በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

አባቴ ወይም እናቴ ታማሚ ቢሆኑስ?

አባቴ ወይም እናቴ ታማሚ ቢሆኑስ?

 አብዛኞቹ ወጣቶች ወላጆቻቸውን የማስታመም ጉዳይ አያሳስባቸውም። ምክንያቱም ወላጆቻቸው የጤና እክል ሳይገጥማቸው ዓመታት ሊያልፉ ይችላሉ።

 ሆኖም ገና በልጅነትህ አባትህ ወይም እናትህ ቢታመሙስ? እንዲህ ዓይነት ችግር የገጠማቸውን ሁለት ወጣቶች ምሳሌ እንመልከት።

 የኤመላይን ታሪክ

 እናቴ መገጣጠሚያን፣ ቆዳንና የደም ቧንቧዎችን የሚጎዳ ኤለርስ-ዳንሎስ ሲንድረም (EDS) የሚባል ከባድና ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል ሕመም አለባት።

 በሽታው መድኃኒት የለውም፤ እናቴ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ሕመሙ እየባሰባት መጥቷል። እንዲያውም የደም ሴሎቿ መጠን በጣም ከማነሱ የተነሳ ሕይወቷ አደጋ ላይ የወደቀባቸው እንዲሁም ሥቃይዋ እጅግ ከመክበዱ የተነሳ ሞትን የተመኘችባቸው ጊዜያት ነበሩ።

 እኔና ቤተሰቦቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስንሆን የጉባኤያችን አባላት ሁላችንንም በጣም ያበረታቱናል! ለምሳሌ፣ እኩያዬ የሆነች አንዲት ልጅ በቅርቡ ለቤተሰባችን ካርድ ላከችልን፤ ምን ያህል እንደምትወደንና መቼም ቢሆን ከጎናችን እንደምትሆን በካርዱ ላይ ገለጻ ነበር። እንዲህ ዓይነት ጓደኛ ማግኘት እንዴት ደስ ይላል!

 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤም በጣም ረድቶኛል። ከምወዳቸው ጥቅሶች አንዱ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው” የሚለው በመዝሙር 34:18 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ነው። ሌላው የምወደው ጥቅስ ደግሞ ዕብራውያን 13:6 ሲሆን ጥቅሱ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም” ይላል።

 በተለይ ዕብራውያን 13:6 ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው። ከምንም በላይ የምፈራው ነገር እናቴን በሞት ማጣት ነው። እናቴን በጣም እወዳታለሁ፤ በየቀኑ ከእሷ ጋር የማሳልፈው ቀን በማግኘቴም አመስጋኝ ነኝ። ይህ ጥቅስ፣ ወደፊት የሚያጋጥመኝን ማንኛውንም ነገር ልቋቋመው እንደምችል እንድተማመን ያደርገኛል።

 ሆኖም የሚያስፈራኝ ሌላም ነገር አለ። EDS በዘር የሚተላለፍ በሽታ ነው። እናቴ በሽታው የተላለፈባት ከእናቷ ሲሆን ከእሷ ደግሞ ወደ እኔ ተላልፏል። በመሆኑም እኔም EDS አለብኝ። ሆኖም ዕብራውያን 13:6 ይሖዋ በዚህም ረገድ “ረዳቴ” እንደሚሆን ያረጋግጥልኛል።

 ስላለፈው ጊዜ ከማሰብ ወይም ስለ ወደፊቱ ከመጨነቅ ይልቅ አሁን ያለኝን ነገር ለማድነቅ እሞክራለሁ። እናቴ ከዚህ ቀደም ምን ማድረግ ትችል እንደነበረና አሁን አቅሟ ምን ያህል እንደተገደበ የማነጻጽር ከሆነ በሐዘን እዋጣለሁ ። መጽሐፍ ቅዱስ አሁን የሚያጋጥሙን ፈተናዎች፣ ወደፊት በሽታ በሌለበት ዓለም ውስጥ ከምናገኘው የዘላለም ሕይወት ጋር ሲወዳደሩ “ጊዜያዊና ቀላል” እንደሆኑ ይናገራል።—2 ቆሮንቶስ 4:17፤ ራእይ 21:1-4

 ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ኤመላይን አዎንታዊ አመለካከት ይዛ እንድትቀጥል የረዳት ምንድን ነው? አንተስ ተፈታታኝ ችግሮች ሲያጋጥሙህ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ የምትችለው እንዴት ነው?

 የኤመሊ ታሪክ

 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ አባቴ በመንፈስ ጭንቀት መሠቃየት ጀመረ። ቀድሞ የማውቀው አባቴ በአዲስ ሰው የተተካ ያህል ተሰምቶኝ ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ አባቴ በከባድ ሐዘን፣ መሠረተ ቢስ በሆነ ፍርሃት እንዲሁም ከልክ ባለፈ ጭንቀት ይዋጣል። ይህ ችግር ከጀመረው አሁን 15 ዓመት አልፎታል። በሐዘን ስሜት እንዲዋጥ የሚያደርገው ምንም ምክንያት እንደሌለ እያወቀም እንዲህ ያለው ስሜት ሲያሸንፈው ምን ያህል እንደሚጨንቀው መገመት ይቻላል!

 እኔና አባቴ የይሖዋ ምሥክሮች ስንሆን የጉባኤያችን አባላት ይህ ነው የማይባል ድጋፍ ይሰጡናል። የእምነት አጋሮቻችን ደጎችና የሰው ችግር የሚገባቸው ናቸው፤ አንዳቸውም ቢሆኑ አባቴን ለጉባኤው እንደማይጠቅም እንዲሰማው አድርገውት አያውቁም። አባቴ የገጠመውን ከባድ ችግር በጽናት ሲቋቋም ማየቴ ከመቼውም ይበልጥ እንድወደው አድርጎኛል።

 እርግጥ፣ በከባድ ጭንቀት የማይዋጠውና በሕመም የማይሠቃየው እንዲሁም ደስተኛ የነበረው የድሮ አባቴ ይናፍቀኛል። አሁን አባቴ በአእምሮው ውስጥ ካለ የማይታይ ጠላት ጋር በየቀኑ ስለሚታገል በጣም ያሳዝነኛል።

 ያም ሆኖ አባቴ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ለምሳሌ፣ በቅርቡ የመንፈስ ጭንቀቱ ብሶበት በነበረበት ወቅት፣በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጥረት ያደርግ ነበር። የሚያነበው ጥቂት ቁጥሮችን ብቻ ቢሆንም ይህ ትልቅ ብርታት ሰጥቶታል። እንዲህ ያለው ከቁጥር የማይገባ የሚመስል ልማድ እንኳ በሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። በዚያ ከባድ ወቅት አባቴ የወሰደው እርምጃ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንድኮራበት አድርጎኛል።

 ‘የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ ነው’ የሚለውን በነህምያ 8:10 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ከልቤ እወደዋለሁ። ይህ ሐሳብ በእርግጥም ትክክል ነው። ጉባኤ ውስጥ ስሆንና ሙሉ በሙሉ ተሳትፎ ሳደርግ የሚሰማኝ ደስታ፣ በውስጤ የሚፈጠረውን የባዶነት ስሜት ለማሸነፍ ይረዳኛል። ቀኑን ሙሉ ደስ ብሎኝ አሳልፋለሁ። የአባቴ ምሳሌ፣ የሚያጋጥመን ችግር ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን ሆኖ እንደሚደግፈን አስተምሮኛል።

 ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ኤመሊ አባቷ በታመመበት ወቅት የደገፈችው እንዴት ነው? በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃይን ሰው መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?