በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

አሁን የምንኖረው አምላክ ያሰበልንን ዓይነት ሕይወት አይደለም። ምድር ለፈጣሪ ለመገዛት ፈቃደኛ በሆኑ፣ የእሱን አመራር በሚቀበሉ እና ግሩም ባሕርያቱን በሚያንጸባርቁ ሰዎች ልትሞላ ይገባ ነበር። የአምላክ ዓላማ የምድር ነዋሪዎች ልጆች እያሳደጉና አዳዲስ ነገሮችን እየተማሩ እንዲሁም ገነትን እያስፋፉ በደስታ እንዲኖሩ ነበር።

አምላክ ወደፊት እሱ ያሰበልንን ዓይነት ሕይወት እንደምንመራ ቃል ገብቷል

  • “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።”—መዝሙር 46:9

  • “ምድርን እያጠፉ ያሉትን የምታጠፋበት የተወሰነው ጊዜ መጣ።”—ራእይ 11:18

  • “ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24

  • “የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።”—ኢሳይያስ 65:22

እነዚህ ትንቢቶች የሚፈጸሙት እንዴት ነው? አምላክ ልጁን ኢየሱስን ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል፤ ኢየሱስ የሚያስተዳድረው መንግሥት ከሰማይ ሆኖ ምድርን የሚገዛ ፍጹም መንግሥት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መስተዳድር የአምላክ መንግሥት በማለት ይጠራዋል። (ዳንኤል 2:44) የአምላክ ቃል ስለ ኢየሱስ ሲናገር “አምላክም . . . ዙፋን ይሰጠዋል፤ . . . ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል” ይላል።—ሉቃስ 1:32, 33

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ብዙ ተአምራትን ሠርቷል፤ ይህም ወደፊት ምድርን ሲገዛ የሰዎችን ሕይወት ከአሁኑ እጅግ የተሻለ እንደሚያደርግ ያሳያል።

ኢየሱስ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንደሚያመጣ በተግባር አሳይቷል

  • ሁሉንም ዓይነት ሕመም ፈውሷል፤ ይህም የሰው ልጆችን ከበሽታ እንደሚገላግላቸው ያሳያል።—ማቴዎስ 9:35

  • ባሕሩን ጸጥ አሰኝቷል፤ ይህም የተፈጥሮ ኃይሎችን በመቆጣጠር ለሰዎች ጥበቃ እንደሚያደርግ ያሳያል።—ማርቆስ 4:36-39

  • በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግቧል፤ ይህም የሰው ልጆችን መሠረታዊ ፍላጎቶች እንደሚያሟላ ያሳያል።—ማርቆስ 6:41-44

  • በአንድ ሠርግ ላይ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ቀይሯል፤ ይህም የሰው ልጆች ሕይወት አስደሳች እንዲሆን እንደሚያደርግ ያሳያል።—ዮሐንስ 2:7-11

አምላክ ለሚወዱት ሰዎች ያዘጋጀውን ሕይወት መውረስ የምትችለው እንዴት ነው? ወደ ሕይወት የሚወስደውን ‘መንገድ’ ማግኘት ያስፈልግሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ መንገድ ሲናገር “መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ይላል።—ማቴዎስ 7:14

ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ማግኘት

የሕይወት መንገድ ምንድን ነው? አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ ልትሄድበትም በሚገባህ መንገድ የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።” (ኢሳይያስ 48:17) በዚህ መንገድ ላይ መሄድ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ያስገኛል።

ኢየሱስ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” ብሏል። (ዮሐንስ 14:6) ኢየሱስ ያስተማራቸውን እውነቶች በማመንና እሱ የተወውን ምሳሌ በመከተል ወደ አምላክ መቅረብና የተሻለ ሕይወት መምራት እንችላለን።

የሕይወትን መንገድ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? በዓለም ላይ ብዙ ሃይማኖቶች አሉ፤ ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው።” (ማቴዎስ 7:21) በተጨማሪም ኢየሱስ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 7:16) መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ እንድትችል ይረዳሃል።—ዮሐንስ 17:17

በሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ የምትችለው እንዴት ነው? የሕይወት ምንጭ የሆነውን አምላክ ከማወቅ ይጀምራል፤ ይኸውም ማንነቱን፣ ስሙን፣ ባሕርያቱን፣ ምን እያደረገ እንዳለ እንዲሁም ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ ይኖርብሃል። *

አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው እንዲሠሩ፣ እንዲበሉ፣ እንዲዝናኑና ልጆች እንዲያሳድጉ ብቻ አይደለም። ከዚህ ባለፈ ስለ ፈጣሪያችን ማወቅና ወዳጆቹ መሆን እንችላለን። የእሱን ፈቃድ በማድረግ እንደምንወደው እናሳያለን። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተን . . . ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ዮሐንስ 17:3

አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት “የሚጠቅምህን ነገር” ያስተምርሃል።—ኢሳይያስ 48:17

የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ

ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማስደሰት አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። እንዲህ ማድረግ ከባድ መስሎ ሊታይህ ይችላል። ሆኖም በሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ ስትጀምር የተሻለ ሕይወት መምራት ትችላለህ፤ ደግሞም ይህ ጉዞ እንደ ማንኛውም ጉዞ የመጀመሪያውን እርምጃ ከመውሰድ ይጀምራል። ስለ አምላክ ለሚነሱ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ከፈለግክ የይሖዋ ምሥክሮች በሚመችህ ሰዓትና ቦታ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ሊያስተምሩህ ፈቃደኞች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት www.isa4310.com/am የተባለውን ድረ ገጽ መጠቀም ትችላለህ።