የጴጥሮስ ሁለተኛው ደብዳቤ 2:1-22

  • “ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ” (1-3)

  • ሐሰተኛ አስተማሪዎች ፍርድ ይጠብቃቸዋል (4-10ሀ)

    • ወደ እንጦሮጦስ የተጣሉ መላእክት (4)

    • የጥፋት ውኃ፤ ሰዶምና ገሞራ (5-7)

  • ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሚያሳዩት ባሕርይ (10ለ-22)

2  ይሁን እንጂ በሕዝቡ መካከል ሐሰተኛ ነቢያት እንደነበሩ ሁሉ በእናንተም መካከል ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ።+ እነዚህ ሰዎች ጥፋት የሚያስከትል ኑፋቄ በስውር ያስገባሉ፤ የዋጃቸውን+ ጌታ እንኳ ሳይቀር ክደው በራሳቸው ላይ ፈጣን ጥፋት ያመጣሉ።  በተጨማሪም ብዙዎች እነሱ በማንአለብኝነት የሚፈጽሙትን ድርጊት* ይፈጽማሉ፤+ በዚህም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል።+  እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች አስመሳይ ቃላት በመናገር እናንተን በስግብግብነት ይበዘብዟችኋል። ሆኖም ከብዙ ዘመን በፊት የተበየነባቸው ፍርድ+ አይዘገይም፤ ጥፋት እንደሚደርስባቸውም ጥርጥር የለውም።*+  ደግሞም አምላክ ኃጢአት የሠሩትን መላእክት ከመቅጣት ወደኋላ አላለም፤+ ይልቁንም በድቅድቅ ጨለማ አስሮ* በማስቀመጥ ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ+ ወደ እንጦሮጦስ* ጣላቸው።+  እንዲሁም የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን+ ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ+ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ+ የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም።+  ደግሞም ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆኑ+ የሰዶምና የገሞራ ከተሞችን አመድ በማድረግ ፈርዶባቸዋል።+  ሆኖም ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በማንአለብኝነት በሚፈጽሙት ድርጊት* እጅግ እየተሳቀቀ ይኖር የነበረውን ጻድቁን ሎጥን አድኖታል።+  ይህ ጻድቅ ሰው ዕለት ተዕለት በመካከላቸው ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው መረን የለቀቀ ድርጊታቸው ጻድቅ ነፍሱን* ያስጨንቅ ነበር።  በመሆኑም ይሖዋ፣* ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድንና+ ዓመፀኞችን ደግሞ በፍርድ ቀን ለሚደርስባቸው ጥፋት እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆይ ያውቃል።+ 10  በተለይ ደግሞ ሰዎችን ለማርከስ+ ሲሉ ከእነሱ ጋር የፆታ ብልግና ለመፈጸም የሚመኙትንና ሥልጣን ያላቸውን የሚንቁትን*+ ለፍርድ ጠብቆ ያቆያቸዋል። ደፋሮችና በራሳቸው የሚመሩ ከመሆናቸውም በላይ የተከበሩትን ሲሳደቡ አይፈሩም። 11  ይሁንና መላእክት፣ ከእነሱ የላቀ ብርታትና ኃይል ያላቸው ቢሆንም ለይሖዋ* ካላቸው አክብሮት የተነሳ* ሐሰተኛ አስተማሪዎቹን በመስደብ አልነቀፏቸውም።+ 12  እነዚህ ሰዎች ግን ተይዘው ለመገደል እንደተወለዱ፣ በደመ ነፍስ እንደሚንቀሳቀሱ አእምሮ የሌላቸው እንስሳት ናቸው፤ በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ።+ በሚከተሉት የጥፋት ጎዳና የተነሳ ለጥፋት ይዳረጋሉ። 13  በሠሩት ክፉ ድርጊት የተነሳ በራሳቸው ላይ ክፉ ነገር በማምጣት ብድራታቸውን ይቀበላሉ። በጠራራ ፀሐይ የሥጋ ፍላጎታቸውን ማርካትን እንደ ደስታ ይቆጥሩታል።+ እነዚህ ሰዎች እንደ ቆሻሻና እድፍ ናቸው፤ ከእናንተ ጋር በግብዣ ላይ ሲገኙ አታላይ በሆኑ ትምህርቶቻቸው ሌሎችን በማሳት እጅግ ይደሰታሉ።+ 14  አመንዝራ ዓይን+ ያላቸው በመሆኑ ኃጢአት ከመሥራት መታቀብ አይችሉም፤ ጸንተው ያልቆሙትንም* ያማልላሉ። መስገብገብ የለመደ ልብ አላቸው። የተረገሙ ልጆች ናቸው። 15  ቀናውን መንገድ ትተው በተሳሳተ ጎዳና ሄደዋል። ለጥቅም ሲል ክፉ ድርጊት መፈጸም የመረጠውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለዋል።+ 16  በለዓም ግን ትክክለኛውን መመሪያ በመጣሱ ተወቅሷል።+ መናገር የማትችል አህያ እንደ ሰው ተናግራ የነቢዩን የእብደት አካሄድ ለመግታት ሞከረች።+ 17  እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በአውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማም ይጠብቃቸዋል።+ 18  በከንቱ ጉራ ይነዛሉ። በተሳሳተ ጎዳና ከሚመላለሱት መካከል በቅርቡ ያመለጡትን ሰዎች የሥጋ ምኞቶቻቸውን በመቀስቀስና+ ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት በመፈጸም* ያማልሏቸዋል።+ 19  እነሱ ራሳቸው የመጥፎ ሥነ ምግባር ባሪያዎች ሆነው ሳሉ ነፃ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤+ ማንም ሰው በሌላ ሰው ከተሸነፈ የዚያ ሰው ባሪያ ይሆናልና።*+ 20  ስለ ጌታችንና አዳኛችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባገኙት ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ+ ተመልሰው በዚሁ ነገር ከተጠመዱና ከተሸነፉ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ እንደሚሆንባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።+ 21  የጽድቅን መንገድ በትክክል ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደኋላ ከሚሉ ቀድሞውኑ ባያውቁት ይሻላቸው ነበር።+ 22  “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ የታጠበች አሳማም ተመልሳ ጭቃ ላይ ትንከባለላለች”+ የሚለው እውነተኛ ምሳሌ በእነሱ ላይ ተፈጽሟል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሚፈጽሙትን እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” እዚህ ላይ የገባው አሴልጊያ የሚለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።”
“ጉድጓድ ውስጥ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ጌትነትን የሚንቁትን።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በይሖዋ ፊት።”
ወይም “ጸንተው ያልቆሙትን ነፍሳትም።”
ወይም “እፍረተ ቢስነት በሚንጸባረቅበት ድርጊት።” እዚህ ላይ የገባው አሴልጊያ የሚለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ለተሸነፈለት ነገር ሁሉ ባሪያ ነውና።”