ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 3:1-19

  • ኢየሱስ ከሙሴ ይበልጣል (1-6)

    • ‘ሁሉን ነገር የሠራው አምላክ ነው’ (4)

  • ‘እምነት የለሽ ልብ በውስጣችሁ እንዳያቆጠቁጥ ተጠንቀቁ’ (7-19)

    • “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ” (7, 15)

3  ስለሆነም የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች+ የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች፣ በእሱ እንደምናምን በይፋ የምንናገርለትን፣ ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ።+  ሙሴ በመላው የአምላክ ቤት ላይ ታማኝ እንደነበረ ሁሉ+ እሱም ለሾመው ታማኝ ነበር።+  ቤቱን የሠራው፣ ከቤቱ የበለጠ ክብር ስላለው እሱ* ከሙሴ የበለጠ ክብር ይገባዋል።+  እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው።  ሙሴም በመላው የአምላክ ቤት ላይ ታማኝ አገልጋይ ነበር። አገልግሎቱም ከጊዜ በኋላ ለሚነገሩ ነገሮች ምሥክር ነው።  ክርስቶስ ግን በአምላክ ቤት ላይ የተሾመ ታማኝ ልጅ ነበር።+ እኛም አፋችንን ሞልተን የመናገር ነፃነታችንንና የምንደሰትበትን ተስፋችንን እስከ መጨረሻው አጥብቀን ከያዝን የአምላክ ቤት ነን።+  ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦+ “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ  በምድረ በዳ እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት በተፈጸመበት በፈተና ቀን እንደሆነው ልባችሁን አታደንድኑ፤+  በዚያ፣ አባቶቻችሁ ያደረግኩትን ሁሉ ለ40 ዓመት ቢያዩም እኔን በመፈተን ተገዳደሩኝ።+ 10  በዚህም ምክንያት በዚያ ትውልድ በጣም ተንገሸገሽኩ፤ እንዲህም አልኩ፦ ‘ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፤ መንገዴንም ሊያውቁ አልቻሉም።’ 11  በመሆኑም ‘ወደ እረፍቴ አይገቡም’ ብዬ በቁጣዬ ማልኩ።”+ 12  ወንድሞች፣ ሕያው ከሆነው አምላክ በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ ከእናንተ መካከል በማናችሁም ውስጥ እንዳያቆጠቁጥ ተጠንቀቁ፤+ 13  ከዚህ ይልቅ ከእናንተ መካከል አንዳችሁም ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል እንዳትደነድኑ “ዛሬ”+ ተብሎ የሚጠራ ጊዜ እስካለ ድረስ በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ። 14  የክርስቶስ ተካፋዮች የምንሆነው* በመጀመሪያ የነበረንን ትምክህት እስከ መጨረሻው አጽንተን ከያዝን ብቻ ነውና።+ 15  ይህም “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ እንደሆነው ልባችሁን አታደንድኑ” እንደተባለው ነው።+ 16  ድምፁን ቢሰሙም እንኳ እጅግ ያስቆጡት እነማን ነበሩ? ይህን ያደረጉት ሙሴ እየመራቸው ከግብፅ የወጡት ሁሉ አይደሉም?+ 17  ከዚህም ሌላ ለ40 ዓመት አምላክ በእነሱ እንዲንገሸገሽ ያደረጉት እነማን ናቸው?+ እነዚያ ኃጢአት የሠሩትና ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረው አይደሉም?+ 18  ደግሞስ ወደ እረፍቴ አይገቡም ብሎ የማለው ስለ እነማን ነው? እነዚያን ያልታዘዙትን በተመለከተ አይደለም? 19  ስለዚህ ሊገቡ ያልቻሉት እምነት በማጣታቸው የተነሳ እንደሆነ እንረዳለን።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ኢየሱስን ያመለክታል።
ወይም “ከክርስቶስ ጋር አብረን የምንካፈለው።”