በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጆን ፎክስ እና በዘመኑ የነበረው ሁከት

ጆን ፎክስ እና በዘመኑ የነበረው ሁከት

ጆን ፎክስ እና በዘመኑ የነበረው ሁከት

ሰው ልጅ ሌሎች ከሠሩት ስህተት ይማራል ወይስ ከታሪክ ለሚያገኘው ትምህርት ጆሮ ዳባ ልበስ ይላል? ሰዎች መጽሐፉን ሲያነቡ፣ በዘመኑ ይደርስ የነበረውን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ግፍ ለመቀበል አሻፈረኝ ይላሉ በሚል ተስፋ ብዕሩን ያነሳውን የእንግሊዛዊው የጆን ፎክስን የሕይወት ታሪክ በምታነብበት ጊዜ ስለዚህ ጥያቄ አስብ።

ጆን ፎክስ በተሃድሶ ዘመን የሠራቸው የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ለበርካታ ክፍለ ዘመናት በእንግሊዝ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ጆን ፎክስ፣ አክትስ ኤንድ ሞንይመንትስ ኦቭ ዘ ቸርች የተባለውን መጽሐፉን ጽፎ ለመጨረስ 25 ዓመታት ፈጅቶበታል። አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ከእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ የዚህን መጽሐፍ ያህል በእንግሊዞች ቋንቋና ባሕል ላይ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ተጽዕኖ ያሳደረ መጽሐፍ የለም።

ሁከት የነገሠበት ዘመን

ጆን ፎክስ የተወለደው በ1516 ወይም በ1517 በቦስተን፣ እንግሊዝ ሲሆን ማርቲን ሉተር 95 የተቃውሞ ነጥቦችን ጀርመን ውስጥ ዊትንበርግ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን በር ላይ የለጠፈውም በዚሁ ወቅት እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም በሮማ ካቶሊክ እምነት ውስጥ ያደገው ፎክስ ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ያለው የተሃድሶ አራማጆች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ሥልጣንና ትምህርቶች መቃወም በጀመሩበት ዘመን ነበር።

ፎክስ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ከሌሎች ትምህርቶች በተጨማሪ ግሪክኛና ዕብራይስጥ የተማረ ሲሆን ይህም መጽሐፍ ቅዱስን መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ እንዲያነብ አስችሎታል። ፎክስ፣ አንዳንድ የካቶሊክ ትምህርቶችን መቀበል እየከበደው የመጣው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። በዚህም የተነሳ አብረውት የሚማሩ ተማሪዎች የፕሮቴስታንቶችን እምነት ሳይቀበል አልቀረም የሚል ጥርጣሬ ስላደረባቸው ጉዳዩን ለዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ሹክ አሉ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በፎክስ ላይ የቅርብ ክትትል ይደረግበት ጀመር።

ፎክስ፣ የማስተርስ ዲግሪውን በ1543 ከተቀበለ በኋላ የቅስና ማዕረግ ሊሰጠው ታስቦ ነበር። ነገር ግን ቄሶች እንዳያገቡ በሚከለክለው ድንጋጌ ስላልተስማማ ቅስናውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ይህን እርምጃ መውሰዱ አቋሙ ይፋ እንዲወጣ አደረገ። ፎክስ፣ በመናፍቅነት በመጠርጠሩ በ1545 ዩኒቨርሲቲውን በገዛ ፈቃዱ ለቀቀ፤ በዚያ ዘመን፣ መናፍቅ እንደሆነ በማስረጃ የተረጋገጠበት ሰው የሞት ፍርድ ሊፈረድበት ይችል ነበር። ለከፍተኛ ደረጃ ሊያበቃው ይችል የነበረውን የዩኒቨርሲቲ ሥራውን ትቶ ዋርዊክሻየር ውስጥ በምትገኘው ስትራትፎርድ አፖን ኤቨን በተባለች ከተማ አቅራቢያ የሚኖር አንድን ቤተሰብ በግል ማስተማር ጀመረ። በዚያም አግነስ ራንዳል የተባለች ሴት አገባ።

