በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የጤና ችግር ቢኖርብኝ ምን ላድርግ? (ክፍል 2)

የጤና ችግር ቢኖርብኝ ምን ላድርግ? (ክፍል 2)

 ሰዎች የተለያዩ ዓይነት የጤና ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።

  •   አንዳንዶች ያለባቸው የጤና ችግር በቀላሉ ለሌሎች ይታያል፤ ሌሎች ግን ለሌሎች በግልጽ በማይታይ ሕመም ይሠቃያሉ።

  •   አንዳንዶች የሚያምማቸው አልፎ አልፎ ሲሆን ሌሎች ግን በየቀኑ ከበሽታቸው ጋር ይታገላሉ።

  •   አንዳንድ ሰዎች በሽታቸውን ሊቆጣጠሩት ወይም መድኃኒት ሊያገኙለት ይችላሉ፤ ሌሎች ግን በሽታቸው እየተባባሰ የሚሄድ አልፎ ተርፎም ለሕይወታቸው አስጊ ሊሆን ይችላል።

 ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት የጤና ችግሮች በሙሉ ወጣቶችንም ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። በዚህ ርዕስ ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር ያጋጠማቸው አራት ወጣቶችን እንመለከታለን። አንተም አንድ ዓይነት የጤና ችግር ካለብህ ከሚናገሩት ሐሳብ ማበረታቻ ማግኘት ትችላለህ።

 ጌናኤል

 ከሁሉ የሚከብደኝ የአቅም ገደብ እንዳለብኝ አምኜ መቀበል ነው። ብዙ ነገሮችን ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ይሁን እንጂ በየቀኑ ራሴን ካለሁበት ሁኔታ ጋር ማስማማት ያስፈልገኛል።

 ሞተር ኒውሮመስኩላር ዲስኦርደር የተባለ በሽታ አለብኝ፤ ይህ በሽታ መረጃ ከአንጎል ወደ ሰውነት በትክክል እንዳይተላለፍ የሚያደርግ ነው። አንዳንዴ ከራስ ጸጉሬ እስከ እግር ጥፍሬ ያሉ የሰውነቴ ክፍሎች ይንቀጠቀጣሉ ወይም ደግሞ ሽባ ይሆናሉ። በዚህ ምክንያት እንደ መራመድ፣ መናገር፣ ማንበብ፣ መጻፍና የሌሎችን ሐሳብ መረዳት ያሉ ቀላል ነገሮችን እንኳ ማድረግ ከባድ ይሆንብኛል። በሽታው በጣም ሲጠናብኝ የጉባኤያችን ሽማግሌዎች መጥተው ይጸልዩልኛል። እንዲህ ሲያደርጉ ወዲያውኑ እረጋጋለሁ።

 ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመኝ ይሖዋ እንደሚደግፈኝና እንደሚያጸናኝ ይሰማኛል። ያለብኝ በሽታ እሱን በሙሉ ልቤ ከማገልገል እንዲያግደኝ አልፈልግም። ሌሎች ሰዎች ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጠውን ተስፋ እንዲያውቁ መርዳትን በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ እሰጠዋለሁ፤ በቅርቡ አምላክ ምድርን ገነት የሚያደርጋት ሲሆን መከራን ሁሉ ያስወግዳል።​—ራእይ 21:1-4

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ አንተስ እንደ ጋናኤል ለሌሎች ያለህን አሳቢነት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?​—1 ቆሮንቶስ 10:24፤ 10:24

 ዛካሪ

 በ16 ዓመቴ፣ እየተስፋፋ የሚሄድ የአንጎል ካንሰር እንዳለብኝ ታወቀ። ሐኪሞች በስምንት ወር ውስጥ እንደምሞት ነግረውኝ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሕይወቴን ለማቆየት እየታገልኩ ነው።

 ዕጢው ያለበት ቦታ በስተ ቀኝ በኩል ያለው የሰውነቴ ክፍል ሙሉ በሙሉ ሽባ እንዲሆን አድርጎታል። መራመድ ስለማልችል እኔን ከቦታ ወደ ቦታ ለማንቀሳቀስ አንድ ሰው ቤት ቤት ይውላል።

 በሽታዬ እየተባባሰ በመምጣቱ ከሰዎች ጋር መነጋገር ከባድ እየሆነብኝ ሄደ። ልጅ እያለሁ በጣም እንቀሳቀስ ነበር፤ ውኃ ላይ መንሸራተት እንዲሁም ቅርጫት ኳስና መረብ ኳስ መጫወት ያስደስተኛል። የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ተጠምጄ ነበር። ብዙ ሰዎች፣ በጣም የሚወዱትን ነገር ማድረግ አለመቻል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚረዱት አይመስለኝም።

 በኢሳይያስ 57:15 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በጣም አበረታትቶኛል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ‘መንፈሳቸው የተሰበረውን’ እንደሚረዳና ለእኔም እንደሚያስብልኝ ማረጋገጫ ሰጥቶኛል። በተጨማሪም በኢሳይያስ 35:6 ላይ የሚገኘው ይሖዋ የሰጠው ተስፋ በጣም አጽናንቶኛል፤ ጥቅሱ ወደፊት እንደገና በእግሬ መራመድ እንደምችልና ፍጹም ጤንነት አግኝቼ ይሖዋን እንደማገለግለው የሚገልጽ ሐሳብ ይዟል።

