ራእይ 4:11) በዙሪያህ የምትመለከታቸው ነገሮች ሁሉ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ እንደሠራቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። ይሁን እንጂ የመማሪያ መጻሕፍቱና አስተማሪህ ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው ይላሉ። ‘ታዲያ እኔ ማን ሆኜ ነው ከእነዚህ ሁሉ “ምሑራን” ጋር የምሟገተው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

አይዞህ፣ በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የማታምነው አንተ ብቻ አይደለህም። በርካታ የሳይንስ ሊቃውንትም ሳይቀር የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ አይቀበሉትም። ብዙ መምህራንና ተማሪዎችም ቢሆኑ በዝግመተ ለውጥ አያምኑም።

ያም ቢሆን በፈጣሪ እንደምታምን በሚገባ ለማስረዳት መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምር ማወቅ ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ሐሳብ በማይሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ መከራከር አያስፈልግህም። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት፦

የሳይንስ መማሪያ መጽሐፌ መሬትና ሥርዓተ ፀሐይ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደኖሩ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምድርን ጨምሮ መላው ጽንፈ ዓለም የመጀመሪያው የፍጥረት ቀን ከመጀመሩ በፊት እንደነበረ ይናገራል። በመሆኑም ምድርና ሥርዓተ ፀሐይ በቢሊዮን ዓመታት የሚቆጠር ዕድሜ ሊኖራቸው ይችላል።​—ዘፍጥረት 1:1

ምድርና በውስጧ ያሉት ነገሮች በስድስት ቀናት ውስጥ ሊፈጠሩ እንደማይችሉ አስተማሪዬ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ስድስቱ የፍጥረት ቀናት፣ ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ እንደነበራቸው አይገልጽም።

በጊዜ ሂደት በእንስሳትና በሰዎች ላይ የታዩ ለውጦች እንዳሉ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን በክፍል ውስጥ ተመልክተናል። አምላክ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች “እንደየወገናቸው” እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:20, 21) ሕይወት ያለው ነገር ሕይወት ከሌለው ነገር እንደመጣ ወይም አምላክ በአንድ ሴል አማካኝነት የዝግመተ ለውጥን ሂደት እንዳስጀመረ የሚገልጸውን ሐሳብ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፍም። ቢሆንም እያንዳንዱ ‘ወገን’ ወይም ዝርያ ዓይነቱ ብዙ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እያንዳንዱ ፍጥረት ‘ከወገኑ’ ሳይወጣ ለውጥ ሊያካሂድ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ አይቃወምም።

አስተማሪህ ወይም የክፍልህ ልጅ እንደሚከተሉት ያሉ ሐሳቦች ቢያነሱ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ካገኘኸው ትምህርት አንጻር ምን ብለህ ትመልሳለህ?

“ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ መሆኑን ሳይንስ አረጋግጧል።” ․․․․․

“አምላክን ላየው ስለማልችል በእሱ መኖር አላምንም።” ․․․․․

ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ ሁን!

ወላጆችህ ክርስቲያኖች ከሆኑ በፍጥረት የምታምነው እነሱ ስላስተማሩህ ብቻ ሊሆን ይችላል። እያደግህ ስትሄድ ግን አምላክን ‘በማሰብ ችሎታህ ተጠቅመህ’ ማምለክ ትፈልጋለህ፤ በሌላ አባባል ለምታምንባቸው ነገሮች ጽኑ መሠረት ሊኖርህ ይገባል። (ሮም 12:1) እንግዲያው ‘እኔ በግሌ ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳምነኝ ምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ይህን ጥያቄ ለመመለስ የ14 ዓመቱ ሳም የሰውን አካል በምሳሌነት ይጠቅሳል። እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ ነገር እጅግ የረቀቀና ውስብስብ ነው። እንዲሁም ሁሉም የአካል ክፍሎች ግሩም በሆነ ሁኔታ ተቀናጅተው ይሠራሉ። የሰው አካል የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ሊሆን አይችልም!” ሆሊ የተባለችው የ16 ዓመት ወጣትም በዚህ ትስማማለች። እንዲህ ትላለች፦ “የስኳር በሽታ እንዳለብኝ ከተነገረኝ ጊዜ ጀምሮ የሰው አካል እንዴት እንደሚሠራ ብዙ ተምሬያለሁ። ለምሳሌ ቆሽት፣ በጨጓራና በአንጀት መሃል ተወሽቃ የምትገኝ አንዲት ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ደምና ሌሎች የአካላችን ክፍሎች በትክክል መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ ረገድ ምን ያህል ትልቅ ድርሻ እንደምታበረክት መመልከቱ በጣም ያስደንቃል።”