አግነስ፣ አሥርቱን ትእዛዛትና አባታችን ሆይ የሚለውን የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ለልጆቿ ስላስተማረች በኮቨንተሪ ከተማ አቅራቢያ ትኖር ስለነበረችው ስሚዝ የተባለች መበለት ለፎክስ ነገረችው። ይህች ሴት ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረችው በላቲን ሳይሆን በእንግሊዝኛ ነበር። ይህ ድርጊቷ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ እሷና ተመሳሳይ ክስ የቀረበባቸው ሌሎች ስድስት ወንዶች ግንድ ላይ ታስረው በእሳት ተቃጥለው ነበር። ይህ ዓይን ያወጣ ግፍ ሕዝቡን በጣም ስላስቆጣው፣ የአካባቢው ጳጳስ ሰዎቹ የተቃጠሉት በዓርብ ዕለትና በሌሎች የጾም ቀናት ሥጋ በመብላት “የከፋ ወንጀል” ስለሠሩ ነው ብለው አስወሩ።

እነዚህ ሰማዕታት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በእንግሊዝኛ ሊያውቁ የቻሉት እንዴት ነው? ይህ ከመሆኑ ከ150 ዓመታት በፊት ጆን ዊክሊፍ የቤተ ክርስቲያን ተቃውሞ ሳይበግረው መጽሐፍ ቅዱስን ከላቲን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሞ ነበር፤ በተጨማሪም ሎላርድ ተብለው የሚጠሩ ተጓዥ ሰባኪዎችን አሠልጥኖ ነበር። * እነዚህ ሰባኪዎች በእጅ የተጻፉ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ይዘው በመዘዋወር ለሰዎች ያነቡ ነበር። በዚህ ምክንያት የአገሪቱ ፓርላማ እንቅስቃሴያቸውን ለማስቆም ሞከረ። በመሆኑም በ1401 መናፍቃንን የማሰርና የማሠቃየት አልፎ ተርፎም ግንድ ላይ አስሮ የማቃጠል ሥልጣን ለጳጳሳቱ የሚሰጥ ሕግ አወጣ።

ፎክስ፣ እንዳይታሰር በመፍራቱ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ለንደን ሄደ፤ በዚያም ከትንሽ ጊዜ በኋላ የፕሮቴስታንቶችን አቋም ማራመድ ጀመረ። ለንደን እያለ በጀርመን የተሃድሶ አራማጆች የተዘጋጁ ትራክቶችን ወደ እንግሊዝኛ የተረጎመ ሲሆን በላቲን ቋንቋ የተጻፉ ሌሎች ትራክቶችንም ተርጉሟል። እሱ ራሱም የተወሰኑ ትራክቶችን አዘጋጅቷል።

በተጨማሪም ፎክስ፣ በእንግሊዝ የሚኖሩ የሎላርዶችን ታሪክ ማጠናቀር ጀመረ፤ ከዚያም ይህን ሥራውን በ1554 ጨረሰ። በላቲን ቋንቋ የተዘጋጀውና 212 ቅጠሎች ያሉት ይህ አነስተኛ መጽሐፍ ዛሬ የፈረንሳይ ከተማ በሆነችው በስትራስቡርግ ታተመ። ይህ እትም አክትስ ኤንድ ሞንይመንትስ ኦቭ ዘ ቸርች የተባለው መጽሐፉ የመጀመሪያ ክፍል ነው ማለት ይቻላል። ከአምስት ዓመት በኋላ በዚህ መጽሐፍ ላይ ተጨማሪ ነገሮችን በማከል 750 ትላልቅ ገጾች ያሉት ጥራዝ እንዲሆን አደረገ።

አለመቻቻል ያስከተለው አስከፊ መዘዝ

በአውሮፓ በተካሄደው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ሳቢያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ተጨፍጭፈዋል። አክራሪ ካቶሊክ የነበረችውና ነፍሰ በላ የሚል ስም ያተረፈችው ሜሪ፣ በ1553 የእንግሊዝ ንግሥት ሆነች። የእንግሊዝ ፓርላማ ከሮም ጋር ያለውን ግንኙነት በ1534 ሙሉ በሙሉ አቋርጦ ስለነበረ ንግሥቲቷ እንግሊዝ እንደገና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሥልጣን ሥር እንድትሆን ለማድረግ ቆርጣ ተነስታ ነበር። በአምስት ዓመት የግዛት ዘመኗ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ 300 የሚያክሉ ወንዶችና ሴቶች መናፍቃን ናቸው በሚል እንዲቃጠሉ ተደርጓል። ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ በእስር ቤት እንዳሉ ሞተዋል።

