በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

መክብብ 3:11—“ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው”

መክብብ 3:11—“ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው”

 “አምላክ ሁሉንም ነገር በወቅቱ ውብ አድርጎ ሠርቶታል። ደግሞም ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል፤ ይሁንና የሰው ልጆች እውነተኛው አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያከናወነውን ሥራ በምንም ዓይነት መርምረው ሊደርሱበት አይችሉም።”—መክብብ 3:11 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።”—መክብብ 3:11 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የመክብብ 3:11 ትርጉም

 “አምላክ ሁሉንም ነገር በወቅቱ ውብ አድርጎ ሠርቶታል።” እዚህ ላይ “ውብ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ከውጫዊ ውበት ያለፈ ነገርን ያመለክታል። ቃሉ “በሚገባ የተደራጀ፣” “ሥርዓታማ” ወይም “ተስማሚ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (መክብብ 3:11 የግርጌ ማስታወሻ) ውብ ከሆኑት የአምላክ ሥራዎች መካከል የፈጠራቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ፈቃዱን ዳር ለማድረስ ያከናወናቸው ነገሮች በሙሉ ይገኙበታል።—ዳንኤል 2:21፤ 2 ጴጥሮስ 3:8፤ ራእይ 4:11

 “ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል።” አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። (መዝሙር 37:29) በመሆኑም ሰዎች ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረጉ ምንም አያስገርምም። ያም ቢሆን የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ በማመፅ በራሳቸውና በዘሮቻቸው ላይ ሞት አመጡ። (ዘፍጥረት 3:17-19፤ ሮም 5:12) አምላክ ግን የሰው ልጆች ለዘላለም ለመኖር ያላቸውን ፍላጎት ጨምሮ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 145:16) ይሖዋ የሰው ልጆች እንደገና ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖራቸው ሲል ምን ዝግጅት እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ ያብራራል።—ሮም 6:23

 “የሰው ልጆች እውነተኛው አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያከናወነውን ሥራ በምንም ዓይነት መርምረው ሊደርሱበት አይችሉም።” የአምላክ ጥበብ በጣም ጥልቅና ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ “የማይደረስበት” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮም 11:33) ይሁንና አምላክ እሱን ማስደሰት ለሚፈልጉ ሰዎች ዓላማውን ለመግለጥ ፈቃደኛ ነው።—አሞጽ 3:7

የመክብብ 3:11 አውድ

 የመክብብን መጽሐፍ የጻፈው፣ አምላክ በሰጠው ጥበብ የሚታወቀውና የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞን ነው። መጽሐፉ ለሕይወት ጠቃሚ ስለሆኑና ምንም እርባና ስለሌላቸው ነገሮች የሚገልጽ ተግባራዊ ምክር ይዟል። (መክብብ 1:2, 3፤ 2:1, 17፤ 7:1፤ 12:1, 13) በምዕራፍ 3 ላይ ሰለሞን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ስለሚያጋጥሙን የተለመዱ ነገሮች ገልጿል። በርካታ ሥራዎችና እንቅስቃሴዎች ተዘርዝረዋል። (መክብብ 3:1-8, 10) ሰዎች ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል የፈለጉትን መርጠው በፈለጉት ጊዜ እንዲያከናውኑ አምላክ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። (ዘዳግም 30:19, 20፤ ኢያሱ 24:15) ሰዎች ልፋታቸው መልካም ውጤት የሚያስገኝላቸው ከአምላክ ዓላማ ጋር ተስማምተው እሱ የመደበውን “ጊዜ” ሲያከብሩ ብቻ እንደሆነ ሰለሞን ተናግሯል። “ይህ የአምላክ ስጦታ ነው” ብሏል።—መክብብ 3:1, 12, 13

 የመክብብ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።