በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ “ቅዱሳን” መጸለይ ተገቢ ነው?

ወደ “ቅዱሳን” መጸለይ ተገቢ ነው?

ወደ “ቅዱሳን” መጸለይ ተገቢ ነው?

ማሪ እና ቴሬዛ ራሳቸውን “ጥሩ ካቶሊኮች” እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። ሁለቱም “በቅዱሳን” ያምኑ ነበር። ማሪ እርዳታ ለማግኘት ወደ “ቅዱሳን” መጸለይ እንደምትችል ታምን ነበር። ቴሬዛም የትውልድ መንደሯ ጠባቂ እንደሆነ ወደሚታመነው “ቅዱስ” አዘውትራ ትጸልይ ነበር። እንዲሁም ከእሷ ጋር ተመሳሳይ ስም ወዳላት “ቅድስት ቴሬዛ” ትጸልይ ነበር።

ሪ እና ቴሬዛ ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረከት ለማግኘት ወደ “ቅዱሳን” ይጸልያሉ። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው ከሆነ “ቅዱሳን ለሰዎች ይማልዳሉ” እንዲሁም “ከአምላክ እርዳታ ለማግኘት እነሱን መለመን ‘ጥሩና ጠቃሚ’ ነው።”

ይሁንና አምላክ ጉዳዩን እንዴት ይመለከተዋል? ስለ እኛ እንዲማልዱልን ወደ “ቅዱሳን” መጸለያችንን አምላክ ይቀበለዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እንመልከት።

“ቅዱሳንን” መለመን ይኖርብናል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ወደ “ቅዱሳን” እንደጸለዩ የሚናገር ሐሳብ አንድም ቦታ አናገኝም። ለምን? ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው “የቅዱሳን አማላጅነት ጥቅም በግልጽ የታወቀው በ3ኛው መቶ ዘመን” ስለነበረ ነው። ይህ ደግሞ ክርስቶስ ከሞተ ከ200 ዓመታት በኋላ ማለት ነው። በመሆኑም ይህ ትምህርት ከኢየሱስም ሆነ ስለ እሱ አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የመነጨ አይደለም። ታዲያ እነሱ ይህን ትምህርት ያላስተማሩት ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አምላክ ብቻ መጸለይ እንዳለብን በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያስተምር ሲሆን መጸለይ ያለብንም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንደሆነ ይናገራል። ኢየሱስ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 14:6) ይህ ግልጽ የሆነ ሐሳብ በማቴዎስ 6:9-13 ላይ ከተመዘገበው የኢየሱስ ትምህርት ጋር ይስማማል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ስለ ጸሎት ባስረዳቸው ጊዜ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ። . . .” (ማቴዎስ 6:9) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጸለይ ያለብን በሰማይ ወደሚኖረው አባታችን ብቻ ነው። ይህ እውነት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ነው።

ጸሎት የአምልኮ ክፍል ነው

ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው “ጸሎት ለአምላክ፣ ለአማልክት ወይም ለሌሎች የሚመለኩ ነገሮች የሚቀርቡ አምልኮታዊ ክብር የታከለባቸው ቃላትንና ሐሳቦችን ያመለክታል። . . . ከሞላ ጎደል በዓለም ላይ ባሉት ሃይማኖቶች በሙሉ፣ ጸሎት ወሳኝ የሆነ የአምልኮ ክፍል ነው ሊባል ይችላል።” በመሆኑም ‘ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን ከሆነው አካል ውጪ ለማንኛውም ሌላ አካል ጸሎት ለማቅረብ መንበርከካችን ተገቢ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። (መዝሙር 36:9) ኢየሱስ “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት [ያመልኩታል]፤ . . . ምክንያቱም አብ እንዲህ ዓይነት ሰዎች እንዲያመልኩት ይፈልጋል” ብሏል። (ዮሐንስ 4:23) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪያችን እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ “ቀናተኛ” አምላክ እንደሆነ ይናገራል።—ዘዳግም 4:24፤ 6:15

