በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመን ያለፈበት ወይስ ከዘመኑ የቀደመ?

ዘመን ያለፈበት ወይስ ከዘመኑ የቀደመ?

ሳይንስ

መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም ከሳይንስ አንጻር በዘመኑ ያልተደረሰባቸውን መረጃዎች ይዟል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ግዑዙ አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ አለው?

በአንድ ወቅት ታዋቂ የሳይንስ ሊቃውንት ‘አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ የለውም’ ብለው ያምኑ ነበር። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የሳይንስ ሊቃውንት፣ አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለው ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ይህን በግልጽ ተናግሯል።—ዘፍጥረት 1:1

ምድር ምን ዓይነት ቅርጽ አላት?

በጥንት ዘመን ብዙ ሰዎች ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ያስቡ ነበር። በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የግሪክ የሳይንስ ሊቃውንት ምድር የሉል ዓይነት ቅርጽ እንዳላት (ድቡልቡል እንደሆነች) ገለጹ። ይሁን እንጂ ሊቃውንቱ ይህን ከማለታቸው ከዘመናት በፊት ይኸውም በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ኢሳይያስ የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ‘ክብ ስለሆነችው ምድር’ ተናግሮ ነበር፤ ኢሳይያስ የተጠቀመበት ቃል “ድቡልቡል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።—ኢሳይያስ 40:22 የግርጌ ማስታወሻ

ሰማያት በጊዜ ሂደት ሊበላሹ ወይም ሊያረጁ ይችላሉ?

በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ግሪካዊው የሳይንስ ሊቅ አርስቶትል፣ በጊዜ ሂደት የሚበላሹት በምድር ላይ ያሉ ነገሮች ብቻ እንደሆኑና በከዋክብት የተሞሉት ሰማያት ግን ፈጽሞ ሊለወጡ ወይም ሊያረጁ እንደማይችሉ አስተምሮ ነበር። ይህ አመለካከት ለብዙ ዘመናት ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ በ19ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የሳይንስ ሊቃውንት ኤንትሮፒ የተባለውን ጽንሰ ሐሳብ አመጡ። በዚህ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት በሰማይም ይሁን በምድር ያለ ማንኛውም ቁስ አካል በጊዜ ሂደት ይበላሻል ወይም ያረጃል። ይህን ሐሳብ ከሚያራምዱ የሳይንስ ሊቃውንት አንዱ የሆኑት ዊልያም ቶምሰን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማያትና ምድር ሲገልጽ “ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ” እንደሚል ተናግረዋል። (መዝሙር 102:25, 26) አምላክ፣ በጊዜ ሂደት የሚመጣው እንዲህ ዓይነቱ መበላሸት የፍጥረት ሥራዎቹን እንዳያጠፋቸው ማድረግ እንደሚችል ቶምሰን ያምኑ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስም የሚያስተምረው ይህንን ነው።—መክብብ 1:4

እንደ ምድራችን ያሉትን ፕላኔቶች ደግፎ ያቆማቸው ምንድን ነው?

አርስቶትል በሰማይ ያሉ አካላት በሙሉ እንደ መስታወት ባሉ ተደራራቢ ሉሎች ውስጥ እንደሚገኙ አስተምሯል፤ እያንዳንዱ የሰማይ አካል የታቀፈበት ሉል በሌላ ሉል ውስጥ እንደታቀፈና ምድር የምትገኘው በማዕከላዊው ክፍል ውስጥ እንደሆነ ተናግሯል። በ18ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ላይ ግን የሳይንስ ሊቃውንት ከዋክብትና ፕላኔቶች በሕዋ ውስጥ ያሉት ያለምንም ድጋፍ ተንጠልጥለው ሊሆን እንደሚችል አምነው መቀበል ጀምሩ። የሚገርመው በ15ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተጻፈው የኢዮብ መጽሐፍ፣ ፈጣሪ ምድርን “ያለምንም ነገር አንጠልጥሏል” ይላል።—ኢዮብ 26:7

ሕክምና

መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና ማስተማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም ከጤና አንጻር ከዘመኑ የቀደሙ መመሪያዎችን ይዟል።

የታመሙ ሰዎች ከጤነኞች ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረግ

የሙሴ ሕግ የሥጋ ደዌ የያዛቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ያዝዝ ነበር። ሆኖም ሐኪሞች በመካከለኛው ዘመን ወረርሽኝ እስከተከሰተበት ጊዜ ድረስ ይህን መመሪያ ተግባራዊ የማድረግን ጥቅም አልተገነዘቡም፤ ይህ ዘዴ ውጤታማ መሆኑ በዘመናችንም ቢሆን ተቀባይነት አለው።—ዘሌዋውያን ምዕራፍ 13 እና 14

አስከሬን ከነኩ በኋላ መታጠብ

እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ ሐኪሞች አስከሬን ከነኩ በኋላ ብዙውን ጊዜ እጃቸውን ሳይታጠቡ ሌሎች ሕመምተኞችን ያክሙ ነበር። ይህ ልማድ ለብዙ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። ሆኖም የሙሴ ሕግ ሬሳ የነካ ማንኛውም ሰው የረከሰ እንደሆነ ይናገራል። እንዲያውም ሕጉ አስከሬን በመንካቱ ምክንያት የረከሰ ሰው ለመንጻት በውኃ መታጠብና ልብሶቹን ማጠብ እንዳለበት ያዝዝ ነበር። እነዚህ ሃይማኖታዊ ደንቦች ከጤና አንጻር ጥቅም እንደነበራቸው ምንም ጥያቄ የለውም።—ዘኁልቁ 19:11, 19

ቆሻሻን ማስወገድ

በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሕፃናት በተቅማጥ ሳቢያ ይሞታሉ፤ በአብዛኛው ለዚህ ዓይነቱ ሕመም የሚጋለጡት በአግባቡ እንዲወገድ ካልተደረገ የሰው ሰገራ ጋር በሚፈጠር ንክኪ ምክንያት ነው። የሙሴ ሕግ፣ ሕዝቡ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ርቀው መጸዳዳት እንዳለባቸውና ሰገራውን ቆፍረው ሊቀብሩት እንደሚገባ ያዝዛል።—ዘዳግም 23:13

ሕፃናት የሚገረዙበት ጊዜ

የአምላክ ሕግ ወንድ ልጅ በተወለደ በስምንተኛው ቀን መገረዝ እንዳለበት አዟል። (ዘሌዋውያን 12:3) አራስ ሕፃናት ሰውነታቸው ሲቆረጥ፣ ደማቸው ቶሎ መቆም የሚችልበት ደረጃ ላይ የሚደርሰው ከተወለዱ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ አንጻር ዘመናዊ ሕክምና ባልነበረበት በጥንት ዘመን አንድ ሕፃን ከመገረዙ በፊት አንድ ሳምንት እንዲያልፍ የሚያዘው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጥበብ ያዘለ እንደሆነ መመልከት ይቻላል።

ስሜትና አካላዊ ጤንነት ያላቸው ዝምድና

የሕክምና ተመራማሪዎችና የሳይንስ ሊቃውንት እንደ ደስታ፣ ተስፋ፣ አመስጋኝነትና ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን የመሳሰሉት ነገሮች ለጤና ጠቃሚ እንደሆኑ ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው፤ የተደቆሰ መንፈስ ግን ኃይል ያሟጥጣል” ይላል።—ምሳሌ 17:22