በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ የሚጠቀሙበት እንዴት ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ የሚጠቀሙበት እንዴት ነው?

 በመዋጮ የምናገኘውን ገንዘብ የምንጠቀምበት ድርጅታችን የሚያከናውናቸውን ሃይማኖታዊና የእርዳታ ሥራዎችን ለመደገፍ ነው። እነዚህ እንቅስቃሴዎች፣ ዋነኛው ሥራችን የሆነው ሰዎችን የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ክፍል ናቸው።—ማቴዎስ 28:19, 20

 በመዋጮ የምናገኘውን ገንዘብ ማንም ሰው ለግል ጥቅሙ እንዲያውለው ፈጽሞ አይፈቀድም። ደሞዝ የሚከፈላቸው ሽማግሌዎች ወይም ቄሶች የሉንም፤ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚሰብኩትም ተከፍሏቸው አይደለም። በቅርንጫፍ ቢሮዎቻችንም ሆነ በዋናው መሥሪያ ቤታችን የሚያገለግሉት የይሖዋ ምሥክሮች የሃይማኖታዊ ሥርዓተ ማኅበር አባላት ሲሆኑ ደሞዝ አይከፈላቸውም፤ ይህ የበላይ አካል አባላትንም ይጨምራል።

የምናከናውናቸው አንዳንድ ሥራዎች

  •   ሕትመት፦ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችንና ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን እንተረጉማለን፣ እናትማለን፣ ወደተለያዩ ቦታዎች እናጓጉዛለን እንዲሁም እናሰራጫለን፤ ጽሑፎቻችንን የምናሰራጨው ያለክፍያ ነው። በተመሳሳይም ጽሑፎቻችን jw.org በተባለው ድረ ገጻችንና JW Library በተባለው አፕሊኬሽናችን ላይ ያለክፍያ ይገኛሉ፤ ገንዘብ ለማግኘት ስንል ድረ ገጻችንና አፕሊኬሽናችን ላይ ምንም ዓይነት ማስታወቂያ እንዲወጣ አናደርግም።

  •   ግንባታ እና እድሳት፦ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ላይ ተሰብስበው አምላክን ለማወደስ የሚጠቀሙባቸውን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምልኮ ቦታዎች እንገነባለን እንዲሁም እናድሳለን። ከቅርንጫፍ ቢሮዎችና ከትርጉም ቢሮዎች ጋር በተያያዘም እንዲሁ እናደርጋለን። ይህን ሥራ በአብዛኛው የሚያከናውኑት ፈቃደኛ ሠራተኞች ናቸው፤ ይህም ወጪ ለመቀነስ ያስችለናል።

  •   አስተዳደር፦ በዋናው መሥሪያ ቤታችን፣ በቅርንጫፍ ቢሮዎችና በትርጉም ቢሮዎች ውስጥ ለሚከናወነው እንቅስቃሴ እንዲሁም ተጓዥ አገልጋዮች ለሚያከናውኑት ሥራ የሚያስፈልገው ገንዘብ የሚገኘው ለዓለም አቀፉ ሥራችን ከሚዋጣው ገንዘብ ነው።

  •   ስብከት፦ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ምሥራቹን ሲሰብኩ ወይም “የአምላክን ቃል” ሲያስተምሩ ደሞዝ አይከፈላቸውም። (2 ቆሮንቶስ 2:17) ሆኖም ሥልጠና የወሰዱና አብዛኛውን ጊዜያቸውን በስብከቱ ሥራ ላይ የሚያሳልፉ የተወሰኑ አገልጋዮች መጠነኛ ቤት ይሰጣቸዋል፤ እንዲሁም መሠረታዊ ነገሮች ይሟሉላቸዋል፤ ይህ አሠራር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ካደረጉት ጋር ተመሳሳይ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:16, 17፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:17, 18

  •   ማስተማር፦ ለትላልቅ ስብሰባዎቻችን የሚሆነው ወጪ የሚሸፈነው በመዋጮ በሚገኘው ገንዘብ ነው። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በድምፅና በቪዲዮ የተቀዱ ነገሮችን እናዘጋጃለን። ከዚህም ሌላ ሽማግሌዎችና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲወጡ የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች አሉን።

  •   በአደጋ የተጎዱትን መርዳት፦ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ምግብ፣ ውኃ እና ቤት እንዲያገኙ እናደርጋለን። እንዲህ ዓይነት እርዳታ የምንሰጠው “በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች” ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሰዎችም ጭምር ነው።—ገላትያ 6:10