ሜሪ ከነገሠች ብዙም ሳይቆይ ፎክስ፣ ስዊዘርላንድ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ባዝል ከተማ ቤተሰቡን ይዞ በመሄዱ በወቅቱ ከነበረው እልቂት ሊተርፍ ችሏል። ፕሮቴስታንት የሆነችው የሜሪ እህት ኤልሳቤጥ ከነገሠች ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም በ1559 ከሌሎች ስደተኞች ጋር ወደ እንግሊዝ ተመለሰ። ኤልሳቤጥ በዚያው ዓመት አክት ኦቭ ሱፕሬመሲ * የተባለውን በቤተ ክርስቲያን ላይ የበላይ ገዥ እንድትሆን ሥልጣን የሚሰጣትን ሕግ እንደገና እንዲጸድቅ አደረገች። በአጸፋው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓየስ አምስተኛ በ1570 ኤልሳቤጥን አወገዟት። ብዙም ሳይቆይ፣ ፕሮቴስታንት የሆነችው ንግሥት ኤልሳቤጥን ለመግደል የተደረገውን እቅድ ጨምሮ አንዳንድ አገሮች ከአገሬው ሰዎች ጋር በመመሳጠር በእንግሊዝ ላይ ሴራ መሸረባቸው ተደረሰበት። በዚህ ምክንያት በመቶ የሚቆጠሩ ካቶሊኮች በአገር መክዳት ወንጀል ተከስሰው በኤልሳቤጥ ትእዛዝ ተገደሉ።

በእርግጥም፣ የሕዝበ ክርስትና ክፍል የሆኑት ካቶሊኮች እና ፕሮቴስታንቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች በጣም ርቀዋል! ኢየሱስ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” ሲል አስተምሮ ነበር። (ማቴዎስ 5:44) ካቶሊኮችም ሆኑ ፕሮቴስታንቶች ይህን በጣም ግልጽ የሆነ መመሪያ ባለመከተላቸው አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው በክርስትና ላይ ብዙ ነቀፋ አምጥተዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በአስመሳይ ክርስቲያኖች ምክንያት “የእውነት መንገድ ይሰደባል” በማለት ጽፏል።—2 ጴጥሮስ 2:1, 2

ፎክስ ሥራውን አጠናቀቀ

ፎክስ ወደ አገሩ እንደተመለሰ ሰፋ ባለ ሁኔታ ዘገባዎችን ማጠናቀር ጀመረ፤ አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ዘገባዎች ሲያነቡ ታሪኮቹ በእርግጥ የተፈጸሙ ነገሮች እንደሆኑ ከራሳቸው ሕይወት መመሥከር ይችሉ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በ1563 የታተመው የዚህ መጽሐፍ የእንግሊዝኛ ቅጂ 1,800 የሚሆኑ ገጾችና በእንጨት ላይ የተቀረጹ ምስሎችን በመጠቀም የተሠሩ በርከት ያሉ ሥዕላዊ መግለጫዎችን የያዘ ሲሆን በወቅቱ ከፍተኛ ሽያጭ ያገኘ መጽሐፍ ሆኖ ነበር።

ይህ መጽሐፍ ከሰባት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ታተመ። በሁለት ጥራዞች የተዘጋጀው ሁለተኛው እትም ከ2,300 የሚበልጡ ገጾችና 153 ሥዕላዊ መግለጫዎች ነበሩት። በሚቀጥለው ዓመት የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን፣ ሠራተኞችና እንግዶች መጽሐፉን እንዲያነቡት በማሰብ በሁሉም ካቴድራሎችና በእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ቤት ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጎን የፎክስ መጽሐፍ አንድ ቅጂ እንዲቀመጥ አዋጅ አወጣች። ብዙም ሳይቆይ ትናንሽ አብያተ ክርስቲያናትም ይህን ምሳሌ ተከተሉ። ማንበብ የማይችሉ ሰዎች እንኳ በቀላሉ በአእምሮ ውስጥ የሚቀረጹትን ሥዕላዊ መግለጫዎች በመመልከት ከመጽሐፉ ጥቅም ማግኘት ይችሉ ነበር።

