በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 11

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

1. የሰው ልጆች መመሪያ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ላለማድረግ እንድንጠነቀቅ የሚረዱን እንዴት ነው?—መዝሙር 36:9

ፈጣሪያችን ከእኛ ይበልጥ ጥበበኛ ነው። አፍቃሪ አባት በመሆኑ ስለ እኛ ያስባል። ከዚህም ሌላ ከእሱ አመራር ውጪ ራሳችንን እንድንመራ አድርጎ አልፈጠረንም። (ኤርምያስ 10:23) በመሆኑም አንድ ትንሽ ልጅ የወላጆቹን መመሪያ ማግኘት እንደሚያስፈልገው ሁሉ የሰው ልጆች በሙሉ ከአምላክ መመሪያ ማግኘት ያስፈልገናል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ የሚያስፈልገንን መመሪያ ይሰጡናል፤ በመሆኑም አምላክ ለእኛ እንደላከልን ስጦታ ናቸው።​—2 ጢሞቴዎስ 3:16ን አንብብ።

የይሖዋ አምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የሚሻለው የሕይወት መንገድ የቱ እንደሆነ የሚያስተምሩን ከመሆኑም በላይ ወደፊት ዘላለማዊ በረከቶችን ማጨድ የምንችልበትን መንገድ ያሳዩናል። የፈጠረን አምላክ በመሆኑ ለሚሰጠን መመሪያዎች አመስጋኝ መሆናችንና በእነሱ መመራታችን ተገቢ እንደሆነ ጥያቄ የለውም።​—መዝሙር 19:7, 11ን እና ራእይ 4:11ን አንብብ።

2. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ አጠቃላይ ወይም መሠረታዊ የሆኑ እውነቶች ናቸው። በሌላ በኩል ግን ሕግ ዝርዝር የሆኑ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። (ዘዳግም 22:8) አንድ መሠረታዊ ሥርዓት ከአንድ ሁኔታ ጋር በተያያዘ እንዴት እንደሚሠራ ለመረዳት እንድንችል የመለየት ወይም የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም ያስፈልገናል። (ምሳሌ 2:10-12) ለምሳሌ፣ ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ቦታችን፣ በቤታችንና በጉዞ ላይ በምንሆንበት ጊዜ መመሪያ ሊሆነን ይችላል። የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ላለማድረግ እንድንጠነቀቅ ይረዳናል።​—የሐዋርያት ሥራ 17:28ን አንብብ።

3. ዋነኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

ኢየሱስ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጣቸው ሁለት መሠረታዊ ሥርዓቶች ተናግሯል። የመጀመሪያው መሠረታዊ ሥርዓት ሰዎች የተፈጠሩበትን ዓላማ የሚገልጽ ሲሆን ይህም አምላክን ማወቅ፣ መውደድና እሱን በታማኝነት ማገልገል ነው። ማንኛውንም ውሳኔ ስናደርግ የመጀመሪያውን መሠረታዊ ሥርዓት ከግምት ማስገባት ይኖርብናል። (ምሳሌ 3:6) በዚህ መሠረታዊ ሥርዓት የሚመሩ ሰዎች ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የሚችሉ ከመሆኑም ሌላ እውነተኛ ደስታና የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።​—ማቴዎስ 22:36-38ን አንብብ።

ሁለተኛው መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-7) ሰዎችን አምላክ በሚይዝበት መንገድ በመያዝ ሁለተኛውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን።​—ማቴዎስ 7:12ን እና 22:39, 40ን አንብብ።

4. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ቤተሰቦች ፍቅርና አንድነት እንዲኖራቸው ይረዷቸዋል። (ቆላስይስ 3:12-14) የአምላክ ቃል ቤተሰቦች ሊመሩበት የሚገባ ሌላ መሠረታዊ ሥርዓትም ይዟል፤ ጋብቻ ዘላቂ ጥምረት መሆን እንዳለበት የሚያስተምር ሲሆን ይህም የቤተሰቡ ደኅንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል።​—ዘፍጥረት 2:24ን አንብብ።

የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረጋችን በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የሚጠቅመን ከመሆኑም ሌላ ውስጣዊ ሰላምና አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ቀጣሪዎች ብዙውን ጊዜ የሚፈልጉት እንደ ሐቀኝነትና ታታሪነት ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩ ሠራተኞችን ነው። (ምሳሌ 10:4, 26፤ ዕብራውያን 13:18) በተጨማሪም የአምላክ ቃል በሚያስፈልጉን ነገሮች ረክተን እንድንኖርና ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ከአምላክ ጋር ላለን ወዳጅነት ትልቅ ቦታ እንድንሰጥ ያስተምረናል።​—ማቴዎስ 6:24, 25, 33ን እና 1 ጢሞቴዎስ 6:8-10ን አንብብ።

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ጤንነታችንን መጠበቅ እንድንችልም ይረዳናል። (ምሳሌ 14:30፤ 22:24, 25) ለምሳሌ፣ ከስካር እንድንርቅ የሚያዝዘውን የአምላክ ሕግ ማክበራችን ከአደጋና ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች ይጠብቀናል። (ምሳሌ 23:20) ይሖዋ የአልኮል መጠጥ እንድንጠጣ የፈቀደልን ቢሆንም ይህን በልክ እንድናደርግ ይጠብቅብናል። (መዝሙር 104:15፤ 1 ቆሮንቶስ 6:10) አምላክ ያወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ከመጥፎ ድርጊቶች ብቻ ሳይሆን ከመጥፎ ሐሳቦችም እንድንርቅ ስለሚያስተምሩን ጠቃሚ ናቸው። (መዝሙር 119:97-100) ይሁንና እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች የሚጠብቁት ጥቅም ስለሚያስገኙላቸው ብቻ አይደለም። ይህን የሚያደርጉት ይሖዋን ማክበር ስለሚፈልጉ ነው።​—ማቴዎስ 5:14-16ን አንብብ።