በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራ የሚደርስብን፣ የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?

መከራ የሚደርስብን፣ የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?

ፈጣሪያችን የሚመለከተን እንደ ልጆቹ አድርጎ ነው። ስለዚህ ችግር እንዲደርስብን አይፈልግም። ሆኖም ሕይወት በችግር የተሞላ ነው። ይህ የሆነው ለምን ድን ነው?

ለመከራ የዳረጉን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ናቸው

“በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ . . . ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”—ሮም 5:12

አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥራቸው ፍጹም አእምሮና ፍጹም አካል ነበራቸው። በተጨማሪም አምላክ፣ ምድር ላይ ኤደን በተባለ ውብ ገነት ውስጥ እንዲኖሩ አደረገ። ከአንዱ በስተቀር በገነት ውስጥ ካሉት ዛፎች ሁሉ መብላት እንደሚችሉ ነገራቸው። አዳምና ሔዋን ግን ከዚያ ከተከለከሉት ዛፍ ፍሬ በሉ፤ በዚህ መንገድ ኃጢአት ሠሩ። (ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:1-19) አምላክ በእሱ ላይ በማመፃቸው ባልና ሚስቱን ከገነት አባረራቸው፤ ከዚያ በኋላ ሕይወታቸው በመከራ የተሞላ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ልጆች ወለዱ፤ ሕይወት ለልጆቻቸውም ከባድ ነበር። ሁሉም አርጅተው ሞቱ። (ዘፍጥረት 3:23፤ 5:5) የምንታመመው፣ የምናረጀውና የምንሞተው ከእነዚህ ወላጆቻችን ስለተገኘን ነው።

ለሚደርስብን መከራ ሌሎቹ ተጠያቂዎች ክፉ መናፍስት ናቸው

“መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።”—1 ዮሐንስ 5:19

እዚህ ላይ “ክፉው” የተባለው ሰይጣን ነው። ሰይጣን፣ በአምላክ ላይ ያመፀ በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር ነው። (ዮሐንስ 8:44፤ ራእይ 12:9) ከጊዜ በኋላ፣ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትም ከሰይጣን ጋር ተባብረዋል። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት፣ አጋንንት ተብለው ተጠርተዋል። ክፉ መናፍስት ኃይላቸውን የሚጠቀሙት ሰዎችን ለማሳሳትና ከፈጣሪ ለማራቅ ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎችን መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚገፋፉት እነሱ ናቸው። (መዝሙር 106:35-38፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1) ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎችን ማሠቃየትና በእነሱ ላይ መከራ ማምጣት ያስደስታቸዋል።

አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን ለመከራ የምንዳርገው እኛ ራሳችን ነን

“አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”—ገላትያ 6:7

ብዙውን ጊዜ መከራ የሚደርስብን፣ በወረስነው ኃጢአትና ሰይጣን በዓለም ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ የተነሳ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ሰዎች በገዛ እጃቸው በራሳቸው ላይ መከራ ያመጣሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መጥፎ ነገር ያደርጉና ወይም የሞኝነት ውሳኔ ይወስኑና የሚያስከትለውን መዘዝ ለማጨድ ይገደዳሉ። በሌላ በኩል ግን፣ ሰዎች ጥሩ ነገር ሲያደርጉ ጥሩ ነገር ያጭዳሉ። ለምሳሌ ሐቀኛ፣ ትጉ ሠራተኛና አፍቃሪ የሆነ ባልና አባት ብዙ መልካም ነገሮችን ያጭዳል፤ ቤተሰቡም ደስተኛ ይሆናል። ቁማርተኛ፣ ሰካራም ወይም ሰነፍ ከሆነ ግን ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን ለድህነት ይዳርጋል። ስለዚህ ፈጣሪያችን የሚለንን መስማታችን ጠቃሚ ነው። እሱ ‘ሰላማችን እንዲበዛልንና’ ሌሎች ብዙ መልካም ነገሮችን እንድናጭድ ይፈልጋል።—መዝሙር 119:165

የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ ነው

“በመጨረሻዎቹ ቀናት . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ . . . ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

በዛሬው ጊዜ የብዙ ሰዎች ባሕርይ ልክ በዚህ ትንቢት ላይ እንደተነገረው ነው። የሰዎች ባሕርይ መለወጡ፣ በዚህ ዓለም ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳይ አንዱ ማስረጃ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባለንበት ዘመን ጦርነት፣ ረሃብ፣ ታላላቅ የምድር ነውጦችና በሽታዎች እንደሚከሰቱም ይናገራል። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8፤ ሉቃስ 21:10, 11) ብዙዎችን ለመከራና ለሞት እየዳረጉ ያሉት እነዚህ ነገሮች ናቸው።