በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓለም ላይ ሃይማኖት ባይኖር ይሻል ይሆን?

በዓለም ላይ ሃይማኖት ባይኖር ይሻል ይሆን?

በዓለም ላይ ሃይማኖት ባይኖር ይሻል ይሆን?

ዲስ ዓይነት አምላክ የለሽነትን የሚያራምዱት ሰዎች፣ ሃይማኖት የሌለበትን ዓለም ይኸውም አጥፍቶ ጠፊዎች፣ ሃይማኖታዊ ጦርነቶችና መንጎቻቸውን የሚበዘብዙ የቴሌቪዥን ወንጌላውያን የሌሉበትን ዓለም ለማየት ይናፍቃሉ። አንተስ እንዲህ ዓይነቱ ዓለም ይማርክሃል?

ይህን ጥያቄ ከመመለስህ በፊት ‘በመላው ምድር አምላክ የለሽነት ቢሰፍን ዓለም የተሻለ እንደሚሆን የሚያሳይ ማስረጃ አለ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፦ በካምቦዲያ ክሜር ሩዥ የተባለው ፓርቲ የማርክሲዝምን ርዕዮተ ዓለም የሚከተል አምላክ የለሽ መንግሥት ለመመሥረት ባደረገው ጥረት 1.5 ሚሊዮን ሰዎች አልቀዋል። አምላክ የለሽ መሆኗን በይፋ ባወጀችው የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ደግሞ የጆሴፍ ስታሊን አገዛዝ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። እርግጥ ነው፣ ለእነዚህ ክፉ ድርጊቶች በሙሉ በቀጥታ መንስኤ የሆነው አምላክ የለሽነት ነው ማለት አይቻልም። ሆኖም እነዚህ እልቂቶች በዓለም ላይ አምላክ የለሽነት መኖሩ በሰዎች መካከል ሰላምና ስምምነት እንደሚሰፍን ዋስትና ሊሆን እንደማይችል ያሳያሉ።

ሃይማኖት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ብዙ መከራ እንዳመጣ የሚካድ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ ለዚህ ተጠያቂው አምላክ ነው? በጭራሽ! አንድ ሰው በሞባይል ስልክ እያወራ መኪና ሲነዳ አደጋ ቢያጋጥመው መኪናውን ያመረተው ፋብሪካ ለአደጋው ተጠያቂ እንደማይሆን ሁሉ አምላክም ሃይማኖት ላስከተለው መከራ ተጠያቂ አይሆንም። በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ መንስኤ የሆኑት ነገሮች በርካታ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አንዱ ከሃይማኖታዊ እምነቶች ይበልጥ ሥር የሰደደ ነው። ይኸውም የወረስነው አለፍጽምና ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” ይላል። (ሮም 3:23) ይህ የኃጢአት ዝንባሌ ራስ ወዳድነትን፣ ተገቢ ያልሆነ ኩራትን፣ በራስ የመመራት ፍላጎትንና ዓመፅን ያበረታታል። (ዘፍጥረት 8:21) በተጨማሪም ሰዎች ለሚፈጽሟቸው መጥፎ ድርጊቶች ሰበብ እንዲፈጥሩና እንዲህ ያለ ድርጊታቸውን በቸልታ ወደሚመለከቱ እምነቶች እንዲያዘነብሉ ያደርጋል። (ሮም 1:24-27) በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ “ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ ዝሙት፣ ሌብነት፣ በሐሰት መመስከርና ስድብ ይወጣሉ” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነው።—ማቴዎስ 15:19

እውነተኛውን ሃይማኖት ከሐሰተኛው መለየት ያስፈልጋል

እስከ አሁን ከተመለከትነው አንጻር በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለውን እውነተኛ አምልኮ ከሐሰተኛው አምልኮ መለየት የግድ ይላል። እውነተኛ አምልኮ ሰዎች በውስጣቸው ያሉትን የኃጢአት ዝንባሌዎች ለማስወገድ እንዲጥሩ ይረዳቸዋል። እንዲሁም የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ደግነትን፣ ጥሩነትን፣ ገርነትን፣ ራስን መግዛትን፣ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆንንና ለሌሎች አክብሮት ማሳየትን ያበረታታል። (ገላትያ 5:22, 23) በሌላ በኩል ግን የሐሰት ሃይማኖት ኢየሱስ ያወገዛቸውን መጥፎ ድርጊቶች በቸልታ በማለፍ በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አካሄድ ይከተላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ የሰዎችን ‘ጆሮ ከመኮርኮር’ ጋር ያመሳስለዋል።—2 ጢሞቴዎስ 4:3

