በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ቃለ ምልልስ | ጊየርሞ ፔሬዝ

የቀዶ ጥገና ሐኪም ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

የቀዶ ጥገና ሐኪም ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

ዶክተር ጊየርሞ ፔሬዝ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኝ 700 አልጋ ባለው አንድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ በኃላፊነት ሲሠራ ቆይቶ አሁን በጡረታ ላይ ይገኛል። ለበርካታ ዓመታት በዝግመተ ለውጥ ያምን ነበር። በኋላ ግን የሰውን አካል ንድፍ ያወጣው አምላክ እንደሆነ አምኗል። ንቁ! ስለ እምነቱ አነጋግሮታል።

በአንድ ወቅት በዝግመተ ለውጥ ታምን የነበረው ለምን እንደሆነ ልትነግረን ትችላለህ?

ያደግኩት በካቶሊክ እምነት ውስጥ ቢሆንም ስለ አምላክ ጥርጣሬ ነበረኝ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ያቃጥላል የሚለውን ሐሳብ ማመን ይከብደኝ ነበር። ስለሆነም የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎቼ፣ ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ እንጂ በፍጥረት እንዳልሆነ ሲያስተምሩኝ ይህ አመለካከት በማስረጃ የተደገፈ መሆን አለበት ብዬ በማመን ተቀበልኩት። በነገራችን ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱም ብትሆን ዝግመተ ለውጥን አትቃወምም፤ ነገር ግን ሂደቱን የሚመራው አምላክ እንደሆነ ታስተምራለች።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ልታዳብር የቻልከው እንዴት ነው?

ባለቤቴ ሱዛን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር፤ እነሱም አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት እንደማያሠቃይ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩአት። * በተጨማሪም አምላክ ምድራችንን ገነት ለማድረግ ቃል መግባቱን ነገሯት። * በስተ መጨረሻ ትርጉም የሚሰጡ ትምህርቶችን አገኘን! በ1989 ኒክ የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ይጠይቀኝ ጀመረ። ስለ ሰው አካልና ስለ አመጣጡ በምንነጋገርበት ጊዜ ያሳየኝ በዕብራውያን 3:4 ላይ የሚገኘው “እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው” የሚለው ቀላልና አሳማኝ እውነታ በጣም አስደነቀኝ።

በሰው አካል ላይ ያደረግከው ጥናት ሕይወት በፍጥረት መገኘቱን እንድታምን ረድቶሃል?

አዎ። ለምሳሌ ሰውነታችን ራሱን በራሱ የሚጠግንበት መንገድ ታስቦበት እንደተሠራ በግልጽ ያሳያል። ቁስል የሚድንበትን ሂደት እንደ ምሳሌ ብንወስድ ይህ ሂደት አራት ተከታታይ ደረጃዎች አሉት፤ እኔም የቀዶ ጥገና ሐኪም እንደመሆኔ መጠን ሥራዬን የማከናውነው ሰውነት ራሱን በራሱ በሚጠግንበት መንገድ ላይ ተመሥርቼ ነው።

እስቲ አካላችን ሲቆስል ምን እንደሚሆን ንገረን።

በዚህ ወቅት የሚፈሰው ደም እንዲቆም የሚያደርጉ ተከታታይ ሂደቶች በጥቂት ሰኮንዶች ውስጥ ይጀምራሉ፤ ይህ የመጀመሪያው ደረጃ ነው። እነዚህ ሂደቶች እጅግ የተወሳሰቡ ከመሆናቸውም በላይ ውጤታማ ናቸው። በተጨማሪም በድምሩ  100,000 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ርዝመት ያላቸውን የደም ቧንቧዎች የሚያካትተው የደም ዝውውር ሥርዓት ራሱን መጠገንና ማንኛውንም ፍሳሽ መዝጋት የሚችል መሆኑ የቧንቧ ሥራ መሐንዲሶችን በጣም የሚያስገርም እንደሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ።

በሁለተኛው የጥገና ደረጃስ ምን ይከናወናል?

በሰዓታት ጊዜ ውስጥ የደሙ መፍሰስ ይቆምና ጉዳት የደረሰበት የአካል ክፍል መቆጣት ይጀምራል። በዚህ ወቅት አስደናቂ የሆኑ ተከታታይ ክንውኖች ይካሄዳሉ። በመጀመሪያ የደም መፍሰስን ለመቀነስ ሲባል ተኮማትረው የነበሩት የደም ቧንቧዎች አሁን እየሰፉ ይሄዳሉ። ይህ መሆኑ በቆሰለው አካባቢ ያለውን የደም ፍሰት ለመጨመር ያስችላል። በመቀጠል በፕሮቲን የበለጸገ ፈሳሽ ጉዳት የደረሰበት አካባቢ እንዲያብጥ ያደርጋል። ይህ ፈሳሽ ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር በማድረግ፣ መርዛማ ነገሮችን በማርከስና ጉዳት የደረሰባቸውን ሕብረ ሕዋሳት በማስወገድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ ያከናውናል። እነዚህ ተከታታይ ክንውኖች እንዲካሄዱ ደግሞ ለዚሁ ዓላማ የሚውሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሞለኪውሎችንና ሴሎችን ማምረት ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ ከእነዚህ ክንውኖች አንዳንዶቹ ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ቀጣዩን ሂደት ያስጀምራሉ።

ቀጣዩ ሂደት ምንድን ነው?

