በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ዮሐንስ 1:1—“በመጀመሪያ ቃል ነበረ”

ዮሐንስ 1:1—“በመጀመሪያ ቃል ነበረ”

 “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከአምላክ ጋር ነበር፤ ቃልም አምላክ ነበር።”—ዮሐንስ 1:1 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።”—ዮሐንስ 1:1 አዲሱ መደበኛ ትርጉም a

የዮሐንስ 1:1 ትርጉም

 ይህ ጥቅስ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ስላሳለፈው ሕይወት መረጃ ይሰጠናል። (ዮሐንስ 1:14-17) “ቃል” (ግሪክኛው፣ ሆ ሎጎስ) የሚለው አገላለጽ ቁጥር 14 ላይ የገባው የማዕረግ ስም ሆኖ ነው። “ቃል” የሚለው የማዕረግ ስም ኢየሱስ የአምላክን ትእዛዝ ወይም መመሪያ ለሌሎች በማስተላለፍ ረገድ የተጫወተውን ሚና ያሳያል። ኢየሱስ ምድር ላይ ባገለገለበት ወቅትም ሆነ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ የአምላክን ቃል ለሌሎች ማሳወቁን ቀጥሏል።—ዮሐንስ 7:16፤ ራእይ 1:1

 “በመጀመሪያ” የሚለው አገላለጽ አምላክ የፍጥረት ሥራውን የጀመረበትንና ቃልን የፈጠረበትን ጊዜ ያመለክታል። ከዚያ በኋላ አምላክ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ የፈጠረው ቃልን ተጠቅሞ ነው። (ዮሐንስ 1:2, 3) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” እንደሆነና “ሌሎች ነገሮች በሙሉ . . . የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት” እንደሆነ ይናገራል።—ቆላስይስ 1:15, 16

 “ቃልም አምላክ ነበር” የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የነበረውን መለኮታዊ ወይም እንደ አምላክ ያለ ባሕርይ ያመለክታል። ኢየሱስ የአምላክ ቃል አቀባይና አምላክ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ለመፍጠር የተጠቀመበት የበኩር ልጁ ስለሆነ እንዲህ ተብሎ መገለጹ ተገቢ ነው።

የዮሐንስ 1:1 አውድ

 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዮሐንስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወትና አገልግሎት ይዘግባል። የመጀመሪያው ምዕራፍ የመክፈቻ ቁጥሮች ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ስላሳለፈው ሕይወት፣ ከአምላክ ጋር ስላለው ልዩ ዝምድና እንዲሁም በአምላክና በሰዎች መካከል ስለሚጫወተው ቁልፍ ሚና ይናገራሉ። (ዮሐንስ 1:1-18) እነዚህ ዝርዝር መረጃዎች ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች ለመረዳት ያስችሉናል።—ዮሐንስ 3:16፤ 6:38፤ 12:49, 50፤ 14:28፤ 17:5

ሰዎች ስለ ዮሐንስ 1:1 ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ የዮሐንስ 1:1 የመጨረሻ ዓረፍተ ነገር “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ተብሎ ሊተረጎም ይገባል።

 እውነታው፦ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ በዚህ መንገድ ቢተረጉሙትም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ግን ከዚህ በተለየ መንገድ ሊተረጎም እንደሚገባ ያምናሉ። ጥቅሱ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ዮሐንስ 1:1 ላይ ሁለት ጊዜ ተጠቅሰው የሚገኙት አምላክ (እግዚአብሔር) [ግሪክኛው፣ ቴኦስ] የሚሉት ቃላት የተለያየ ሰዋስዋዊ አቀማመጥ አላቸው። በመጀመሪያው ላይ ቴኦስ የሚለው ቃል ከፊቱ የግሪክኛ ጠቃሽ አመልካች የተጨመረበት ሲሆን ሁለተኛው ግን አልተጨመረበትም። ብዙ ምሁራን ከሁለተኛው ቴኦስ በፊት ጠቃሽ አመልካች አለመኖሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘ ትራንስሌተርስ ኒው ቴስታመንት ይህን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ሁለተኛው ቴኦስ (አምላክ) በዚህ መንገድ መቀመጡ ቃሉ የቅጽልነት ባሕርይ እንዲኖረው ያደርጋል፤ በመሆኑም ዓረፍተ ነገሩ ‘ቃልም መለኮት ነበር’ የሚል ትርጉም ያስተላልፋል።” b ሌሎች ምሁራን c እና የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ቴኦስ የሚለውን ቃል በሁለቱ ቦታዎች ላይ በተለያየ መንገድ ተርጉመውታል።

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ ይህ ጥቅስ ቃል፣ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር አንድ እንደሆነ ያሳያል።

