የማቴዎስ ወንጌል 7:1-29

  • የተራራው ስብከት (1-27)

    • “በሌሎች ላይ አትፍረዱ” (1-6)

    • ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ፈልጉ፣ አንኳኩ (7-11)

    • ወርቃማው ሕግ (12)

    • ጠባቡ በር (13, 14)

    • “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” (15-23)

    • በዓለት ላይና በአሸዋ ላይ የተሠራ ቤት (24-27)

  • ሕዝቡ በኢየሱስ ትምህርት ተደነቁ (28, 29)

7  “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤*+  በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤+ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል።+  ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?+  ወይም በራስህ ዓይን ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ?  አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።  “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ።+ አለዚያ ዕንቁዎቹን በእግራቸው ይረጋግጧቸዋል፤ ተመልሰውም ይጎዷችኋል።  “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤+ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።+  የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤+ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል።  ደግሞስ ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? 10  ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? 11  ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት+ መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!+ 12  “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።+ ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል የሚሉት ይህንኑ ነው።+ 13  “በጠባቡ በር ግቡ፤+ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ 14  ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።+ 15  “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች+ ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው+ ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።+ 16  ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ?+ 17  በተመሳሳይም ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።+ 18  ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ የበሰበሰም ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም።+ 19  መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ወደ እሳት ይጣላል።+ 20  በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።+ 21  “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው።+ 22  በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣+ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’+ 23  እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።+ 24  “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል።+ 25  ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በዓለት ላይ ስለተመሠረተ አልተደረመሰም። 26  ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውል ሁሉ ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል።+ 27  ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤+ ቤቱም ተደረመሰ፤ እንዳልነበረም ሆነ።” 28  ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤+ 29  የሚያስተምራቸው እንደ እነሱ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነበርና።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መፍረዳችሁን ተዉ።”