በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅመኝ የሚችለው እንዴት ነው?—ክፍል 1፦ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር

መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅመኝ የሚችለው እንዴት ነው?—ክፍል 1፦ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር

 “መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ እንደማልጨርሰው ተሰማኝ!”—ብሪያና

 አንተም ልክ እንደ ብሪያና ይሰማሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ይረዳሃል!

 መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ምን ጥቅም አለው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ አሰልቺ እንደሆነ ይሰማሃል? ከሆነ ይህ የሚያስገርም አይደለም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው በደቃቅ ፊደላት የተጻፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ገጾች ያሉትና አንድም ሥዕል የሌለው መጽሐፍ ሊሆን ይችላል፤ ቴሌቪዥን ወይም ቪድዮ የመመልከትን ያህልም አያስደስትህ ይሆናል።

 ሆኖም ሁኔታውን በዚህ መንገድ ለማሰብ ሞክር፦ ውድ በሆኑ ጌጣ ጌጦች የተሞላ አንድ ጥንታዊ ሣጥን ብታገኝ ውስጡ ያለውን ለማየት አትጓጓም?

 መጽሐፍ ቅዱስም ውድ በሆኑ ጌጣ ጌጦች እንደተሞላ ሣጥን ነው። የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ የሚረዳ ጥበብ በውስጡ ይዟል፦

  •   ጥሩ ውሳኔዎች ለማድረግ

  •   ከወላጆችህ ጋር ተስማምተህ ለመኖር

  •   ጥሩ ጓደኞች ለማፍራት

  •   የሚያጋጥምህን ጭንቀት ለመቋቋም

 ይሁንና እንዲህ ያለው ጥንታዊ መጽሐፍ በዚህ ዘመንም ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ” ስለሆኑ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምክር የመጣው ከሁሉም ከሚበልጠው አካል ነው ማለት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በውድ ነገሮችን ከተሞላ ሣጥን ጋር ይመሳሰላል፤ በውስጡ በዋጋ የማይተመን ጥበብ ይገኛል

 መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የትኞቹን ዘዴዎች መጠቀም ትችላለህ?

 አንዱ መንገድ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ ነው። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ይዘት ለመረዳት ያስችልሃል። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ትችላለህ። እስቲ የሚከተሉትን ሁለት አማራጮች ተመልከት፦

  •    በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን 66 መጻሕፍት በቅደም ተከተል ማለትም ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ማንበብ ትችላለህ።

  •    በመጽሐፉ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ታሪኮች በተፈጸሙበት ቅደም ተከተል ማንበብም ትችላለህ።

 ጠቃሚ ምክር፦ በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘው ተጨማሪ መረጃ ሀ7 የኢየሱስን ምድራዊ ሕይወት አበይት ክንውኖች በጊዜ ቅደም ተከተል ለማወቅ ይረዳሃል።

 ሁለተኛው መንገድ፣ በሕይወትህ ውስጥ ስለሚያሳስብህ ጉዳይ የሚናገር ዘገባ ማንበብ ነው። ለምሳሌ ያህል፦

 ጠቃሚ ምክር፦ መጽሐፍ ቅዱስን ትኩረትህ ሳይከፋፈል ማንበብ እንድትችል ጸጥ ያለ አካባቢ ምረጥ።

 ሦስተኛው መንገድ ደግሞ አንድ ዘገባ ወይም መዝሙር ማንበብ ነው፤ ከዚያም ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ እንደምታደርግ አስብ። በምታነብበት ጊዜ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦

  •    ይሖዋ ይህ ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ለምንድን ነው?

  •    ስለ ይሖዋ ባሕርይ ወይም ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ምን ይገልጻል?

  •    በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ላደርጋቸው የምችላቸው ምን ትምህርቶችን ይዟል?

 ጠቃሚ ምክር፦ ግብ አውጣ! የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራምህን የምትጀምርበትን ቀን ጻፍ።