እንደ ሐሰት ሃይማኖት ሁሉ አምላክ የለሽነትም ሰዎች በሥነ ምግባር ረገድ ግራ እንዲጋቡ ወይም ግልጽ መመሪያ እንዲያጡ ያደርግ ይሆን? ‘አምላክ የለም’ ከተባለ ለድርጊታችን በኃላፊነት የሚጠይቀን መለኮታዊ አካል የለም ማለት ነው፤ እንዲሁም “ልናከብረው የሚገባን ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ደንብ የለም” ማለት እንደሚሆን የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ፊሊፕ ጆንሰን ይናገራሉ። በዚህ ዓይነት ሥነ ምግባርም አንጻራዊ ይሆናል። ይኸውም እያንዳንዱ ሰው ለራሱ የሚመራበትን የሥነ ምግባር መሥፈርት ያወጣል ማለት ነው፤ ያውም ከፈለገ ነው። አምላክ የለሽነት ለአንዳንዶች ማራኪ ፍልስፍና ሆኖ እንዲታያቸው ያደረገው እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እንደሆነ ግልጽ ነው።—መዝሙር 14:1

ይሁንና አምላክ፣ ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎችም ሆኑ አምላክ የለሾች የሚያራምዱትን የሐሰት ትምህርት ብሎም እንዲህ ያለውን ትምህርት የሚያስፋፉትን ሰዎች ለዘላለም አይታገሳቸውም። * አምላክ በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ቅን የሆኑ ሰዎች “በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ” በማለት ቃል ገብቷል። አክሎም “ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ” ብሏል። (ምሳሌ 2:21, 22) አምላክ ይህን ሲያደርግ ማንኛውም ሰው፣ ማንኛውም ሰብዓዊ ፈላስፋና ማንኛውም ሰብዓዊ ድርጅት ሊያስገኘው የማይችል ዓለም አቀፋዊ ሰላምና ደስታ ይሰፍናል።—ኢሳይያስ 11:9

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳማኝ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘውን የማስጠኛ መጽሐፍ ምዕራፍ 11ን ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አምላክ በሃይማኖት ስም ስለሚፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶች ምን ይሰማዋል?

ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የተሰጠው ምድር የቀድሞ ነዋሪዎች በሥነ ምግባር የረከሱ ነበሩ፤ ከነዓናውያን የሚባሉት እነዚህ ሕዝቦች በዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን፣ ግብረ ሰዶምንና ከእንስሳት ጋር መገናኘትን ጨምሮ የተለያዩ የፆታ ብልግናዎችን ይፈጽሙ እንዲሁም በሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ ልጆችን መሥዋዕት ያደርጉ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:2-27) አርኪኦሎጂ ኤንድ ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው የመሬት ቁፋሮ ሲደረግ “በአረማውያን መሠዊያዎች ዙሪያ በነበሩት የመቃብር ቦታዎች ውስጥ የአመድ ክምችቶችና የሕፃናት አፅሞች የተገኙ ሲሆን ይህም [ሕፃናትን መሥዋዕት ማድረግ] በስፋት የሚፈጸም ተግባር እንደነበረ ያመለክታል።” አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ የማመሣከሪያ መጽሐፍ እንደሚገልጸው ከነዓናውያን የአምልኮ ሥርዓታቸውን የሚያከናውኑት በአማልክቶቻቸው ፊት የፆታ ብልግና በመፈጸምና የበኩር ልጆቻቸውን ለእነዚሁ አማልክት መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ ነበር። ይኸው መጽሐፍ አክሎም “የከነዓናውያንን ከተሞች ፍርስራሽ ቆፍረው ጥናት ያደረጉ አርኪኦሎጂስቶች አምላክ ከነዓናውያንን ለምን ከዚያ ቀደም ብሎ እንዳላጠፋቸው በጣም ገርሟቸዋል” ብሏል።

አምላክ ከነዓናውያንን ማጥፋቱ በስሙ የሚፈጸሙ የክፋት ድርጊቶችን ለዘላለም እንደማይታገሥ ልብ እንድንል የሚያደርግ ማሳሰቢያ ነው። የሐዋርያት ሥራ 17:31 “[አምላክ] በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህንንም ለማድረግ ቀን ወስኗል” ይላል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎችም ሆኑ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች የጭካኔ ድርጊቶችን ፈጽመዋል

ቤተ ክርስቲያን ሂትለርን ደግፋለች

የክሜር ሩዥ ፓርቲ ሰለባዎች አፅም፣ ካምቦዲያ

[ምንጭ]

AP Photo