በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ዘረኝነት

ዘረኝነት

የተለያዩ ዘሮች ሊኖሩ የቻሉት እንዴት ነው?

“አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት።”—ዘፍጥረት 3:20

ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) “ሁሉም የሰው ልጆች ዝርያቸው አንድ ሲሆን ሁሉም ከአንድ የዘር ግንድ የመጡ ናቸው” ብሏል።—የዘርና የዘር ጥላቻ አዋጅ፣ 1978

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ አዳምና ሔዋን የተባሉትን ሁለት ሰዎች ከፈጠረ በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው። (ዘፍጥረት 1:28) በመሆኑም አዳምና ሔዋን ለመላው የሰው ዘር አባትና እናት ሆኑ። በኋላ ላይ የጥፋት ውኃ መጥቶ የምድርን ነዋሪዎች በሙሉ ባጠፋ ጊዜ አራት ጥንዶች ማለትም ኖኅና ሚስቱ ከሦስት ልጆቻቸውና ከልጆቻቸው ሚስቶች ጋር ተረፉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም የኖኅ ልጆች ዝርያ እንደሆንን ይናገራል።—ዘፍጥረት 9:18, 19

 አንድ ዘር ከሌላው ይበልጣል?

“በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም [አምላክ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ።”—የሐዋርያት ሥራ 17:26

አንዳንዶች ምን ብለዋል?

በ20ኛው መቶ ዘመን በርካታ ቡድኖች የዘረኝነት አመለካከት አዳብረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ናዚዎች የዘር የበላይነት መኖሩን የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ ማስረጃ እንዳለ ይናገሩ ነበር። በሌላ በኩል ግን ቀደም ሲል የተጠቀሰው የዩኔስኮ አዋጅ “የሰው ዘር አንድ እንደሆነና በዚህም የተነሳ ሁሉም የሰው ዘርና ሁሉም ሕዝብ እኩል” እንደሆነ ገልጿል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 “አምላክ [አያዳላም] . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” ይላል። በዚህ ምክንያት ማንም ሰው አንድ ዘር ከሌላው ይበልጣል ማለት አይችልም።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” በማለት ክርስቲያኖች ሊከተሉ የሚገባውን አቋም ገልጿል። (ማቴዎስ 23:8) ተከታዮቹ ከመከፋፈልና ከመናናቅ ይልቅ “ፍጹም አንድነት እንዲኖራቸው” ጸልዮአል።—ዮሐንስ 17:20-23፤ 1 ቆሮንቶስ 1:10

ዘረኝነት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

“በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ . . . ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ።”—ኢሳይያስ 2:2

አንዳንዶች ምን ያስባሉ?

የዘር ጥላቻ እየተባባሰ በመምጣቱ በብዙ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ዘረኝነትን በማስወገድ ረገድ ጉልህ መሻሻል ስለ መኖሩ ጥርጣሬ አላቸው። እንዲያውም አንዳንዶች የዘር እኩልነት ፈጽሞ ሊኖር አይችልም ከሚል መደምደሚያ ደርሰዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ የዘር ጥላቻ ለዘላለም እንዲቀጥል አይፈቅድም። ከዚህ ይልቅ በእሱ መንግሥት ሥር “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” ሰዎች ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም አንድ ሆነው የሚያገለግሉት ከመሆኑም ሌላ ለሌሎች ሰዎች እውነተኛ ፍቅር ያሳያሉ። (ራእይ 7:9) የአምላክ መንግሥት በልባችን ውስጥ ያለ ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የሰው ዘሮች በሙሉ በመካከላቸው ምንም ዓይነት የዘር ክፍፍል ሳይኖር አንድ ሆነው እንዲኖሩባት ባሰባት በዚህች ምድር ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መስተዳድር ነው። *

^ አን.15 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት። www.isa4310.com/am ላይም ይገኛል።