ክርስቲያኑ ሐዋርያው ዮሐንስ ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሐዋርያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገቡትን በጣም አስደናቂ ራእዮች ከተቀበለ በኋላ በአድናቆት ስሜት ከመዋጡ የተነሳ እነዚህን ነገሮች ያሳየውን ‘መልአክ ለማምለክ እግሩ ሥር ተደፋ።’ በዚህ ጊዜ መልአኩ ምን ምላሽ ሰጠ? “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ ይህን እንዳታደርግ! እኔኮ ከአንተም ሆነ ነቢያት ከሆኑት ወንድሞችህ . . . ሁሉ ጋር አብሬ የማገለግል ባሪያ ነኝ። አምላክን አምልክ” አለው። (ራእይ 22:8, 9) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክን ብቻ ማምለክ እንዳለብን በድጋሚ ያሳስባል።

ከላይ ከተገለጸው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ‘ጸሎት ሰሚ’ ተብሎ የተጠራው አምላክ ብቻ ነው። (መዝሙር 65:2) ከዚህም በላይ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን በጸሎት ለቀረቡለት ተገቢ ልመናዎች በሙሉ መልስ ለመስጠት ሥልጣን፣ እውቀትና ኃይል ያለው እሱ ብቻ ነው። (ኢዮብ 33:4) ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ እሱ ሊያደርጋቸው የማይችላቸው ነገሮች እንዳሉ በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:23፤ 24:36) ያም ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ዘር አማላጅ ሆኖ የማገልገል ኃላፊነትን ጨምሮ ታላቅ ሥልጣን ተሰጥቶታል።

ሩኅሩኅ አማላጅ

ኢየሱስን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ለእነሱ ለመማለድ ሁልጊዜ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ የሚቀርቡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” ብሏል። (ዕብራውያን 7:25) በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ‘በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ ለሚቀርቡት’ ሩኅሩኅ አማላጅ ሆኖ ሊያገለግላቸው ይችላል። ይህ ሲባል እኛ ወደ ኢየሱስ ጸልየን እሱ ጸሎታችንን ያደርስልናል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በኢየሱስ ስም ወደ አምላክ እንጸልያለን ማለት ነው፤ በዚህ መንገድ ኢየሱስ ለተሰጠው ሥልጣን እውቅና እንሰጣለን። ታዲያ ኢየሱስ ፍጹም በሆነ መንገድ ያማልዳል የምንለው ለምንድን ነው?

መጀመሪያ ነገር፣ ኢየሱስ ሰው ሆኖ መኖሩ የሌሎችን ሥቃይ በተሻለ ሁኔታ እንዲረዳ አስችሎታል። (ዮሐንስ 11:32-35) በተጨማሪም የታመሙትን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሳትና ወደ እሱ ለመጡት ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ በመስጠት ለሰዎች ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ማቴዎስ 15:29, 30፤ ሉቃስ 9:11-17) ኃጢአትንም እንኳ ሳይቀር ይቅር ብሏል። (ሉቃስ 5:24) ይህን ማወቃችን የመተማመን ስሜት እንዲኖረን ያደርጋል፤ ምክንያቱም ኃጢአት ብንሠራ “በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”—1 ዮሐንስ 2:1

ፍቅርና ርኅራኄ በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ አማላጅ ሆኖ የማገልገል ሥልጣን አልተሰጠንም። ይሁን እንጂ ለሌሎች መጸለይ እንችላለን። እንዲያውም ለሌሎች ያለን ፍቅር እንድንጸልይላቸው ያነሳሳናል። ያዕቆብ “አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ታላቅ ኃይል አለው፤ ብዙ ነገርም ያከናውናል” በማለት ጽፏል—ያዕቆብ 5:16

ማሪ እና ቴሬዛ መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር እንደነዚህ ያሉትን ውድ እውነቶች መማር ችለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች አንተም እንዲህ እንድታደርግ ይጋብዙሃል። ኢየሱስ እንደተናገረው ‘አምላክን የሚያመልኩት በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።’—ዮሐንስ 4:24