በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለዘላለም መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

ለዘላለም መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ . . . ለዘላለም ይኖራል” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 2:17) ታዲያ የአምላክ ፈቃድ ማለትም አንተ እንድታደርግ የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው?

  •   ስለ አምላክና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ተማር። ኢየሱስ ወደ አምላክ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው።” (ዮሐንስ 17:3) አምላክንና ኢየሱስን “ማወቅ” የሚቻለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በሕይወታችን ውስጥ በተግባር በማዋል ነው። a መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪና ሕይወት ሰጪ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ ያስተምረናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:24, 25) ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ያስተማረውን ኢየሱስን በተመለከተ ይናገራል።—ዮሐንስ 6:67-69

  •   በኢየሱስ ቤዛ ላይ እምነት ይኑርህ። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው “ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” ነው። (ማቴዎስ 20:28) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሰው ልጆች በምድር ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። b (መዝሙር 37:29) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) በኢየሱስ ማመን በእሱ ትምህርቶችና በአባቱ ፈቃድ መሠረት ሕይወታችንን መምራትንም ይጨምራል።—ማቴዎስ 7:21፤ ያዕቆብ 2:17

  •   ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርት። አምላክ ወደ እሱ እንድንቀርብና ወዳጆቹ እንድንሆን ይፈልጋል። (ያዕቆብ 2:23፤ 4:8) አምላክ ዘላለማዊ ነው፤ መቼም ሊሞት አይችልም። ወዳጆቹም ቢሆኑ ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። አምላክ እሱን የሚፈልጉ ሁሉ ‘ለዘላለም ተደስተው እንዲኖሩ’ እንደሚፈልግ በቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል።—መዝሙር 22:26

ብዙዎች የዘላለም ሕይወትን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ የሰው ልጆች በራሳቸው ጥረት ለዘላለም መኖር ይችላሉ።

 እውነታው፦ አንዳንድ የሕክምና ዘዴዎች የሰዎችን የሕይወት ዘመን እንደሚያስረዝሙ ተስፋ ቢሰጡም እነዚህ ጥረቶች ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ አያስችሉም። የዘላለም ሕይወት ሊሰጠን የሚችለው “የሕይወት ምንጭ” የሆነው አምላክ ብቻ ነው። (መዝሙር 36:9) አምላክ ‘ሞትን ለዘላለም በመዋጥ’ ታማኝ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 25:8፤ 1 ዮሐንስ 2:25

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ለዘላለም መኖር የሚችሉት የተወሰነ ዘር ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው።

 እውነታው፦ አምላክ አያዳላም። “ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) የትኛውም ዓይነት ዘርና ባሕል ያላቸው ሰዎች አምላክን እስከታዘዙ ድረስ ለዘላለም መኖር ይችላሉ።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ለዘላለም መኖር አሰልቺ ነው።

 እውነታው፦ የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሰጠን አምላክ ነው፤ አምላክ ደግሞ ይወደናል እንዲሁም ደስተኛ ሆነን እንድንኖር ይፈልጋል። (ያዕቆብ 1:17፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ደስተኛ ሆነን መኖር የምንችለው ትርጉም ያለው ሥራ ካለን ብቻ እንደሆነ አምላክ ያውቃል። (መክብብ 3:12) በመሆኑም አምላክ በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩ ሰዎች፣ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን የሚጠቅም አርኪና ትርጉም ያለው ሥራ እንደሚኖራቸው ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 65:22, 23

 ከዚህም ሌላ ለዘላለም የሚኖሩ ሰዎች ስለ ፈጣሪያቸውና ስፍር ቁጥር ስለሌላቸው የፍጥረት ሥራዎቹ አዳዲስ ነገሮችን መማራቸውን ይቀጥላሉ። አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው ለዘላለም የመኖርና ስለ እሱ የመማር ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው፤ ሆኖም “የሰው ልጆች እውነተኛው አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያከናወነውን ሥራ በምንም ዓይነት መርምረው ሊደርሱበት አይችሉም።” (መክብብ 3:10, 11) በእርግጥም፣ ለዘላለም የሚኖሩ ሰዎች ሁልጊዜም የሚማሩትና የሚሠሩት አስደሳች ነገር ይኖራቸዋል።

a የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ያስተምራሉ። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው እንዴት ነው? የተባለውን ቪዲዮ ተመልከት።

bኢየሱስ ያድናል—እንዴት?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።