 እውነታው፦ “ቃልም ከአምላክ ጋር ነበር” የሚለው ዓረፍተ ነገር ጥቅሱ ስለ ሁለት የተለያዩ አካላት እንደሚናገር ያሳያል። ቃል “ከአምላክ ጋር” እንደነበር ስለተገለጸ እሱ ራሱ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሊሆን አይችልም። የጥቅሱ አውድም ቢሆን ቃል ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እንዳልሆነ ያረጋግጣል። ዮሐንስ 1:18 “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም” ይላል። ቃልን ማለትም ኢየሱስን ግን ሰዎች አይተውታል፤ ምክንያቱም ዮሐንስ 1:14 “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ኖረ፤ [እኛም] ክብሩን አየን” በማለት ይናገራል።

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ ቃል ያልነበረበት ጊዜ የለም።

 እውነታው፦ እዚህ ጥቅስ ላይ የገባው “በመጀመሪያ” የሚለው ቃል የአምላክን “መጀመሪያ” እንደማያመለክት ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ መጀመሪያ የለውም። ይሖዋ d አምላክ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” አለ። (መዝሙር 90:1, 2) ቃል ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መጀመሪያ አለው። እሱ “ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ” ነው።—ራእይ 3:14

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ ቃልን “አምላክ” ብሎ መጥራት የብዙ አማልክት አምልኮ ተቀባይነት እንዳለው ያሳያል።

 እውነታው፦ “አምላክ” ወይም “እግዚአብሔር” ተብሎ ለሚተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ቴኦስ) አብዛኛውን ጊዜ አቻ ሆነው የሚያገለግሉት ኤል እና ኤሎሂም የሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት ናቸው፤ እነዚህ ቃላት የሚገኙት በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት መጻሕፍት ውስጥ ነው። እነዚህ የዕብራይስጥ ቃላት “ኃያል የሆነው፤ ብርቱ የሆነው” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ያላቸው ሲሆን ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ፣ ሌሎች አማልክትን፣ አልፎ ተርፎም ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (መዝሙር 82:6፤ ዮሐንስ 10:34) ቃል “ኃያል የሆነው” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ የሠራው በእሱ በኩል ነው። (ዮሐንስ 1:3) ቃል “አምላክ” መባሉ በኢሳይያስ 9:6 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር ይስማማል፤ ይህ ትንቢት አምላክ የመረጠው መሲሕ ወይም ክርስቶስ “ኃያል አምላክ” (ዕብራይስጡ፣ ኤል ጊቦር) ተብሎ እንደሚጠራ ይናገራል። ሆኖም “ሁሉን ቻይ አምላክ” (ኤል ሻዳይ፣ ዘፍጥረት 17:1፤ 35:11፤ ዘፀአት 6:3፤ ሕዝቅኤል 10:5 ላይ እንደሚገኘው ማለት ነው) ተብሎ እንደሚጠራ አይናገርም።

 መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ አማልክትን ማምለክ ተገቢ እንደሆነ አያስተምርም። ኢየሱስ ክርስቶስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” ብሏል። (ማቴዎስ 4:10) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ብዙ ‘አማልክት’ እና ብዙ ‘ጌቶች’ እንደመኖራቸው መጠን በሰማይም ሆነ በምድር አማልክት ተብለው የሚጠሩ ቢኖሩም እንኳ እኛ ግን ሁሉም ነገር ከእሱ የሆነ እኛም ለእሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ እንዲሁም ሁሉም ነገር በእሱ በኩል የሆነና እኛም በእሱ በኩል የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ።”—1 ቆሮንቶስ 8:5, 6

a የ1954 ትርጉምም ተመሳሳይ አገላለጽ ይጠቀማል።

b ዘ ትራንስሌተርስ ኒው ቴስታመንት፣ ገጽ 451

c ጄሰን ዴቪድ ቤዱን የተባሉ ምሁር እንደተናገሩት ጠቃሽ አመልካች ካልገባ አንባቢያን ቃሉን የሚረዱት ‘የመለኮትነት ባሕርይ የተላበሰ’ እንደሚል አድርገው ነው። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ዮሐንስ 1:1 ላይ የተጠቀሰው ‘ቃል’ የሚያመለክተው ብቻውን አምላክ የሆነውን አካል ሳይሆን የመለኮትነት ባሕርይ የተላበሰን አካል ነው።”—ትሩዝ ኢን ትራንስሌሽን፦ አክዩሬሲ ኤንድ ባያዝ ኢን ኢንግሊሽ ትራንስሌሽንስ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት፣ ገጽ 115፣ 122 እና 123

d ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18