በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገሮች የሚደርሱባቸው ለምንድን ነው?

ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገሮች ይደርሱባቸዋል—ለምን?

ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገሮች ይደርሱባቸዋል—ለምን?

ይሖዋ አምላክ፣ * የሁሉ ነገር ፈጣሪና ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ ብዙ ሰዎች፣ መጥፎ ነገሮችን ጨምሮ በዓለም ላይ ለሚደርሰው ነገር ሁሉ ተጠያቂው እሱ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውነተኛው አምላክ ምን እንደሚል ተመልከት፦

  •  “እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ . . . ነው።”—መዝሙር 145:17

  • “[አምላክ] መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ . . . ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።”—ዘዳግም 32:4

  • “ይሖዋ ከአንጀት የሚራራና መሐሪ [ነው]።”—ያዕቆብ 5:11

አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ አያደርግም። ነገር ግን ሌሎች መጥፎ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸው ይሆን? በጭራሽ። መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም ሰው ፈተና በሚደርስበት ጊዜ ‘አምላክ እየፈተነኝ ነው’ አይበል” ይላል። ለምን? ምክንያቱም “አምላክ በክፉ ነገሮች ሊፈተን አይችልም፤ እሱ ራሱም ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) ይሖዋ አንድን ሰው መጥፎ ነገር እንዲፈጽም በማነሳሳት አይፈትንም። አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ አያደርግም፤ እንዲሁም ሌሎች መጥፎ ነገር እንዲፈጽሙ አያነሳሳም። ታዲያ ለሚደርሱት መጥፎ ነገሮች ተጠያቂው ማን ወይም ምንድን ነው?

በአጉል ጊዜ አጉል ቦታ መገኘት

መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ላይ መከራ የሚደርስበትን አንዱን ምክንያት ሲጠቅስ “ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል” በማለት ይናገራል። (መክብብ 9:11 NW) ያልተጠበቁ ክስተቶች ወይም አደጋዎች ሲደርሱ አንድ ሰው በዚህ መጎዳት አለመጎዳቱ በአብዛኛው የተመካው አደጋው በደረሰበት ሰዓት በቦታው በመኖሩ ወይም ባለመኖሩ ላይ ነው። ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ግንብ ተንዶባቸው ስለሞቱ 18 ሰዎች ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 13:1-5) ሰዎቹ የአደጋው ሰለባዎች የሆኑት ከዚያ በፊት በሠሩት ነገር ምክንያት ሳይሆን ግንቡ በተናደበት ጊዜ በዚያ አካባቢ ስለነበሩ ብቻ ነው። በቅርቡ ደግሞ ጥር 2010 ላይ ሄይቲ በአውዳሚ የምድር መናወጥ ተመትታ ነበር፤ የሄይቲ መንግሥት ከ300,000 የሚበልጡ ሰዎች እንደሞቱ ተናግሯል። ይህ አደጋ እገሌ ከገሌ ሳይል የእነዚያን ሁሉ ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል። በሽታም ቢሆን ማንኛውንም ሰው በማንኛውም ጊዜ ሊይዘው ይችላል።

አምላክ፣ ጥሩ ሰዎችን ክፉ ነገር እንዳይደርስባቸው የማይጠብቃቸው ለምንድን ነው?

አንዳንዶች ‘አምላክ እንደ እነዚህ ያሉ ሕይወትን የሚያሳጡ አደጋዎች እንዳይደርሱ መከላከል አይችልም? ደግሞስ ጥሩ ሰዎችን በአደጋው እንዳይጎዱ ሊጠብቃቸው አይችልም?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። አምላክ እንዲህ እንዲያደርግ ከተፈለገ ግን መጥፎ ነገሮች ከመድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል። አምላክ ወደፊት የሚሆኑ ነገሮችን የማወቅ ችሎታ እንዳለው ግልጽ ቢሆንም እዚህ ላይ ልናስብበት የሚገባ ጥያቄ አለ፤ ይህም ‘አምላክ ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሁልጊዜ ነው?’ የሚል ነው።—ኢሳይያስ 42:9