መጽሐፉ በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት ባገኘበት በዚህ ወቅት ፎክስ ከሮም ቤተ ክርስቲያን መገንጠል ብቻውን በቂ አይደለም የሚል አቋም ከነበራቸው ፒዩሪታኖች ከሚባሉ ፕሮቴስታንቶች ጋር መተባበር ጀምሮ ነበር። ፒዩሪታኖች ማንኛውም የካቶሊክ ርዝራዥ ፈጽሞ መወገድ ይኖርበታል ብለው ያስተምሩ ነበር፤ ይህ አቋማቸው በርካታ የካቶሊክ ልማዶችንና ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ይዛ ከቀጠለችው የእንግሊዝ ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ጋር እስከ መጋጨት ያደረሳቸው መሆኑ የሚያስደንቅ ነው።

ጆን ፎክስ ሁከት በነገሠበት በእሱ ዘመን የተፈጸሙትን በርካታ ሃይማኖታዊ ግፎች በሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ አማካኝነት በማጋለጡ ሰዎች በእንግሊዝ ውስጥ ለሃይማኖትና ለፖለቲካ ባላቸው አመለካከት ላይ ለበርካታ ክፍለ ዘመናት የቆየ ተጽዕኖ አሳድሯል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 በነሐሴ 1, 1980 የመጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “ሎላርዶች፣ ደፋር የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.14 በዲ ኤች ሞንትጎሜሪ የተዘጋጀው ዘ ሊዲንግ ፋክትስ ኦቭ ኢንግሊሽ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ ፓርላማው በ1534 አክት ኦቭ ሱፕሬመሲን ማለትም “ለንጉሥ ሄንሪ ያለ አንዳች ገደብ የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ራስ የመሆን ሥልጣን የሚሰጠውን ሕግ በማውጣት ከዚህ በፊት እንደ አገር መክዳት የሚቆጠረውን ድርጊት ዋጋ ቢስ እንዲሆን አድርጎታል። ንጉሡ ይህንን ሕግ በፊርማው በማጽደቅ ለአንድ ሺህ ዓመት ጸንቶ የቆየውን ደንብ ሽሮ እንግሊዝ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሥልጣን ነፃ የሆነች የራሷ ቤተ ክርስቲያን ያላት አገር እንድትሆን አድርጓል።”

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የፎክስ መጽሐፈ ሰማዕታት

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተሃድሶ እንቅስቃሴዎችን መቃወሟን እየገፋችበት ስትሄድ እንደ ዦ ክረስፐ ያሉ በአውሮፓ የሚገኙ የሰማዕታት ታሪክ ጸሐፊዎች በየአገሮቻቸው በሃይማኖት ስም ስለሚፈጸመው ስደትና ግድያ በዝርዝር መጻፍ ጀመሩ። * በዚህ ምክንያት አክትስ ኤንድ ሞንይመንትስ ኦቭ ዘ ቸርች የተባለው መጽሐፍ የፎክስ መጽሐፈ ሰማዕታት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በኋላ ላይ ደግሞ የታረሙና አጠር ተደርገው የተዘጋጁ እትሞች እየወጡ ሲመጡ ፎክስ የመረጠው ርዕስ ቀርቶ “የፎክስ መጽሐፈ ሰማዕታት” በሚለው ስያሜ ተተካ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.26 በዚህ መጽሔት የመጋቢት 2011 እትም ላይ የወጣውን “የዦ ክረስፐ መጽሐፈ ሰማዕታት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[የሥዕል ምንጭ]

© Classic Vision/age fotostock

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጆን ዊክሊፍ ሎላርድ የሚባሉ ተጓዥ ሰባኪዎችን ልኳል

[የሥዕል ምንጭ]

From the book The Church of England: A History for the People, 1905, Vol. II

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

From Foxe’s Book of Martyrs