የማቴዎስ ወንጌል 10:1-42

  • የኢየሱስ 12 ሐዋርያት (1-4)

  • አገልግሎትን በተመለከተ የተሰጠ መመሪያ (5-15)

  • ደቀ መዛሙርቱ ስደት ይደርስባቸዋል (16-25)

  • ሰውን ሳይሆን አምላክን ፍሩ (26-31)

  • ሰላምን ሳይሆን ሰይፍን አመጣለሁ (32-39)

  • የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት መቀበል (40-42)

10  ከዚያም ኢየሱስ 12ቱን ደቀ መዛሙርት ጠርቶ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያዝዙ ሥልጣን ሰጣቸው፤+ ይህን ያደረገውም ርኩሳን መናፍስትን እንዲያስወጡ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እንዲፈውሱ ነው።  የ12ቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፦+ በመጀመሪያ፣ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና+ ወንድሙ እንድርያስ፣+ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣+  ፊልጶስና በርቶሎሜዎስ፣+ ቶማስና+ ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣+ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ፣  ቀነናዊው* ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን የከዳው የአስቆሮቱ ይሁዳ።+  ኢየሱስ እነዚህን 12ቱን የሚከተለውን መመሪያ በመስጠት ላካቸው፦+ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ማንኛውም የሳምራውያን ከተማም+ አትግቡ፤  ከዚህ ይልቅ ከእስራኤል ቤት ወደጠፉት በጎች ብቻ ሂዱ።+  በምትሄዱበት ጊዜም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ።+  የታመሙትን ፈውሱ፤+ የሞቱትን አስነሱ፤ የሥጋ ደዌ ያለባቸውን አንጹ፤ አጋንንትንም አስወጡ። በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ።  ወርቅ ወይም ብር አሊያም መዳብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤+ 10  ወይም ለጉዞ የምግብ ከረጢት ወይም ሁለት ልብስ* ወይም ትርፍ ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤+ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።+ 11  “በምትገቡበት ማንኛውም ከተማ ወይም መንደር መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው ፈልጉ፤ እስክትወጡም ድረስ እዚያው ቆዩ።+ 12  ወደ ቤትም ስትገቡ ቤተሰቡን ሰላም በሉ። 13  ቤቱ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ሰላማችሁ ይድረሰው፤+ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ። 14  የሚቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የሚሰማ ሰው ካጣችሁ ከዚያ ቤት ወይም ከተማ ስትወጡ፣ የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።*+ 15  እውነት እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ+ ይቀልላቸዋል። 16  “እነሆ፣ በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ጠንቃቆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ።+ 17  ሰዎች ለፍርድ ሸንጎዎች አሳልፈው ይሰጧችኋል፤+ በምኩራቦቻቸውም+ ይገርፏችኋል፤+ ስለዚህ ራሳችሁን ከእነሱ ጠብቁ። 18  ደግሞም በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤+ በዚያ ጊዜ ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ መመሥከር ትችላላችሁ።+ 19  ይሁን እንጂ አሳልፈው ሲሰጧችሁ እንዴት ወይም ምን ብለን እንመልሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና፤+ 20  በምትናገሩበት ጊዜ ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ይልቁንም በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው።+ 21  በተጨማሪም ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ፤ ደግሞም ያስገድሏቸዋል።+ 22  በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤+ እስከ መጨረሻው የጸና* ግን ይድናል።+ 23  በአንድ ከተማ ስደት ሲያደርሱባችሁ ወደ ሌላ ከተማ ሽሹ፤+ እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ እስከሚመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞችና መንደሮች ፈጽሞ አታዳርሱም። 24  “ተማሪ* ከአስተማሪው፣ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም።+ 25  ተማሪ እንደ አስተማሪው፣ ባሪያም እንደ ጌታው ከሆነ በቂ ነው።+ ሰዎች የቤቱን ጌታ ብዔልዜቡል*+ ካሉት ቤተሰቦቹንማ እንዴት ከዚህ የከፋ አይሏቸው! 26  ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ ሁሉ መገለጡ፣ ሚስጥር የሆነም ሁሉ መታወቁ አይቀርም።+ 27  በጨለማ የነገርኳችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በሹክሹክታ የሰማችሁትንም በይፋ ስበኩ።+ 28  ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን* ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤+ ከዚህ ይልቅ ነፍስንም ሆነ ሥጋን በገሃነም* ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ።+ 29  ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም* አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም።+ 30  የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል። 31  ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።+ 32  “እንግዲያው በሰዎች ፊት ለሚመሠክርልኝ+ ሁሉ እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሠክርለታለሁ።+ 33  በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ።+ 34  በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ የመጣሁት ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አይደለም።+ 35  እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ እንዲሁም ምራትን ከአማቷ ለመለያየት ነው።+ 36  በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ። 37  ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም።+ 38  የመከራውን እንጨት* የማይቀበልና የማይከተለኝ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።+ 39  ነፍሱን* ለማዳን የሚሞክር ሁሉ ያጣታል፤ ነፍሱን* ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ሁሉ ግን ያገኛታል።+ 40  “እናንተን የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ሁሉ ደግሞ የላከኝን ይቀበላል።+ 41  ነቢይን ስለ ነቢይነቱ የሚቀበል ሁሉ የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤+ ጻድቅን ስለ ጻድቅነቱ የሚቀበል ሁሉ የጻድቅን ዋጋ ያገኛል። 42  እውነት እላችኋለሁ፣ የእኔ ደቀ መዝሙር በመሆኑ ምክንያት ከእነዚህ ከትናንሾቹ ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውኃ የሚሰጥ ሁሉ በምንም ዓይነት ዋጋውን አያጣም።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቀናተኛው።”
ወይም “ትርፍ ልብስ።”
የእግርን አቧራ ማራገፍ ከኃላፊነት ነፃ መሆንን ያመለክታል።
ወይም “የሚጸና።”
ወይም “ደቀ መዝሙር።”
የአጋንንት አለቃ ወይም ገዢ ለሆነው ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው።
ወይም “ሕይወትን።” የወደፊት ሕይወት ተስፋን ያመለክታል።
ቃል በቃል “አሳሪዮን።” ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ሕይወቱን።”
ወይም “ሕይወቱን።”