ቅዱሳን መጻሕፍት “አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል” ይላሉ። (መዝሙር 115:3) ይሖዋ አስፈላጊ እንደሆነ ያመነበትን ነገር ያደርጋል፤ ይህ ሲባል ግን ማድረግ የሚችለውን ነገር ሁሉ ያደርጋል ማለት አይደለም። አስቀድሞ ለማወቅ የሚወስነውን ነገር በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ  ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንቶቹ የሰዶምና የገሞራ ከተሞች ክፋት በጣም በተስፋፋ ጊዜ አምላክ ለአብርሃም “አድራጎታቸው እኔ ዘንድ እንደ ደረሰው ጩኸት መሆኑን ለማየት ወደዚያው እወርዳለሁ፤ እንደዚያ ካልሆነም ዐውቃለሁ” በማለት ነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 18:20, 21) ይሖዋ ለተወሰነ ጊዜ ያህል፣ በእነዚያ ከተሞች ክፋት ምን ያህል እንደተስፋፋ የማወቅ ችሎታውን አልተጠቀመበትም። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ነገሮችን አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የማይጠቀምበት ጊዜ አለ። (ዘፍጥረት 22:12) ይህ ግን አምላክ ፍጽምና እንደሚጎድለው ወይም ድክመት እንዳለበት የሚያሳይ አይደለም። አምላክ ‘ሥራው ፍጹም’ ስለሆነ የወደፊቱን ጊዜ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ከዓላማው ጋር በሚጣጣም መንገድ ነው፤ ሰዎች እሱ የሚፈልገውን አካሄድ እንዲከተሉ ፈጽሞ አያስገድድም። * (ዘዳግም 32:4) ታዲያ ምን ብለን መደምደም እንችላለን? አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሁልጊዜ ሳይሆን እንደ አስፈላጊነቱ ነው።

አምላክ፣ ጥሩ ሰዎች ወንጀል እንዳይፈጸምባቸው የማይከላከልላቸው ለምንድን ነው?

ተጠያቂዎቹ ሰዎች ናቸው?

ለክፋት ድርጊቶች በተወሰነ መጠን ተጠያቂ የሆኑት ሰዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ጎጂ ወደሆኑ ድርጊቶች የሚመራውን ሂደት እንዴት እንደሚገልጸው ልብ በል። “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ደግሞ በተግባር ሲፈጸም ሞትን ያስከትላል።” (ያዕቆብ 1:14, 15) ሰዎች ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶቻቸውን በተግባር ሲፈጽሟቸው ወይም ለተሳሳተ ምኞት ሲሸነፉ መጥፎ ነገር ያጋጥማቸዋል። (ሮም 7:21-23) ታሪክ እንደሚያሳየው የሰው ልጆች ዘግናኝ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፤ እንዲሁም ይህ ነው የማይባል መከራ እንዲደርስ አድርገዋል። ከዚህም በላይ ክፉ ሰዎች፣ ሌሎችም ምግባረ ብልሹ እንዲሆኑ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፤ ይህም ክፋት ይበልጥ እንዲስፋፋ ያደርጋል።—ምሳሌ 1:10-16

የሰው ልጆች ዘግናኝ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፤ ይህ ነው የማይባል መከራ እንዲደርስም አድርገዋል

ታዲያ አምላክ፣ ሰዎች መጥፎ ነገሮች እንዳያደርጉ ጣልቃ ገብቶ መከልከል ይኖርበታል? እስቲ የሰውን አፈጣጠር እንመልከት። ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክ ሰውን በመልኩ፣ ይኸውም በራሱ አምሳል እንደፈጠረው ይናገራሉ። በመሆኑም ሰዎች የአምላክን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አላቸው። (ዘፍጥረት 1:26) ሰዎች የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ስጦታ ስለተሰጣቸው አምላክን ለመውደድና በእሱ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ ለእሱ ታማኝ ለመሆን መምረጥ ይችላሉ። (ዘዳግም 30:19, 20) ታዲያ አምላክ፣ ሰዎች እሱ የሚፈልገውን ጎዳና እንዲከተሉ የሚያስገድድ ከሆነ የሰጣቸውን የመምረጥ ነፃነት መጋፋት አይሆንበትም? እንዲህ ቢያደርግ የሰው ልጆች፣ አስቀድሞ ከተቀመጠላቸው መመሪያ ምንም ዝንፍ ሳይሉ እንደሚንቀሳቀሱ ማሽኖች ይሆናሉ! የምናደርገውን እና የሚደርስብንን ማንኛውንም ነገር የሚወስነው ዕድላችን ወይም እጣ ፈንታችን ቢሆን ኖሮም ሁኔታው ተመሳሳይ ይሆን ነበር። አምላክ የራሳችንን አካሄድ የመምረጥ ነፃነት በመስጠት ስላከበረን ምንኛ ደስተኞች ነን! ይህ ሲባል ግን የሰው ልጆች ስህተትና የሚያደርጉት መጥፎ ምርጫ ከሚያስከትለው ጉዳት መቼም ቢሆን መገላገል አንችልም ማለት አይደለም።

የመከራ መንስኤ ካርማ ነው?

