በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጸለይ ለምን አስፈለገ? አምላክ ጸሎቴን ይመልስልኛል?

መጸለይ ለምን አስፈለገ? አምላክ ጸሎቴን ይመልስልኛል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ መልስ ይሰጣል። ከመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ካሉ ሰዎች ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው አምላክ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም።” (መዝሙር 145:19) ይሁንና አምላክ ጸሎትህን ሰምቶ መልስ መስጠቱ በአብዛኛው የተመካው በአንተ ላይ ነው።

አምላክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር

  •   ወደ ኢየሱስ፣ ወደ ማርያም፣ ወደ ቅዱሳን፣ ወደ መላእክት ወይም ለምስሎች ሳይሆን ወደ አምላክ መጸለይ ይኖርብናል። ‘ጸሎትን የሚሰማው’ ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው።​—መዝሙር 65:2

  •   ከአምላክ ፈቃድ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መጸለይ ይጠበቅብናል።​—1 ዮሐንስ 5:14

  •   የኢየሱስን ሥልጣን በመቀበል በእሱ ስም መጸለይ ይኖርብናል። ኢየሱስ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል።​—ዮሐንስ 14:6

  •   በእምነት መጸለይ ይኖርብናል፤ አስፈላጊ ከሆነም እምነት እንዲጨመርልን መጸለይ እንችላለን።​—ማቴዎስ 21:22፤ ሉቃስ 17:5

  •   በትህትና ከልባችን መጸለይ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል” ይላል።​—መዝሙር 138:6

  •   ያለማቋረጥ መጸለይ ይኖርብናል። ኢየሱስ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል” ብሏል።​—ሉቃስ 11:9

አምላክ ቦታ የማይሰጠው ነገር

  •   ዘርህ ወይም ዜግነትህ። ‘አምላክ አያዳላም፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።’​—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

  •   አቋቋምህ ወይም አቀማመጥህ። ተቀምጠህ፣ በግንባርህ ተደፍተህ፣ ተንበርክከህ ወይም ቆመህ መጸለይ ትችላለህ።​—1 ዜና መዋዕል 17:16፤ ነህምያ 8:6፤ ዳንኤል 6:10፤ ማርቆስ 11:25

  •   ድምፅህን አሰምተህ መጸለይህ ወይም በልብህ መጸለይህ። አምላክ ሌሎች ሰዎች ሳያስተውሉ በልባችን እንኳ የምናቀርባቸውን ጸሎቶች ይሰማል።​—ነህምያ 2:1-6

  •   ያሰሰበህ ጉዳይ ከባድ ወይም ቀላል መሆኑ። አምላክ ‘ስለ እኛ ስለሚያስብ የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ እንድንጥል’ አበረታቶናል።​—1 ጴጥሮስ 5:7