በጥቂት ቀናት ውስጥ ሰውነታችን ለጥገና የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማምረት ይጀምራል፤ ይህም ሦስተኛው ሂደት መጀመሩን የሚጠቁም ሲሆን በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሥራው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ቁስሉን የሚሸፍን እንደ አሰር ያለ ነገር የሚሠሩ ሴሎች ጉዳት ወደደረሰበት አካባቢ ሄደው መባዛት ይጀምራሉ። በተጨማሪም ትናንሽ የደም ሴሎች በማቆጥቆጥ ጉዳት ወደደረሰበት አካባቢ ያድጋሉ፤ ከዚያም በማፍረሱና በመጠገኑ ሥራ የሚፈጠረውን ቆሻሻ ያስወግዳሉ እንዲሁም ምግብ ያጓጉዛሉ። በሌላ ውስብስብ ሂደት አማካኝነት ደግሞ ቁስሉ እንዲገጥም የሚያደርጉ ልዩ ተግባር ያላቸው ሴሎች ይባዛሉ።

በጣም ብዙ ሥራ ነው! ጥገናው በምን ያህል ጊዜ ያልቃል?

የመጨረሻ ደረጃ የሆነው መልክ የማስያዙ ሥራ ወራት ሊፈጅ ይችላል። የተሰበሩ አጥንቶች ቀድሞ ወደነበራቸው ጥንካሬ ይመለሳሉ፤ ለስላሳ በሆኑ የሰውነት ክፍሎች ላይ ያለውን ቁስል ሸፍኖት የነበረው አሰር ደግሞ በጠንካራ ሕዋሳት ይተካል። በአጠቃላይ ሲታይ ቁስል የሚድንበት ሂደት በሚገርም መንገድ እርስ በርስ የተቀናጀ ነው።

በሥራ ላይ ያጋጠመህ አንተን በጣም ያስደነቀህ ነገር አለ?

የሰው አካል እንዴት ራሱን በራሱ እንደሚጠግን ስመለከት በጣም እደነቃለሁ

አዎ። አስታውሳለሁ በአንድ ወቅት፣ በጣም ከባድ የመኪና አደጋ የደረሰባት አንዲት የ16 ዓመት ልጅ አክሜ ነበር። ልጅቷ ቆሽቷ ስለተቀደደና በሰውነቷ ውስጥ ደም ይፈስሳት ስለነበረ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነበረች። ከዓመታት በፊት ቢሆን ኖሮ ቀዶ ሕክምና በማድረግ ቆሽቷን ለመጠገን ወይም ለማውጣት እንሞክር ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ሐኪሞች ይበልጥ የሚታመኑት ሰውነታችን ባለው ራሱን በራሱ የመጠገን ችሎታ ላይ ነው። ያደረግኩላት ሕክምና ቢኖር ኢንፌክሽኑን ማዳን፣ ያጣችውን ፈሳሽ መተካት፣ ደም እንዳያንሳት ማድረግና የሥቃይ ማስታገሻ መስጠት ብቻ ነበር። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በተደረገላት ምርመራ ቆሽቷ ሙሉ በሙሉ እንደዳነ ተረጋገጠ! የሰው አካል እንዴት ራሱን በራሱ እንደሚጠግን ስመለከት በጣም እደነቃለሁ። ይህ ደግሞ የሰውነታችንን ንድፍ ያወጣው አምላክ እንደሆነ ያለኝን እምነት ያጠናክረዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ትኩረትህን የሳቡት ለምንድን ነው?

ወዳጃዊ መንፈስ እንዳላቸውና ሁልጊዜ ለጥያቄዎቼ መልስ የሚሰጡኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ አስተዋልኩ። በተጨማሪም እምነታቸውን በድፍረት የሚገልጹ መሆናቸውና ሰዎችን ስለ አምላክ ለማስተማር የሚያደርጉት ጥረት አስደነቀኝ።

የይሖዋ ምሥክር መሆንህ በሥራህ ረገድ ጠቅሞሃል?

አዎ። አንደኛ ነገር፣ ሐኪሞችም ሆኑ ነርሶች የታመሙና አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች በብዛት በመመልከታቸው ሳቢያ የሚመጣውን የመሰላቸት ስሜት እንድቋቋም ረድቶኛል። በተጨማሪም በሽተኞች ማውራት በሚፈልጉበት ጊዜ፣ ፈጣሪያችን በሽታንና ሥቃይን እንደሚያስወግድ * እንዲሁም ማንም “ታምሜአለሁ” * የማይልበት ዓለም እንደሚያመጣ የሰጠንን ተስፋ እገልጽላቸዋለሁ።