በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ዮሐንስ 14:6—“እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ”

ዮሐንስ 14:6—“እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ”

 “ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ‘እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።’”—ዮሐንስ 14:6 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ ‘መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።’”—ዮሐንስ 14:6 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የዮሐንስ 14:6 ትርጉም

 አብን ማለትም ይሖዋ a አምላክን ማምለክ የሚፈልግ ሰው ኢየሱስ ያለውን ወሳኝ ሚና መገንዘብ ያስፈልገዋል።

 ‘እኔ መንገድ ነኝ።’ ኢየሱስ ተቀባይነት ባለው መልኩ ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻልበትን “መንገድ” ከፍቶልናል። ለምሳሌ ያህል ወደ አምላክ የሚጸልዩ ሰዎች በኢየሱስ ስም መጸለይ ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 16:23, 24) ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሲል መሞቱ ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ ወይም የእሱን ሞገስ መልሰው እንዲያገኙ አስችሏል። (ሮም 5:8-11) በተጨማሪም ኢየሱስ አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች በአኗኗራቸው ሊከተሉት የሚገባ አርዓያ ትቷል።—ዮሐንስ 13:15

 ‘እኔ እውነት ነኝ።’ ኢየሱስ ምንጊዜም እውነት ይናገር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። (1 ጴጥሮስ 2:22) አንድ ሰው ኢየሱስን በማዳመጥ ስለ አምላክ እውነቱን መማር ይችላል። (ዮሐንስ 8:31, 32) በተጨማሪም ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንዲፈጸሙ ስላደረገ “እውነት” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ አምላክ የገባው ቃል እውን እንዲሆን አድርጓል።—ዮሐንስ 1:17፤ 2 ቆሮንቶስ 1:19, 20፤ ቆላስይስ 2:16, 17

 ‘እኔ ሕይወት ነኝ።’ ኢየሱስ በእሱ የሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16, 36) በተጨማሪም የሞቱ ሰዎችን ስለሚያስነሳ ለእነሱም “ሕይወት” ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:25

 “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ኢየሱስ የሚጫወተውን ልዩ ሚና መቀበል ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ ስም ወደ አምላክ በመጸለይ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ሥልጣን እንደሚቀበሉ ያሳያሉ። (ዮሐንስ 15:16) በተጨማሪም መዳን የሚገኘው በኢየሱስ በኩል ብቻ እንደሆነ ያምናሉ።—የሐዋርያት ሥራ 4:12፤ ፊልጵስዩስ 2:8-11

የዮሐንስ 14:6 አውድ

 ከዮሐንስ 13 እስከ 17 ያሉት ምዕራፎች ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባለው ምሽት ላይ ለ11 ታማኝ ሐዋርያቱ የሰጠውን ምክር የያዙ ናቸው። ምዕራፍ 14 ላይ ኢየሱስ ተከታዮቹን በእሱና በአባቱ እንዲያምኑ አበረታቷቸዋል፤ ከዚህም ሌላ እሱንና አባቱን እንዲወዱና እንዲታዘዙ አሳስቧቸዋል። (ዮሐንስ 14:1, 12, 15-17, 21, 23, 24) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ያለውን የቅርብ ዝምድናም ገልጾላቸዋል። (ዮሐንስ 14:10, 20, 28, 31) ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሰማይ የሚመለስ ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱን እንደማይተዋቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ዮሐንስ 14:18) በተጨማሪም “አብ በስሜ የሚልከው ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ” ከእናንተ ጋር ይሆናል ሲል ቃል ገብቶላቸዋል። (ዮሐንስ 14:25-27) ኢየሱስ በዚህና በሌሎች መንገዶች ተከታዮቹን ወደፊት ለሚያጋጥሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች አዘጋጅቷቸዋል።