አንተ በግልህ ፈጣሪ መኖሩን እንድታምን የሚያደርጉህን ሦስት ምክንያቶች ከዚህ በታች ጻፍ።

1. ․․․․․

2. ․․․․․

3. ․․․․․

በአምላክና በፍጥረት የምታምን በመሆንህ የምትሸማቀቅበት ወይም የምታፍርበት ምንም ምክንያት የለም። ማስረጃዎቹን ሁሉ ስንመረምር ድንቅ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ እንደሠራን ማመን ፍጹም ምክንያታዊ ሆኖ እናገኘዋለን።

እንዲያውም ያላንዳች አሳማኝ ማስረጃ በጭፍን እንድናምን የሚጠይቅብን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እንጂ በፈጣሪ ማመን አይደለም፤ በዝግመተ ለውጥ ማመን ተአምር ሠሪ ሳይኖር በተፈጸመ ተአምር የማመን ያህል ነው! በማሰብ ችሎታህ ተጠቅመህ ጉዳዩን በጥንቃቄ ካጤንከው ስለ አምላክ ለመናገር የበለጠ ድፍረት ይኖርሃል።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

በአንተ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ሲጠመቁ ትመለከት ይሆናል። አንተስ ለመጠመቅ ዝግጁ ነህ?

ቁልፍ ጥቅስ

“በምሥራቹ አላፍርም፤ እንዲያውም ምሥራቹ ለሚያምን ሁሉ . . . መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው።”​—ሮም 1:16

ጠቃሚ ምክር

ስለ እምነትህ ስትናገር ሐሳብህን ለምትገልጽበት መንገድ ትኩረት ልትሰጠው ይገባል። ሁኔታህ በእምነትህ እንደምታፍር የሚያሳይ ከሆነ እኩዮችህ እንዲያሾፉብህ መንገድ ትከፍታለህ። ይሁንና አብረውህ የሚማሩት ልጆች የራሳቸውን አመለካከት ሲገልጹ እንደሚያደርጉት አንተም በልበ ሙሉነት የምትናገር ከሆነ በእነሱ ዘንድ አክብሮት ማትረፍህ አይቀርም።

ይህን ታውቅ ነበር?

አንዳንድ ጊዜ አስተማሪዎች የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ ይህን ማድረግ ያቅታቸዋል፤ በዚህ ጊዜ ጽንሰ ሐሳቡን የተቀበሉት በእርግጥ አምነውበት ሳይሆን በዚህ መንገድ ስለተማሩ ብቻ መሆኑን ይገነዘባሉ።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ከክፍሌ ልጅ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለመጀመር እንዲህ ማለት እችላለሁ፦ ․․․․․

በፈጣሪ የማምነው ለምን እንደሆነ ብጠየቅ እንዲህ እላለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ስለምታምንባቸው ነገሮች ለሌሎች መናገር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

● በትምህርት ቤት ውስጥ በፍጥረት እንደምታምን ለመናገር ቀላል የሚሆኑልህ የትኞቹ ዘዴዎች ናቸው?

● ሁሉን ነገር ለፈጠረው አምላክ አመስጋኝ መሆንህን እንዴት መግለጽ ትችላለህ?​—የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27

[በገጽ 299 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ትምህርት ቤት እኛ ብቻ መስበክ የምንችልበት የአገልግሎት ክልል ነው።”​—ኢራይዳ

[በገጽ 298 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እምነትህ መናገር ልክ የሙዚቃ መሣሪያ እንደ መጫወት ችሎታ ይጠይቃል፤ በተለማመድክ ቁጥር ይበልጥ ብቃት እያዳበርክ ትሄዳለህ

[በገጽ 300 እና 301 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እምነትህ በመናገር ረገድ የሚሰማህን ፍርሃት ማሸነፍ ትችላለህ