የሂንዱ ወይም የቡድሂዝም እምነት ተከታይ የሆኑ ብዙ ሰዎች በሪኢንካርኔሽን እና በካርማ ያምናሉ። ካርማ ምንድን  ነው? ካርማ የሚባለው ‘አንድ ሰው በአሁኑ ሕይወቱ ውስጥ ለሚያጋጥሙት ነገሮች ምክንያት የሚሆኑት በቀድሞ ሕይወቱ ያደረጋቸው ነገሮች ናቸው’ የሚለው እምነት ነው። በመሆኑም የሂንዱ ወይም የቡድሂዝም እምነት ተከታይ የሆነን ሰው በዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ የቀረበውን ጥያቄ ብትጠይቀው “በጥሩ ሰዎች ላይ መጥፎ ነገሮች የሚደርሱት በካርማ ሕግ ምክንያት ነው። በቀድሞው ሕይወታቸው ወቅት ለሠሩት ኃጢአት ዋጋቸውን እየተቀበሉ ነው” የሚል መልስ ይሰጥሃል። *

የካርማን ሕግ ካነሳን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት ምን እንደሚል መመልከቱ ጠቃሚ ነው። የሰው ዘር ታሪክ በጀመረበት በኤደን ገነት ፈጣሪ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዳም የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ ኃጢአት ባይሠራ ኖሮ ለዘላለም በኖረ ነበር። ሞት፣ አዳም የአምላክን ትእዛዝ በመጣሱ ምክንያት የመጣ ቅጣት ነው። ከዚያም አዳምና ሔዋን፣ ልጆች ሲወለዱ “ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) በመሆኑም “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነው” ሊባል ይችላል። (ሮም 6:23) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” በማለት ይገልጻል። (ሮም 6:7) በሌላ አነጋገር ሰዎች ሲሞቱ የኃጢአታቸውን ቅጣት ከፍለዋል፤ በመሆኑም ከመሞታቸው በፊት ለሠሩት ኃጢአት ሲቀጡ አይኖሩም።

በዛሬው ጊዜ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ መንስኤው ካርማ እንደሆነ ይናገራሉ። በካርማ የሚያምን ሰው፣ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ የሚደርሰው መከራ እምብዛም ሳይረብሸው በፀጋ ተቀብሎት ይኖራል። ይሁን እንጂ ይህ ጽንሰ ሐሳብ መጥፎ ነገሮች የማይኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አይሰጥም። በካርማ ትምህርት መሠረት አንድ ግለሰብ እንዲህ ካለው ሁኔታ መገላገል የሚችለው በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ባሕርይና ልዩ እውቀት በማዳበር እንደገና ከመወለድ ሂደት ነፃ ሲወጣ ብቻ እንደሆነ ይታመናል። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሐሳቦች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው በጣም የተለዩ ናቸው። *

የክፋት ዋነኛው መንስኤ

የመከራ ዋነኛ መንስኤ “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ታውቃለህ?—ዮሐንስ 14:30

ይሁንና የክፋት ዋነኛው መንስኤ ሰው አይደለም። መጀመሪያ ላይ የአምላክ ታማኝ መልአክ የነበረው ሰይጣን ዲያብሎስ “በእውነት ውስጥ ጸንቶ [ባለመቆሙ]” ኃጢአት ወደ ዓለም እንዲገባ አድርጓል። (ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ዓመፅ አስነሳ። (ዘፍጥረት 3:1-5) ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰይጣንን “ክፉው” እና “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ጠርቶታል። (ማቴዎስ 6:13፤ ዮሐንስ 14:30) አብዛኞቹ የሰው ልጆች፣ የይሖዋን መልካም መንገዶች ችላ እንዲሉ ሰይጣን በሚያሳድርባቸው ግፊት ተሸንፈው የእሱ ዓይነት አካሄድ እየተከተሉ ነው። (1 ዮሐንስ 2:15, 16)“መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው” በማለት 1 ዮሐንስ 5:19 ይናገራል። የክፋትን ጎዳና በመምረጥ ከሰይጣን ጋር የተባበሩ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትም አሉ። ሰይጣንና አጋንንቱ ‘መላውን ዓለም እያሳሳቱ’ እንደሆነና ‘በምድር ላይ ወዮታ’ እንዳስከተሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 12:9, 12) በመሆኑም ለክፋት ዋነኛው ተጠያቂ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሰዎች ላይ ለሚደርሱት መጥፎ ነገሮች ተጠያቂው አምላክ አይደለም፤ ሰዎች እንዲሠቃዩም አያደርግም። እንዲያውም በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው አምላክ ክፋትን ለማስወገድ ቃል ገብቷል።

^ አን.3 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።

^ አን.11 አምላክ ክፋት እንዲቀጥል የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለመረዳት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።

^ አን.16 ስለ ካርማ ሕግ አመጣጥ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ስንሞት ምን እንሆናለን? የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 8-12 ተመልከት።

^ አን.18 ሙታን ስላሉበት ሁኔታና የሞቱ ሰዎች ስላላቸው ተስፋ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ለማወቅ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 6 እና 7 ተመልከት።