በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ አለመኖሩን ሳይንስ አረጋግጧል?

አምላክ አለመኖሩን ሳይንስ አረጋግጧል?

አምላክ አለመኖሩን ሳይንስ አረጋግጧል?

ንተኒ ፍሉ የተባሉት ብሪታንያዊ ፈላስፋ አምላክ የለሽነትን በማራመድ በባልደረቦቻቸው ዘንድ የታወቁ ሲሆኑ ለ50 ዓመታት ያህል ይህን አመለካከታቸውን ይዘው ቆይተዋል። “መንፈሳዊ ትምህርትና ማታለያው” በሚል ርዕስ በ1950 ያሳተሙት ጽሑፍ በ20ኛው መቶ ዘመን “በስፋት በመታተም ረገድ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የፍልስፍና ጽሑፍ ለመሆን በቅቷል።” ፍሉ “በወቅቱ ከነበሩት በአምላክ ወይም በአማልክት ማመንን ከተቹ ሐያሲያን ሁሉ ጥልቅ እውቀት ያላቸው” እንደሆኑ በ1986 ተገልጾ ነበር። በመሆኑም ፍሉ አመለካከታቸውን እንደለወጡ በ2004 ሲገልጹ ጉዳዩ ለብዙዎች አስደንጋጭ ሆነባቸው።

ፍሉ አመለካከታቸውን እንዲለውጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው? በአጭሩ ሳይንስ ነው። እኚህ ሰው የተመለከቷቸው ማስረጃዎች አጽናፈ ዓለም፣ የተፈጥሮ ሕግጋትና ሕይወት እንዲሁ በአጋጣሚ ሊገኙ እንደማይችሉ እንዲያምኑ አደረጓቸው። አንተስ ይህ መደምደሚያ ምክንያታዊ ይመስልሃል?

የተፈጥሮ ሕግጋት ከየት መጡ?

የፊዚክስ ሊቅና ደራሲ የሆኑት ፖል ዴቪስ፣ ሳይንስ እንደ ዝናብ ስለመሳሰሉት ተፈጥሯዊ ክስተቶች ማብራሪያ በመስጠት ረገድ ጥሩ ድርሻ እንዳበረከተ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “‘የተፈጥሮ ሕግጋት የኖሩት ለምንድን ነው?’ እንደሚሉት ላሉ . . . ጥያቄዎች [ሳይንስ] ግልጽ የሆነ መልስ የለውም። ሳይንሳዊ ግኝቶች እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ አላስገኙም፤ ሥልጣኔ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ አሁንም ድረስ አብዛኞቹ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ያላገኙ ሲሆን እነዚህ ጥያቄዎች ዛሬም ግራ ያጋቡናል።”

“ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር በተፈጥሮ ውስጥ ሥርዓት መኖሩ ብቻ አይደለም” በማለት ፍሉ በ2007 ጽፈዋል። “እነዚህ ሥርዓቶች ከሒሳብ ስሌት አንጻር ዝንፍ የማይሉ፣ ምንጊዜም ትክክል የሆኑና ‘እርስ በርስ የተሳሰሩ’ መሆናቸውም ትኩረት የሚስብ ነው። አንስታይን እነዚህ ሥርዓቶች የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ለመኖሩ ማስረጃ እንደሆኑ ተናግሯል። ልናነሳው የሚገባው ጥያቄ ‘ተፈጥሮ በዚህ መልክ እንዴት ሊቀመጥ ቻለ?’ የሚል ነው። ይህ ኒውተንን፣ አንስታይንንና ሃይዘንበርግን ጨምሮ በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት ያነሱት ጥያቄ ሲሆን መልሳቸውም ‘የአምላክ አእምሮ ያስገኘው ስለሆነ ነው’ የሚል ነው።”

በእርግጥም ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት አጽናፈ ዓለምን፣ የተፈጥሮ ሕግጋትንና ሕይወትን ያስገኘ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ ማመን ከሳይንስ ጋር እንደማይጋጭ ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ነገሮች እንዲሁ በአጋጣሚ ተገኙ ብሎ መናገር አእምሯችን ሊቀበለው የማይችል ነገር ነው። በየዕለቱ የምናያቸው ነገሮች፣ ንድፍ በተለይ ደግሞ እጅግ የተራቀቀ ንድፍ አለንድፍ አውጪ ሊገኝ እንደማይችል ይጠቁማሉ።

የትኛውን እምነት ትመርጣለህ?

