በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከከባድ በሽታ ጋር መኖር—መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው እርዳታ አለ?

ከከባድ በሽታ ጋር መኖር—መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው እርዳታ አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ። አምላክ ለታመሙ አገልጋዮቹ ያስባል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ታሞ ባለበት ዐልጋ ላይ እግዚአብሔር ይንከባከበዋል።” (መዝሙር 41:3) ከከባድ በሽታ ጋር የምትኖር ከሆነ የሚከተሉት ሦስት ነጥቦች ሁኔታውን ለመቋቋም ሊረዱህ ይችላሉ፦

  1.   ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ለማግኘት ጸልይ። “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም” ጭንቀትህን ለመቀነስና ሁኔታውን ለመቋቋም ይረዳሃል።​—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

  2.   አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤ የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል” ይላል። (ምሳሌ 17:22) ሳቂታ ለመሆን ጥረት ማድረግህ ከሐዘን ስሜት እንድትወጣ ብቻ ሳይሆን ለጤናህም ይጠቅምሃል።

  3.   በወደፊት ተስፋዎችህ ላይ ያለህን እምነት አጠናክር። እውነተኛ ተስፋ ከባድ በሽታ ቢኖርብህም ደስተኛ እንድትሆን ይረዳሃል። (ሮም 12:12) መጽሐፍ ቅዱስ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል” ሰው የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 33:24) በዚያን ጊዜ አምላክ፣ ዘመናዊ ሳይንስ መፍትሔ ያላስገኘላቸው ሥር የሰደዱ በሽታዎችን በሙሉ ይፈውሳል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ተመልሰው ወጣት እንደሚሆኑ ሲናገር “በዚህ ጊዜ ሥጋው እንደ ሕፃን ልጅ ገላ ይታደሳል፤ ወደ ወጣትነቱም ዘመን ይመለሳል” ይላል።​—ኢዮብ 33:25

 ማሳሰቢያ፦ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ የሚሰጠውን እርዳታ ቢቀበሉም ከባድ በሽታ ሲያጋጥማቸው የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። (ማርቆስ 2:17) ያም ቢሆን አንድን የሕክምና ዓይነት ለይተን በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አናቀርብም፤ በዚህ ረገድ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ውሳኔ ማድረግ እንደሚኖርበት እናምናለን።