በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ማቴዎስ 11:28-30—“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”

ማቴዎስ 11:28-30—“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”

 “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”—ማቴዎስ 11:28-30 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”—ማቴዎስ 11:28-30 የ1954 ትርጉም

የማቴዎስ 11:28-30 ትርጉም

 ኢየሱስ አድማጮቹ ወደ እሱ እንዲመጡ ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦላቸዋል። ከእሱ መማራቸው እረፍትና እፎይታ እንደሚያስገኝላቸው ዋስትና ሰጥቷቸዋል።

 “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ።” ኢየሱስ ይህን ፍቅራዊ ግብዣ ያቀረበላቸው ሰዎች የሃይማኖት መሪዎቻቸው በጫኑባቸው ሕጎችና ወጎች የተነሳ ‘ሸክም ከብዷቸው’ ነበር። (ማቴዎስ 23:4፤ ማርቆስ 7:7) ሕዝቡ ራሳቸውን ለማስተዳደር ለረጅም ሰዓት መሥራትና መልፋት ይጠበቅባቸው የነበረ መሆኑ እንዲሁም የነበረባቸው ጭንቀት ሸክም ሆኖባቸው ነበር።

 “እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ።” ኢየሱስ፣ እሱ ያቀረበውን ደግነት የሚንጸባረቅበት ግብዣ ለሚቀበሉ ሰዎች እረፍት ወይም እፎይታ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። እረፍት የሰጣቸው አምላክ በእርግጥ ከእነሱ የሚጠብቀው ምን እንደሆነ እንዲገነዘቡ በመርዳት ነው። (ማቴዎስ 7:24, 25) ይህ እውቀት ከሐሰት ትምህርቶችና ጨቋኝ ከሆኑ ሃይማኖታዊ ወጎች ባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል። (ዮሐንስ 8:31, 32) የኢየሱስን ትምህርቶች መማርና ተግባራዊ ማድረግ ጥረት ቢጠይቅም እንዲህ ማድረግ እረፍት ያስገኛል።

 “ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ።” በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ ሠራተኞች ከባድ ሸክም ለመሸከም ትከሻ ላይ የሚደረግ የእንጨት ቀንበር ይጠቀሙ ነበር። በዚህም ምክንያት “ቀንበር” የሚለው ቃል ለሌላ ሰው ሥልጣን ወይም መመሪያ መገዛት የሚል ትርጉም ማስተላለፍ ጀመረ። (ዘሌዋውያን 26:13፤ ኢሳይያስ 14:25፤ ኤርምያስ 28:4) “ከእኔም ተማሩ” የሚለው ሐረግ “ደቀ መዛሙርቴ (ተማሪዎቼ) ሁኑ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ፣ አድማጮቹ እሱን በመከተልና ምሳሌውን በመኮረጅ ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑ እያበረታታቸው ነበር።—ዮሐንስ 13:13-15፤ 1 ጴጥሮስ 2:21

 “ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” ኢየሱስ፣ አድማጮቹ ወዲያውኑ ከችግሮቻቸው በሙሉ እንደሚገላገሉ ቃል መግባቱ አልነበረም። ሆኖም አድማጮቹ ማጽናኛና ተስፋ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:25-32፤ 10:29-31) የእሱ ደቀ መዛሙርት የሆኑና ትምህርቶቹን የተቀበሉ ሰዎች አምላክን ማገልገል ሸክም እንዳልሆነ፣ ከዚህ ይልቅ እውነተኛ እርካታ እንደሚያስገኝ ተገንዝበዋል።—1 ዮሐንስ 5:3

 “ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።” በወቅቱ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በተለየ ኢየሱስ ትሑትና ገር ነበር። (ዮሐንስ 7:47-49) ጨካኝ ወይም ጨቋኝ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ደግና በቀላሉ የሚቀረብ ሰው ነበር። ከተከታዮቹ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነበር። (ማቴዎስ 7:12፤ ማርቆስ 6:34፤ ሉቃስ 9:11) በተጨማሪም ተከታዮቹ የአምላክን ምሕረት ማግኘትና ንጹሕ ሕሊና መያዝ የሚያስገኘውን እረፍት ማጣጣም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳይቷቸዋል። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ 6:14) የኢየሱስ ግሩም ባሕርያት ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ ብቻ ሳይሆን ልዝብ የሆነውን ቀንበሩን እንዲሸከሙና ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑም አነሳስተዋቸዋል።

የማቴዎስ 11:28-30 አውድ

 ኢየሱስ በማቴዎስ 11:28-30 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው በ31 ዓ.ም. በገሊላ የስብከት ዘመቻ ላይ በነበረበት ወቅት ነው። ከወንጌል ጸሐፊዎች መካከል፣ ኢየሱስ ያቀረበውን ይህን ደግነት የሚንጸባረቅበት ግብዣ የጻፈው ሐዋርያው ማቴዎስ ብቻ ነው። ማቴዎስ አይሁዳዊ ከመሆኑም ሌላ በቀድሞ ሕይወቱ ቀረጥ ሰብሳቢ ስለነበር ሕዝቡ ሮማውያን በጣሉባቸው ግብር እንዲሁም ብልሹ በሆነው የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የተነሳ ሸክም እንደበዛባቸው በገዛ ዓይኑ ተመልክቷል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ አባቱ ይሖዋ a የሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ ምስኪኖችንና የተጨቆኑ ሰዎችን ወደ እሱ እንዲመጡ ሲጋብዝ መመልከቱ ማቴዎስን አበረታቶት መሆን አለበት።—ማቴዎስ 11:25-27

 የማቴዎስ ወንጌል፣ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕና የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያሉትን ግሩም ባሕርያት ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—ማቴዎስ 1:20-23፤ ኢሳይያስ 11:1-5

 የማቴዎስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።