አዲስ ዓይነት አምላክ የለሽነትን የሚያስፋፉት ሰዎች አመለካከታቸው በዋነኝነት በሳይንስ ላይ እንደተመሠረተ ቢለፍፉም ሐቁ ግን አምላክ የለሽነትም ሆነ በአምላክ ማመን ሙሉ በሙሉ በሳይንስ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም። ሁለቱም አመለካከቶች እምነት ይጠይቃሉ፦ አምላክ የለሽነትን የሚያራምዱ ሰዎች፣ ሁሉም ነገሮች የተገኙት እንዲሁ በአጋጣሚ እንደሆነ ሲያምኑ አምላክ አለ የሚሉት ደግሞ እነዚህን ነገሮች ወደ ሕልውና ያመጣ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ ያምናሉ። አዲሶቹ አምላክ የለሾች “ሃይማኖታዊ እምነቶች በሙሉ ጭፍን እምነት ናቸው” የሚለውን አመለካከት እንደሚያስፋፉ እንግሊዝ በሚገኘው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሒሳብ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ሌኖክስ ጽፈዋል። አክለውም ይህ አመለካከታቸው “የተሳሳተ መሆኑን ጠበቅ አድርገን መግለጽ ያስፈልገናል” ብለዋል። እንግዲያው አሁን የሚነሳው ጥያቄ፦ ትክክለኛነቱ በማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችለው እምነት የትኛው ነው? የአምላክ የለሾቹ ወይስ የሃይማኖተኞቹ? የሚል ነው። እስቲ የሕይወትን አመጣጥ እንደ ምሳሌ እንመልከት።

የዝግመተ ለውጥ አማኞች የሕይወት አመጣጥ ሊፈታ ያልቻለ እንቆቅልሽ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ያም ቢሆን እርስ በርስ የሚጋጩ ብዙ ጽንሰ ሐሳቦች አሏቸው። በአምላክ መኖር የማያምኑት ሪቻርድ ዶከንዝ የተባሉ ታዋቂ ግለሰብ፣ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ በጣም ብዙ ፕላኔቶች ከመኖራቸው አንጻር በሆነ ቦታ ሕይወት መገኘቱ እንደማይቀር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እምነት የሚጣልባቸው በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት ስለዚህ ጉዳይ ያን ያህል እርግጠኞች አይደሉም። የካምብሪጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ባሮ “ሕይወትና አእምሮ በዝግመተ ለውጥ እንደመጣ” ማመን “በምንም መልኩ እንደማያስኬድ” ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ውስብስብ በሆነና ለሕይወት በማይመች አካባቢ ሕይወት በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ሊገኝ እንዳይችል የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ በመሆኑም በቂ መጠን ያለው ካርቦን በቂ ጊዜ ከተሰጠው፣ ሊከሰት የማይችል ምንም ነገር የለም ብሎ ማሰብ እብሪት ይሆናል።”

በተጨማሪም ሕይወት እንዲሁ የኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች ውሕድ እንዳልሆነ ማስታወስ አለብን። ከዚህ ይልቅ ሕይወት በዲ ኤን ኤ ውስጥ በተቀመጠ እጅግ ውስብስብ የሆነ መረጃ ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም ስለ ሕይወት አመጣጥ ስንናገር ስለ ባዮሎጂያዊ መረጃ አመጣጥም ጭምር መናገራችን ነው። እስከ አሁን ከምናውቀው አንጻር መረጃ ሊገኝ የሚችልበት ብቸኛ ምንጭ ምንድን ነው? በአጭር አነጋገር አእምሮ ነው። እንደ ኮምፒውተር ፕሮግራም፣ የሒሳብ ቀመር፣ ኢንሳይክሎፒዲያ ያሉ ውስብስብ መረጃዎች ሌላው ቀርቶ የኬክ አዘገጃጀት መመሪያ እንኳ እንዲያው በአጋጣሚ ሊገኝ ይችላል? ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው። ሆኖም በውስብስብነታቸውና በውጤታማነታቸው ከእነዚህ ነገሮች አንዳቸውም ቢሆኑ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ከተቀመጠው ጄኔቲካዊ መረጃ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም።

ሁሉም ነገር በአጋጣሚ ተገኘ ብሎ መናገር በሳይንሱ መስክ ተቀባይነት አለው?

