በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገንዘብ መበደር ይኖርብኛል?

ገንዘብ መበደር ይኖርብኛል?

“መበደር እንደ ሠርግ፣ የተበደሩትን መመለስ ግን እንደ ለቅሶ ነው።”—የስዋሂሊ ምሳሌያዊ አነጋገር

ይህ አባባል በምሥራቅ አፍሪካ ባሉ ሰዎች ዘንድ በሰፊው የታወቀ ነው፤ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ብዙ ሰዎችም እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዳላቸው ጥርጥር የለውም። አንተስ ከጓደኛህ ወይም ከሌላ ቦታ ገንዘብ መበደርን አስመልክቶ እንዲህ ይሰማሃል? ገንዘብ መበደር አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ቢመስልም ይህን ማድረግ የተሻለው አማራጭ ነው? መበደር ምን አደጋዎች አሉት?

አንድ ሌላ የስዋሂሊ አባባል፣ ብድር የሚያስከትለውን ዋና አደጋ ይገልጻል። “መበደርም ሆነ ማበደር ወዳጅነትን ያበላሻሉ” ይላል። ብድር፣ አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ያለው ወዳጅነት ወይም ዝምድና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል። ግለሰቡ ገንዘቡን በጊዜው ለመመለስ ጥሩ ዕቅድ ቢያወጣም ብሎም ይህን ለማድረግ ፍላጎቱ ቢኖረውም እንኳ ሁኔታዎች እንደተጠበቀው ላይሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ገንዘቡ ሳይከፈል ብድሩን ለመመለስ የተዋዋሉበት ጊዜ ቢያልፍ አበዳሪው ሊበሳጭ ይችላል። ይህም ቅያሜ እንዲፈጠር እንዲሁም በአበዳሪውና በተበዳሪው አልፎ ተርፎም በቤተሰቦቻቸው መካከል የነበረው ግንኙነት እንዲሻክር ሊያደርግ ይችላል። ብድር የጠብ መንስኤ ሊሆን ስለሚችል ያጋጠመንን የገንዘብ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ቀላሉ መንገድ አድርገን ልንመለከተው አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ መጨረሻ አማራጭ አድርገን ልንቆጥረው ይገባል።

ገንዘብ መበደር አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድናም ጭምር ሊነካበት ይችላል። እንዴት? አንደኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሆን ብሎ ዕዳውን ለመክፈል እምቢተኛ የሆነ ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 37:21) በተጨማሪም ‘ተበዳሪ የአበዳሪ ባሪያ ነው’ በማለት በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 22:7) ተበዳሪው የተበደረውን ገንዘብ እስኪመልስ ድረስ ለአበዳሪው ግዴታ እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል። “የሰው እግር ከተዋስክ የምትሄደው ሰውየው ወደሚፈልገው ቦታ ብቻ ነው” የሚል አንድ የአፍሪካውያን አባባል አለ። ይህ አባባል ከባድ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቀ ሰው የፈለገውን ነገር የማድረግ ነፃነት እንደሌለው የሚጠቁም ነው።

በመሆኑም አንድ ሰው የተበደረውን ገንዘብ ለመመለስ ቅድሚያ መስጠት አለበት። አለበለዚያ ችግሮች መነሳታቸው አይቀርም። ዕዳ እየተከማቸ ሲሄድ አንድ ሰው ጭንቀት ሊገጥመው፣ እንቅልፍ ሊያጣ፣ ከመጠን በላይ ለመሥራት ሊገደድ ይችላል፤ ወይም ደግሞ በባልና ሚስት መካከል ጭቅጭቅ ሊፈጠርና ቤተሰብ ሊፈርስ ይችላል፤ አልፎ ተርፎም በግለሰቡ ላይ ክስ ሊመሠረትበትና እስር ቤት ሊገባ ይችላል። በእርግጥም “እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ  አይኑርባችሁ” የሚለው በሮም 13:8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው።

መበደር አስፈላጊ ነው?

ቀደም ሲል ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር ገንዘብ ለመበደር ስናስብ ጠንቃቃ መሆናችን አስፈላጊ ነው። በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል አስተዋይነት ነው፦ ያለህበት ሁኔታ እንድትበደር የሚያስገድድ ነው? መበደር ያስፈለገህ ገንዘቡ ቤተሰብህን ለማስተዳደር የግድ ስለሚያስፈልግህ ነው? ወይስ መበደሩን የፈለግኸው በተወሰነ መጠንም ቢሆን የስግብግብነት መንፈስ ስላደረብህ ምናልባትም አሁን ካለህ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ለመድረስ ስላሰብክ ነው? ብድር በመውሰድ ራስህን ግዴታ ውስጥ ከማስገባት ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ባለህ ጥቂት ነገር ረክተህ ብትኖር የተሻለ ነው።

እርግጥ ነው፣ ለመበደር የሚያስገድድ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፤ ለምሳሌ፣ አንድ ድንገተኛ ሁኔታ ሊፈጠርና ከመበደር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለህ ሊሰማህ ይችላል። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ለመበደር ከወሰነ መልካም ምግባር እንዳለው ማሳየት ይኖርበታል። ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

