በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለአረጋውያን መጽናኛና ተስፋ መስጠት

ለአረጋውያን መጽናኛና ተስፋ መስጠት

በብዙ አገራት እንደሚስተዋለው ሁሉ በአውስትራሊያም የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ከእነዚህ አረጋውያን መካከል አንዳንዶቹ የሚኖሩት በአረጋውያን መጦሪያ ተቋማት ውስጥ ነው፤ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች አረጋውያኑን ከጤናቸውና በየዕለቱ ከሚያስፈልጋቸው ነገር ጋር በተያያዘ እርዳታ ይሰጧቸዋል።

እርግጥ ነው፣ በአረጋውያን መጦሪያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው አካላዊ እርዳታ ብቻ አይደለም። አረጋውያኑ አንዳንድ ጊዜ ሊሰላቹ፣ ብቸኝነት ሊሰማቸው አልፎ ተርፎም ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ቪክቶሪያ፣ አውስትራሊያ ውስጥ በምትገኘው ፖርትላንድ ከተማ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ በሚገኙ ሁለት የአረጋውያን መጦሪያ ተቋማት ውስጥ ለሚኖሩ አረጋውያን በየሳምንቱ ጉብኝት ያደርጋሉ።

ለአረጋውያኑ የሚስማማ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት

በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከነዋሪዎቹ ጋር ሲገናኙ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ፤ ለምሳሌ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ስለተከሰቱ ወሳኝ ክንውኖች ይነጋገራሉ። ጄሰን “ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰነ ሐሳብ ለአረጋውያኑ እናነብላቸዋለን፤ ከዚያም በዘገባዎቹ ላይ ውይይት እናደርጋለን” ሲል ተናግሯል። አብዛኞቹ አረጋውያን የጤና እክል አለባቸው፤ በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮቹ፣ አምላክ ሕመምንና ሞትን እንደሚያስቀር የገባውን ቃል በመንገር መጽናኛና ተስፋ ይሰጧቸዋል።

ቶኒ የተባለ በዚያ የሚያገለግል የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ ከነዋሪዎቹ ጋር የምንወያየው ለሠላሳ ደቂቃ ያህል ብቻ ነበር፤ በኋላ ግን አረጋውያኑ ለበለጠ ጊዜ እንድናወያያቸው ፈለጉ። በዚህ የተነሳ አሁን የምናወያያቸው ለአንድ ሰዓት ያህል ነው። እርግጥ፣ አንዲት አረጋዊት ውይይቱን ወደ ሁለት ሰዓት ብናራዝመው ደስ እንደሚላቸው ነግረውን ነበር።” አንዳንዶቹ አረጋውያን ማየት የተሳናቸው፣ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ አሊያም ዕቃዎችን ለመያዝ የሚቸገሩ በመሆናቸው የይሖዋ ምሥክሮቹ በውይይቱ ወቅት ይረዷቸዋል፤ እንዲሁም በውይይቱ ላይ የቻሉትን ያህል ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያበረታቷቸዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮቹ ከነዋሪዎቹ ጋር አምላክን የሚያወድሱ መዝሙሮችን የሚዘምሩ ሲሆን አረጋውያኑ አብዛኛውን ጊዜ ተጨማሪ መዝሙር ለመዘመር ጥያቄ ያቀርባሉ። ጆን a የተባሉ አንድ አረጋዊ “መዝሙሮቻችሁን በጣም እንወዳቸዋለን። ስለ አምላክ እንድናውቅና ለእሱ አክብሮት እንዲኖረን ይረዱናል” ሲሉ ተናግረዋል። ጁዲት የተባሉ ማየት የተሳናቸው አንዲት አረጋዊት ደግሞ የሚወዷቸውን መዝሙሮች ሙሉ ግጥም በቃላቸው ይዘውታል።

የይሖዋ ምሥክሮቹ በዚያ ለሚኖር ለእያንዳንዱ አረጋዊ ትኩረት ይሰጣሉ። ብራያን የተባለ አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ የታመመ አረጋዊ ካለ የይሖዋ ምሥክሮቹ ክፍላቸው ድረስ ሄደው እንደሚጠይቋቸው ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ሄደን እናጫውታቸዋለን እንዲሁም ስላሉበት ሁኔታ ለማወቅ ጥረት እናደርጋለን። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፣ የታመሙት አረጋውያን ተሽሏቸው እንደሆነ ለማወቅ በሌላ ቀን ተመልሰን ሄደን እንጠይቃቸዋለን።”

