በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የኖኅ እና የጥፋት ውኃው ታሪክ እውነተኛ ነው?

የኖኅ እና የጥፋት ውኃው ታሪክ እውነተኛ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የጥፋት ውኃው ዘገባ እውነተኛ ታሪክ ነው። አምላክ የጥፋት ውኃውን ያመጣው ክፉ ሰዎችን ለማጥፋት ነበር፤ ሆኖም ጥሩ ሰዎችንና እንስሳትን ለማዳን ሲል ኖኅ መርከብ እንዲሠራ አደረገ። (ዘፍጥረት 6:11-20) የጥፋት ውኃው ዘገባ እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም ይህ ታሪክ “በአምላክ መንፈስ መሪነት” የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

 እውነተኛ ታሪክ ወይስ ተረት?

 መጽሐፍ ቅዱስ ኖኅ በእርግጥ ምድር ላይ የኖረ ሰው እንደነበረና የጥፋት ውኃው ተረት ወይም አፈ ታሪክ ሳይሆን እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ ይገልጻል።

  •   የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ኖኅ በእርግጥ ምድር ላይ የኖረ ሰው እንደነበር ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን የጻፉት ዕዝራና ሉቃስ የታሪክ ምሁራን ነበሩ፤ ሁለቱም በእስራኤል ብሔር የዘር ሐረግ ውስጥ ኖኅን አካትተውታል። (1 ዜና መዋዕል 1:4፤ ሉቃስ 3:36) ወንጌል ጸሐፊዎቹ ማቴዎስና ሉቃስ፣ ኢየሱስ ስለ ኖኅና ስለ ጥፋት ውኃ የተናገረውን ሐሳብ ዘግበዋል።—ማቴዎስ 24:37-39፤ ሉቃስ 17:26, 27

     በተጨማሪም ነቢዩ ሕዝቅኤልና ሐዋርያው ጳውሎስ ኖኅ የእምነትና የጽድቅ ምሳሌ መሆኑን ጽፈዋል። (ሕዝቅኤል 14:14, 20፤ ዕብራውያን 11:7) ኖኅ በገሃዱ ዓለም ያልኖረ ሰው ቢሆን ኖሮ ምሳሌውን እንድንከተል ያበረታቱን ነበር? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የኖኅንም ሆነ የሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን ምሳሌ እንድንከተል የተበረታታነው የእነዚህ ሰዎች ታሪክ እውነተኛ ስለሆነ ነው።—ዕብራውያን 12:1፤ ያዕቆብ 5:17

  •   መጽሐፍ ቅዱስ የጥፋት ውኃውን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ ይሰጣል። ስለ ጥፋት ውኃው የሚናገረው ዘገባ እንደ ተረት “ከዕለታት አንድ ቀን” ብሎ የሚጀምር አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ከጥፋት ውኃው ጋር የተያያዙ ክስተቶች የተፈጸሙበትን ዓመት፣ ወርና ቀን ለይቶ ይጠቅሳል። (ዘፍጥረት 7:11፤ 8:4, 13, 14) ከዚህም በተጨማሪ ኖኅ የገነባውን መርከብ ልኬት በዝርዝር ይዟል። (ዘፍጥረት 6:15) እነዚህ መረጃዎች የጥፋት ውኃው ዘገባ ተረት ሳይሆን እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ ያረጋግጣሉ።

 የጥፋት ውኃው የመጣው ለምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ከጥፋት ውኃው በፊት “የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ [በዝቶ]” እንደነበር ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:5) አክሎም “ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር” ይላል፤ ይህ የሆነው ምድር በዓመፅና በፆታ ብልግና ስለተሞላች ነበር።—ዘፍጥረት 6:11፤ ይሁዳ 6, 7

 ይህ ችግር በዋነኝነት የተከሰተው ከሴቶች ጋር ግንኙነት ለመፈጸም ሲሉ ሰማይን ትተው በመጡ ክፉ መላእክት የተነሳ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እነዚህ መላእክት ኔፍሊም የተባሉ ልጆች ወለዱ፤ እነዚህ የመላእክት ልጆች በሰዎች ላይ መከራ አምጥተዋል። (ዘፍጥረት 6:1, 2, 4) በዚህ ጊዜ አምላክ ክፋትን ከምድር ላይ በማጥፋት ጥሩ ሰዎች እንዲተርፉ ለማድረግ ወሰነ።—ዘፍጥረት 6:6, 7, 17

 የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ ሰዎች አውቀው ነበር?

 አዎ። አምላክ የጥፋት ውኃ እንደሚያመጣ ለኖኅ ከነገረው በኋላ ቤተሰቡንና እንስሳቱን ለማዳን መርከብ እንዲሠራ አዘዘው። (ዘፍጥረት 6:13, 14፤ 7:1-4) ኖኅ ጥፋት እንደሚመጣ ሰዎችን ቢያስጠነቅቅም ሰዎቹ ማስጠንቀቂያውን ችላ አሉ። (2 ጴጥሮስ 2:5) መጽሐፍ ቅዱስ “የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም” ይላል።—ማቴዎስ 24:37-39

 የኖኅ መርከብ ምን ይመስል ነበር?

 መርከቡ ትልቅ ሣጥን ይመስል ነበር፤ ርዝመቱ 133 ሜትር፣ ወርዱ 22 ሜትር፣ ከፍታው ደግሞ 13 ሜትር ነበር። a መርከቡ የተሠራው ከጎፈር እንጨት ሲሆን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ቅጥራን ተለቅልቋል። መርከቡ ምድር ቤትና ሁለት ፎቆች እንዲሁም ብዙ ክፍሎች ነበሩት። በሩ በጎን በኩል ነበር፤ ከላይ ደግሞ መስኮቶች የነበሩት ይመስላል። ውኃ በቀላሉ እንዲወርድ ለማስቻል ጣሪያው አሞራ ክንፍ ተደርጎ የተሠራ ሳይሆን አይቀርም።—ዘፍጥረት 6:14-16

 ኖኅ መርከቡን ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ ወስዶበታል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ኖኅ መርከቡን ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ እንደወሰደበት አይናገርም፤ ሆኖም በርካታ አሥርተ ዓመታት ሳይፈጅበት አይቀርም። ኖኅ የመጀመሪያ ልጁን ሲወልድ 500 ዓመት አልፎት ነበር፤ የጥፋት ውኃው ሲመጣ ደግሞ 600 ዓመቱ ነበር። bዘፍጥረት 5:32፤ 7:6

 አምላክ ኖኅን መርከብ እንዲሠራ ያዘዘው ሦስቱ ልጆቹ አድገው ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ነው፤ ይህ ደግሞ 50 ወይም 60 ዓመት ወስዶ ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 6:14, 18) ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ኖኅ መርከቡን ለመሥራት 40 ወይም 50 ዓመት ወስዶበታል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።

a መጽሐፍ ቅዱስ የመርከቡን ልኬት የዘገበው በክንድ ነው። ዕብራውያን አንድ ክንድ የሚሉት 44.45 ሴንቲ ሜትር ነበር።—ዚ ኢለስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ፣ የተሻሻለ እትም፣ ክፍል 3 ገጽ 1635

b እንደ ኖኅ ያሉ ሰዎችን ዕድሜ አስመልክቶ በታኅሣሥ 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የጥንት ሰዎች በእርግጥ ረጅም ዕድሜ ኖረዋል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።