አንደኛ፣ አንድ ሰው ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ገንዘብ አለው ብለህ ስላሰብክ ብቻ መጠቀሚያ ልታደርገው አይገባም። አንድ ሰው ገንዘብ ስላለው ብቻ እኛን በገንዘብ የመርዳት ግዴታ እንዳለበት ሊሰማን አይገባም። ወይም ደግሞ እንደዚህ ካለው ሰው ከተበደርን በኋላ ቃላችንን የመጠበቅ ግዴታ እንደሌለብን ማሰብ አይኖርብንም። ብዙ ገንዘብ ያላቸው በሚመስሉ ሰዎች መቅናት አይኖርብህም።—ምሳሌ 28:22 የ1954 ትርጉም

በተጨማሪም የተበደርከውን ገንዘብ በወቅቱ መልሰህ ክፈል። አበዳሪው የተበደርከውን ገንዘብ በዚህ ቀን መመለስ አለብህ ባይልህም እንኳ አንተ ራስህ ቀነ ገደብ አስቀምጥ፤ ከዚያም ባስቀመጥከው ቀነ ገደብ ውስጥ ብድሩን ክፈል። በመካከላችሁ አለመግባባት እንዳይፈጠር ከፈለግህ ውላችሁን በጽሑፍ ማስፈርህ ጠቃሚ ነው። (ኤርምያስ 32:9, 10) የሚቻል ከሆነም አንተ ራስህ አበዳሪውን በአካል አግኝተህ የተበደርከውን ገንዘብ መልስለት፤ ይህም እሱን ለማመስገን አጋጣሚ ይሰጥሃል። የተበደርከውን ገንዘብ በታማኝነት የምትመልስ ከሆነ በመካከላችሁ ያለው ግንኙነት ጥሩ ይሆናል። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን፣ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን” ብሏል። (ማቴዎስ 5:37) በተጨማሪም “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል” የሚለውን ወርቃማ ሕግ ምንጊዜም አስታውስ።—ማቴዎስ 7:12

ጠቃሚ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገንዘብ ለመበደር የሚገፋፋንን ስሜት ለመቆጣጠር የሚያስችል ቀላል ምክር ይሰጣል። እንዲህ ይላል፦ “በእርግጥ፣ ባለው ነገር ለሚረካ ሰው ለአምላክ ማደር ትልቅ ትርፍ ያስገኛል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:6) በሌላ አነጋገር፣ አንድ ሰው ባለው ነገር የሚረካ ከሆነ መበደር ከሚያስከትላቸው አሳዛኝ መዘዞች ያመልጣል። እርግጥ ነው፣ የምንፈልገውን ነገር ወዲያውኑ እጃችን ውስጥ ማስገባት ትልቅ ነገር ተደርጎ በሚታይበት በዚህ ዓለም ውስጥ ባለን ነገር ረክቶ መኖር ቀላል አይደለም። በመሆኑም ‘ለአምላክ የማደር’ ባሕርይ የሚያስፈልገን እዚህ ላይ ነው። እንዴት?

በእስያ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ወጣት በነበሩበት ወቅት የራሳቸው ቤት ባላቸው ሰዎች ይቀኑ ነበር። በመሆኑም ያጠራቀሙትን ገንዘብ እንዲሁም ከባንክና ከዘመዶቻቸው የሚያገኙትን ብድር ተጠቅመው ቤት ለመግዛት ወሰኑ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በየወሩ የሚከፍሉት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እየከበዳቸው መጣ። ተጨማሪ ሥራ ይዘው ረጅም ሰዓት መሥራት ጀመሩ፤ ይህ ደግሞ ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ እንዲቀንስ አደረገ። ባልየው እንዲህ ብሏል፦ “የሚሰማኝ ውጥረትና ሕመም እንዲሁም እንቅልፍ ማጣቴ በራሴ ላይ ከባድ ድንጋይ እንደተጫነብኝ እንዲሰማኝ አደረገ። መፈናፈኛ አጣሁ።”

“ቁሳዊ ነገሮችን ከመንፈሳዊ ነገሮች አንጻር መመልከት ከችግር ይጠብቃል”

ከጊዜ በኋላ በ1 ጢሞቴዎስ 6:6 ላይ ያለውን ሐሳብ ያስታወሱ ሲሆን ብቸኛው መፍትሔ ቤቱን መሸጥ እንደሆነ ወሰኑ። ሸክማቸውን ሙሉ በሙሉ እስኪገላገሉ ድረስ ሁለት ዓመት ፈጅቷል። ባልና ሚስቱ ከተሞክሯቸው የተማሩት ነገር ምንድን ነው? “ቁሳዊ ነገሮችን ከመንፈሳዊ ነገሮች አንጻር መመልከት ከችግር ይጠብቃል” በማለት ተናግረዋል።

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን የስዋሂሊ ምሳሌያዊ አነጋገር ብዙ ሰዎች ያውቁታል። ሆኖም ገንዘብ ከመበደር አላገዳቸውም። ታዲያ ከላይ ከተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አንጻር ‘ገንዘብ መበደር ይኖርብኛል?’ በሚለው ጥያቄ ላይ በቁም ነገር ማሰብ የጥበብ አካሄድ አይሆንም?