በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የገንዘብ ችግርና ዕዳ—መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላል?

የገንዘብ ችግርና ዕዳ—መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ። የሚከተሉት አራት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ከገንዘብና ከዕዳ ጋር በተያያዘ ሊረዱህ ይችላሉ፦

  1.   ዕቅድ አውጣ። “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል።” (ምሳሌ 21:5) አንድን ነገር ቅናሽ ስላገኘህ ብቻ ለመግዛት አትቸኩል። ከዚህ ይልቅ ዕቅድ ወይም በጀት አውጣ፤ ከዚያም ያወጣኸውን ዕቅድ በጥብቅ ተከተል።

  2.   አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አትግባ። “ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።” (ምሳሌ 22:7) ዕዳ ካለብህና መክፈል ካቃተህ ይህን ግዳጅህን መወጣት ስለምትችልበት ሌላ መንገድ ከአበዳሪዎችህ ጋር ለመደራደር ጥረት አድርግ። ተስፋ አትቁረጥ። መጽሐፍ ቅዱስ ሳያመዛዝን ለአንድ ተበዳሪ ዋስ ለሆነና በኋላም ተጠያቂ ለሆነ ሰው የሚሰጠውን የሚከተለው ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ፦ “በጎረቤትህ እጅ ስለወደቅህ፣ ሄደህ ራስህን አዋርድ፤ ጎረቤትህን አጥብቀህ ነዝንዘው። ዐይኖችህ እንቅልፍ አይያዛቸው፣ ሽፋሽፍቶችህም አያንጐላጁ።” (ምሳሌ 6:1-5) የመጀመሪያው ሙከራህ ባይሳካም እንኳ ማስተካከያ እንዲደረግልህ ጥረት ማድረግህን መቀጠል ይኖርብሃል።

  3.   ለገንዘብ ተገቢ አመለካከት ይኑርህ። “ራሳቸውን የሚወዱ ሰዎች ሀብታም ለመሆን ሲጣደፉ፣ ድኽነት በቶሎ የሚመጣባቸው መሆኑን አይገነዘቡም።” (ምሳሌ 28:22 የ1980 ትርጉም) ምቀኝነትና ስግብግብነት በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ኪሳራ ከማስከተል ባሻገር መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ እንድንል ያደርጉናል።

  4.   ባለህ ነገር ረክተህ ኑር። “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ገንዘብ ደስታንም ሆነ እርካታን ሊገዛ አይችልም። በምድር ላይ ካሉት እጅግ ደስተኛ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሃብታም አይደሉም። ለደስታቸው ምክንያት የሆኑት ነገሮች ለቤተሰባቸውና ለጓደኞቻቸው ያላቸው ፍቅር እንዲሁም ከአምላክ ጋር የመሠረቱት ዝምድና ነው።​—ምሳሌ 15:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7