አምላክ የለሾች “አጽናፈ ዓለም እንዴት እንደመጣ ባይታወቅም እንዲሁ ተገኝቷል፤ ለሕይወት የሚመች የሆነውም በአጋጣሚ ነው” ብለው እንደሚያምኑ ፖል ዴቪስ ተናግረዋል። አክለውም አምላክ የለሾች እንደሚከተለው ብለው እንደሚናገሩ ገልጸዋል፦ “ሁኔታዎች ከዚህ የተለዩ ቢሆኑ ኖሮ እኛም በሕይወት ተገኝተን ስለዚህ ጉዳይ አንከራከርም ነበር። አጽናፈ ዓለምም ሆነ በውስጡ ያሉት ነገሮች እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ። ሆኖም አጽናፈ ዓለም ምንም ዓይነት ንድፍም ሆነ ዓላማ ወይም ትርጉም የለውም፤ ቢያንስ ለእኛ ስሜት የሚሰጥ ቁም ነገር የለውም።” ፖል ዴቪስ እንዲህ ብለዋል፦ “እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት መደገፍ ቀላል ነው፤ እንዲያውም [ከአወዛጋቢው ጉዳይ] ለማምለጥ ቀዳዳ ይከፍታል።”

ሞለኪውላር ባዮሎጂስት የሆኑት ማይክል ዴንተን ዝግመተ ለውጥ፣ አስጊ ሁኔታ ላይ የወደቀ ጽንሰ ሐሳብ (እንግሊዝኛ) በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት ዝግመተ ለውጥ “በቁም ነገር ከሚታይ . . . ሳይንሳዊ ጽንሰ ሐሳብ ይልቅ ከመካከለኛው ዘመን ኮከብ ቆጠራ ጋር የሚመሳሰል” ጽንሰ ሐሳብ ነው ወደሚል ድምዳሜ ደርሰዋል። በተጨማሪም እኚሁ ሰው፣ ዳርዊን ያመነጨው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የዘመናችን ታላቁ ተረት እንደሆነ ተናግረዋል።

በእርግጥም ሁሉም ነገር በአጋጣሚ ተገኘ ብሎ መናገር እንደ ተረት የሚቆጠር ነገር ነው። እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት፦ አንድ የአርኪኦሎጂ ባለሙያ ከሞላ ጎደል አራት ማዕዘን የሆነ ድንጋይ አገኘ እንበል። ይህ ባለሙያ ድንጋዩ እንዲህ ዓይነት ቅርጽ የኖረው በአጋጣሚ ነው ብሎ ቢናገር ምክንያታዊ ይሆናል። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ከወገብ በላይ ያለውን የሰው አካል የሚያሳይ በረቀቀ መንገድ የተሠራ አንድ የድንጋይ ቅርጽ አገኘ። ይኼኛውም ድንጋይ እንዲህ ዓይነት ቅርጽ ሊኖረው የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ ነው ይላል? በፍጹም። ‘አንድ ሰው ሠርቶታል’ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስም “በእርግጥ እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው” ይላል። (ዕብራውያን 3:4) አንተስ በዚህ አባባል ትስማማለህ?

ፕሮፌሰር ሌኖክስ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፦ “ስላለንበት አጽናፈ ዓለም ይበልጥ ባወቅን መጠን ‘እዚህ ምድር ላይ የተገኘነው ለምንድን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ የተሻለ ማብራሪያ የሚሰጠው፣ ጽንፈ ዓለምን በዓላማ የሠራ አንድ ፈጣሪ አምላክ አለ የሚለው መላ ምት መሆኑ ይበልጥ ተአማኒነት ያገኛል።”

የሚያሳዝነው፣ ሰዎች በአምላክ መኖር እንዳያምኑ እንቅፋት ከሚሆኑባቸው ነገሮች መካከል በስሙ የሚፈጸሙ የክፋት ድርጊቶች ይገኙበታል። በዚህም የተነሳ አንዳንዶች ሃይማኖት ባይኖር የሰው ዘር የተሻለ ሕይወት ይመራል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። አንተስ ምን ይመስልሃል?