“ወደ እኛ የላካችሁ አምላክ ነው”

በአረጋውያን መጦሪያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩት አብዛኞቹ አረጋውያን በሚደረግላቸው ጉብኝት ደስተኛ ናቸው። በየሳምንቱ በውይይቱ ላይ የሚሳተፉ ፒተር የተባሉ አረጋዊ “ፕሮግራሞቹን የምጠባበቀው በጉጉት ነው” ብለዋል። ጁዲት የተባሉት አረጋዊት ደግሞ የምትንከባከባቸውን ሴት “ዛሬ እኮ ረቡዕ ነው! ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራሙ አዘጋጂኝ። ማርፈድ አልፈልግም!” ይሏታል።

አረጋውያኑ የሚማሩት ነገር የሚያስደስታቸው ሲሆን ከአምላክ ጋር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መቀራረብ እንደቻሉ ይሰማቸዋል። ሮበርት የተባሉ አረጋዊ፣ ኢየሱስ ካስተማራቸው ነገሮች መካከል አንዱን ከተማሩ በኋላ “ከዚህ በፊት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ፈጽሞ ተረድቼው አላውቅም ነበር። አሁን ግን ገብቶኛል!” ሲሉ ተናግረዋል። ዴቪድ የተባሉት አረጋዊ ደግሞ መጸለይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የተገነዘቡ ሲሆን “ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት አስችሎኛል፤ አምላክ እውን እንዲሆንልኝም ረድቶኛል” ብለዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠው ተስፋም አረጋውያኑን ያስደስታቸዋል። ሊኔት የተባሉ አረጋዊት “ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ አጽናኝ ሐሳብ ስለምታካፍሉን እናመሰግናችኋለን” በማለት ለይሖዋ ምሥክሮቹ ተናግረዋል። ሌላ አረጋዊት ደግሞ “ወደ እኛ የላካችሁ አምላክ ነው” ብለዋል።

ማርጋሬት የተባሉ አረጋዊት በጉብኝቱ በጣም ስለተደሰቱ በአቅራቢያቸው ባለ የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ ዘወትር ሄደው ይሰበሰባሉ። የጤና እክል ስላለባቸውና ብዙም መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ወደ አዳራሹ ለመሄድ ትልቅ ጥረት ማድረግ ይጠይቅባቸዋል። እኚህ ሴት ለይሖዋ ምሥክሮቹ “የሕይወታችንን ዓላማ እንድናውቅ ረድታችሁናል” በማለት ተናግረዋል።

‘በጣም አስደናቂ እርዳታ እያደረጋችሁ ነው’

በአረጋውያን መጦሪያ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችም የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያደርጉት ጉብኝት አድናቆት አላቸው። በአካባቢው የምታገለግል አና የተባለች የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ የሚሠሩት ሰዎች፣ አረጋውያኑ ከውይይቱ በኋላ ይበልጥ ደስተኞች እንደሚሆኑ አስተውለዋል። በዚህም የተነሳ በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ያበረታቷቸዋል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ብራያን ደግሞ “ሠራተኞቹ የወዳጅነት መንፈስ ያላቸውና ተባባሪ ናቸው። ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ ብዙ መሥዋዕት ይከፍላሉ” በማለት ተናግሯል።

የአረጋውያኑ ቤተሰቦችም፣ የሚወዷቸው የቤተሰባቸው አባላት በውይይቱ ሲደሰቱ ማየታቸው አስደስቷቸዋል። በዚያ የሚኖሩ አረጋዊ ወላጅ ያሏት አንዲት ሴት “ለእናቴ እያደረጋችሁላት ያለው እርዳታ በጣም አስደናቂ ነው” በማለት ለይሖዋ ምሥክሮቹ ምስጋናዋን ገልጻለች።

a በአረጋውያን መጦሪያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ስም ተቀይሯል።