በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?

ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?

 ጊዜህን በአግባቡ መጠቀም ያለብህ ለምንድን ነው?

  •   ጊዜ እንደ ገንዘብ ነው። ካባከንከው በሚያስፈልግህ ጊዜ ልታጣው ትችላለህ። በአግባቡ ከተጠቀምክበት ደግሞ የሚያስደስቱህን ነገሮች ለማድረግ የሚያስችል ትርፍ ጊዜ ይኖርሃል!

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰነፍ ሰው ይመኛል፤ ነገር ግን ምንም አያገኝም፤ ትጉ ሰው ግን በሚገባ ይጠግባል።”—ምሳሌ 13:4

     ዋናው ነጥብ፦ ጊዜህን በአግባቡ መጠቀምህ ተጨማሪ ነፃነት ይሰጥሃል እንጂ ነፃነትህን አይገድብብህም።

  •   ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ ትልቅ ሰው ስትሆን የሚጠቅምህ አስፈላጊ ችሎታ ነው። ጊዜህን የምትጠቀምበት መንገድ ሥራህን ይዘህ እንድትቀጥል ወይም ከሥራ እንድትባረር ሊያደርግህ ይችላል። አንተም ብትሆን የራስህ ድርጅት ቢኖርህ በተደጋጋሚ አርፍዶ የሚመጣ ሠራተኛ እንዲኖርህ እንደማትፈልግ የታወቀ ነው።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ ሰው በብዙ ነገርም ታማኝ ነው።”—ሉቃስ 16:10

     ዋናው ነጥብ፦ ጊዜህን የምትጠቀምበት መንገድ ስለ ማንነትህ የሚናገረው ነገር አለ።

 እውነቱን ለመናገር ግን፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ቀላል አይደለም። እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን እስቲ እንመልከት።

 እንቅፋት #1፦ ጓደኞች

 “ጓደኞቼ አብረን እንድንዝናና ከጠየቁኝ፣ ጊዜ ባይኖረኝ እንኳ አብሬያቸው እሄዳለሁ። ‘ሥራዬን ቤት ስመለስ ቶሎ ቶሎ እሠራዋለሁ’ ብዬ አስባለሁ። ይህ ደግሞ የሚሳካው ሁልጊዜ አይደለም፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ችግር ውስጥ ገብቼ አውቃለሁ።”—ሲንቲያ

 እንቅፋት #2፦ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች

 “ቴሌቪዥን በጣም ፈታኝ ነገር ነው። አንዳንድ ፕሮግራሞችንና ፊልሞችን ላለማየት መወሰን በጣም ይከብዳል።”—አይቪ

 “ታብሌቴን በመጠቀም ብዙ ሰዓት ላባክን እችላለሁ። ባትሪው እስካላለቀ ድረስ ማቆም ያቅተኛል፤ በኋላ ግን ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል።”—ማሪ

 እንቅፋት #3፦ ዛሬ ነገ ማለት

 “የትምህርት ቤት ሥራዎቼንም ሆነ ሌሎች ማከናወን ያሉብኝን ነገሮች ለመሥራት ዛሬ ነገ የማለት ዝንባሌ አለኝ። ሥራውን መጨረስ ያለብኝ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ የማይረባ ነገር እየሠራሁ ጊዜዬን አባክናለሁ፤ ይህ በጣም መጥፎ የጊዜ አጠቃቀም ነው።”—ቤት

ጊዜህን በአግባቡ መጠቀምህ ተጨማሪ ነፃነት ይሰጥሃል እንጂ ነፃነትህን አይገድብብህም

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

  1.   ማከናወን ያለብህን ሥራዎች በዝርዝር ጻፍ። ለምሳሌ የቤት ውስጥ ሥራዎችህንና የትምህርት ቤት ሥራህን ልትጽፍ ትችላለህ። ከዚያም በአንድ ሳምንት ውስጥ እያንዳንዱን ሥራ ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንደሚያስፈልግህ ጻፍ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

  2.   በትርፍ ጊዜህ ማድረግ የምትፈልጋቸውን ነገሮች ዘርዝረህ ጻፍ። ይህ ደግሞ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን እንደመጠቀም ወይም ቴሌቪዥን እንደመመልከት ያሉትን ነገሮች ሊጨምር ይችላል። ከዚያም በአንድ ሳምንት ውስጥ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ነገር በማድረግ ምን ያህል ሰዓት እንደምታሳልፍ ጻፍ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ በመጠቀም . . . በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 4:5

  3.   ዕቅድ አውጣ። የጻፍካቸውን ሁለት ዝርዝሮች መለስ ብለህ ተመልከት። አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች በቂ ጊዜ መድበሃል? በትርፍ ጊዜህ ከምታከናውናቸው ነገሮች ጊዜ መቀነስ ያስፈልግህ ይሆን?

     ጠቃሚ ምክር፦ በቀኑ ውስጥ ልታከናውናቸው የምትፈልጋቸውን ነገሮች በየዕለቱ ዘርዝረህ ጻፍ፤ ከዚያም እያንዳንዱን ነገር ስትጨርስ ምልክት አድርግበት።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።”—ምሳሌ 21:5

  4.   በዕቅድህ ተመራ። አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለማከናወን ስትል አልፎ አልፎ፣ አንዳንድ ግብዣዎችን አለመቀበል ይኖርብህ ይሆናል። በጥቅሉ ሲታይ ግን በዕቅድህ ከተመራህ ተጨማሪ ትርፍ ጊዜ ማግኘትህ አይቀርም፤ ይህ ትርፍ ጊዜ ደግሞ ይበልጥ አስደሳች ይሆንልሃል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ታታሪዎች ሁኑ እንጂ አትስነፉ።”—ሮም 12:11

  5.   የሚያዝናናህን ነገር በማድረግ ለራስህ ሽልማት ስጥ፤ ሆኖም ይህን ለማድረግ አትቸኩል። ታራ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ፣ ለማከናወን ባቀድኳቸው ነገሮች ዝርዝር ውስጥ ያሉ ሁለት ነገሮችን እንደጨረስኩ ስመለከት ‘ለ15 ደቂቃ ቴሌቪዥን ካየሁ በኋላ ወደ ሥራዬ እመለሳለሁ’ ብዬ አስባለሁ። ከዚያ ግን 15 ደቂቃ፣ 30 ደቂቃ፣ አንድ ሰዓት እያለ ሳይታወቀኝ ቴሌቪዥን በማየት ሁለት ሰዓት አባክናለሁ!”

     ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? መዝናኛን የዕለታዊ እንቅስቃሴህ አንዱ ክፍል እንደሆነ አድርገህ ከማሰብ ይልቅ ሥራህን ስትጨርስ እንደምታገኘው ሽልማት አድርገህ ተመልከተው።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው . . . ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም።”—መክብብ 2:24