 አንዳንድ ጊዜ ሕመሜን መቋቋም በጣም ይከብደኛል፤ ያም ቢሆን ይሖዋ ከጎኔ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። ስሜቴ ሲደቆስ ወይም ልሞት ነው የሚል ስጋት ሲያድርብኝ ሁልጊዜ እጸልያለሁ። ምንም ነገር ከይሖዋ ፍቅር ሊለየኝ አይችልም።​—ሮም 8:39

 ዛካሪ ይህን ቃለ መጠይቅ ካደረገ ከሁለት ወራት በኋላ በ18 ዓመቱ በሞት አንቀላፍቷል። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሙታን እንደሚነሱ ያለው ጠንካራ እምነት እስከ መጨረሻው ድረስ አልቀነሰም።

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ጸሎት ዛካሪን እንደረዳው ሁሉ አንተንም ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ እንድትኖር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

 አናዪስ

 ከተወለድኩ ከጥቂት ቀናት በኋላ አንጎሌ ውስጥ ደም በመፍሰሱ መላው ሰውነቴን የሚነካ ጉዳት ደረሰብኝ፤ በተለይ እግሮቼ በጣም ተጎዱ።

 አሁን፣ አጭር ርቀት ለመጓዝ የምመረኮዘው ነገር ያስፈልገኛል፤ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ግን ብዙውን ጊዜ ተሽከርካሪ ወንበር እጠቀማለሁ። በተጨማሪም ጡንቻዎቼ ድንገት ስለሚኮማተሩ እንደ መጻፍ ያሉ ትኩረት የሚጠይቁ ነገሮችን ማከናወን አልችልም።

 ያለሁበት ሁኔታ ከሚፈጥርብኝ ውጥረት በተጨማሪ የምወስደው ሕክምናም ከባድ ነው። ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ በሳምንት ለበርካታ ጊዜያት የፊዚዮቴራፒ ሕክምና እወስዳለሁ። በአምስት ዓመቴ የመጀመሪያውን ከባድ ቀዶ ጥገና ያደረግሁ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሦስት ጊዜ አድርጌያለሁ። የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ቀዶ ጥገናዎች በጣም ከባድ ነበሩ፤ ምክንያቱም እስካገግም ድረስ ለሦስት ወር ያህል ወደ ቤት አልተመለስኩም።

 ቤተሰቦቼ በጣም ረድተውኛል። ከእነሱ ጋር አብሬ መሳቄና መጫወቴ ስሜቴ እንዳይደቆስ ይረዳኛል። ያለሌሎች እገዛ ራሴን መንከባከብ ስለማልችል ልብሴን በማልበስ እና በሌሎች ነገሮች ረገድ እናቴና እህቶቼ ይተባበሩኛል። ታኮ ጫማ ማድረግ አለመቻሌ ያሳዝነኛል። በልጅነቴ ግን አንድ ቀን ታኮ ጫማ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፤ እጆቼን ጫማው ውስጥ አስገብቼ እየዳህኩ ስሄድ ሁላችንም በሳቅ ሞትን!

 ያለሁበት ሁኔታ እንዲቆጣጠረኝ አልፈቀድኩም። የተለያዩ ቋንቋዎችን እማራለሁ። በውኃ ወይም በበረዶ ላይ መንሸራተት ባልችልም በመዋኘት ይህን ለማካካስ እሞክራለሁ። የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን መስበክና እምነቴን ለሌሎች መግለጽ ያስደስተኛል። ሰዎች ሳነጋግራቸው በትኩረት ያዳምጡኛል።

 ወላጆቼ፣ አሁን ያለሁበት ሁኔታ ጊዜያዊ እንደሆነ ከልጅነቴ ጀምሮ አስተምረውኛል። ከትንሽነቴ አንስቶ፣ በይሖዋ እንዲሁም የእኔን ችግሮች ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት መከራ እንደሚያስወግድ በገባው ቃል ላይ እምነት አዳብሬያለሁ። ይህም ወደፊት እንድገፋ ብርታት ሆኖኛል።​—ራእይ 21:3, 4

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ አንተም እንደ አናዪስ፣ የጤና ችግር እንዲቆጣጠርህ እንዳልፈቀድክ ማሳየት የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

 ዡልያና

 ኦውቶኢምዩን ዲሶርደር የተባለ ከባድ የጤና እክል አለብኝ፤ ይህ እክል ልብን፣ ሳንባንና ደምን የሚያውክ ነው። በሽታው ኩላሊቶቼንም ጎድቷቸዋል።

 የአሥር ዓመት ልጅ እያለሁ ሉፐስ የተባለ በሽታ እንዳለብኝ ታወቀ፤ በሽታው በጣም የሚያሠቃየኝ ሲሆን ሰውነቴ ይዝላል፤ እንዲሁም ስሜቴ በድንገት ይለዋወጣል። አንዳንድ ጊዜ ምንም እንደማልጠቅም ይሰማኛል።

 በ13 ዓመቴ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታችን መጣች። ይህቺ ሴት ኢሳይያስ 41:10ን ያነበበችልኝ ሲሆን ጥቅሱ፣ ይሖዋ አምላክ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ . . . በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ” እንዳለ ይናገራል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመርኩት ያን ጊዜ ነው። ይህ ከሆነ ስምንት ዓመታት ያለፉ ሲሆን አሁንም አምላክን በሙሉ ልብ እያገለገልሁ ነው፤ በተጨማሪም ያለብኝ በሽታ እንዲቆጣጠረኝ ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ። ይሖዋ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ስለሰጠኝ አዎንታዊ መሆን ችያለሁ።​—2 ቆሮንቶስ 4:7

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ኢሳይያስ 41:10 ዡልያናን እንደረዳት ሁሉ አንተንም አዎንታዊ አመለካከት እንድትይዝ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?