በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | ትዳር

ትዕግሥት ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?

ትዕግሥት ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?

 “ባለትዳሮች በየቀኑ ትዕግሥታቸውን የሚፈትን ነገር ያጋጥማቸዋል። ከማግባታችሁ በፊት ትዕግሥት ያን ያህል አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ አይሰማችሁ ይሆናል፤ ሆኖም ለተሳካ ትዳር ትዕግሥት በጣም ወሳኝ ነው።”—ጆን

 ታጋሽ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

  •   ትዳር ከመሠረትን በኋላ የትዳር ጓደኛችን ድክመት ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ሊታየን ይችላል።

     “ተጋብታችሁ የተወሰነ ጊዜ ከቆያችሁ በኋላ የትዳር ጓደኛችሁ ባሉት ድክመቶች ላይ ማተኮር ትጀምሩ ይሆናል። እንዲህ ያለ አሉታዊ አመለካከት ካዳበራችሁ ደግሞ በቀላሉ ትዕግሥት ልታጡ ትችላላችሁ።”—ጀሲና

  •   ትዕግሥት ማጣት ሳናመዛዝን እንድንናገር ሊያደርገን ይችላል።

     “የተሰማኝን ነገር ቶሎ እናገራለሁ፤ እንዲያውም አንዳንዴ ከመቸኮሌ የተነሳ መናገር የሌለብኝን ነገር ልናገር እችላለሁ። ይበልጥ ታጋሽ ብሆን ኖሮ ቆም ብዬ በማሰብ አንዳንድ ነገሮችን ሳልናገር ማለፍ እችል ነበር።”—ካርመን

     መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4) ከዚህ አንጻር እርስ በርስ የሚዋደዱ ሁለት ሰዎች ምንጊዜም አንዳቸው ሌላውን በትዕግሥት እንደሚይዙ እንጠብቅ ይሆናል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆን እንዲህ ብሏል፦ “የትኛውንም ጥሩ ባሕርይ ከማዳበር ይልቅ ማጣቱ ቀላል ነው፤ ከትዕግሥት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ትዕግሥት ለማዳበር ጥረት ይጠይቃል።”

 ትዕግሥት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

  •   ትዕግሥታችንን የሚፈትን ድንገተኛ ሁኔታ ሲያጋጥመን።

     ምሳሌ፦ የትዳር ጓደኛህ ደግነት የጎደለው ነገር ተናገረች እንበል። አንተም ደግነት የጎደለው ነገር በመናገር አጸፋውን ለመመለስ ትፈተን ይሆናል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ቁጣ የሞኝ ሰው መለያ ስለሆነ ለቁጣ አትቸኩል።”—መክብብ 7:9 የግርጌ ማስታወሻ

     ትዕግሥት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው? ቆም ብለህ አስብ። መልስ ከመስጠትህ በፊት የትዳር ጓደኛህ ደግነት የጎደለው ነገር የተናገረችው ሆን ብላ አንተን ለመጉዳት ሳይሆን በሌላ ምክንያት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ፋይቲንግ ፎር ዩር ሜሬጅ የተባለው መጽሐፍ “አብዛኛውን ጊዜ ይበልጥ የሚያበሳጨን የትዳር ጓደኛችን የተናገረው ነገር ሳይሆን ለተናገረው ነገር የሰጠነው ትርጉም ነው” ይላል።

     የትዳር ጓደኛህ አንተን የሚያበሳጭ ነገር የተናገረችው ሆን ብላ ቢሆንም እንኳ አጸፋ ከመመለስ ይልቅ ትዕግሥት ማሳየትህ ችግሩ እንዳይባባስ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል” ይላል።—ምሳሌ 26:20

     “ሚስቴን እንደ ጠላቴ አድርጌ ለመመልከት ስፈተን እሷን እንድወዳት የሚያነሳሱኝን ምክንያቶች ቆም ብዬ አስባለሁ፤ ከዚያም ወዲያውኑ ለእሷ መልካም ነገር ለማድረግ እሞክራለሁ።”—ኤታን

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦

    •  የትዳር ጓደኛህ ደግነት የጎደለው ነገር ስትናገር ወይም ስታደርግ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?

    •  ሌላ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ ይበልጥ ትዕግሥት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

  •   ትዕግሥታችንን የሚፈትን ነገር በተደጋጋሚ ሲያጋጥመን።

     ምሳሌ፦ ባለቤትህ ሁልጊዜ ታረፍዳለች፤ ይህ ደግሞ ያበሳጭሃል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 3:13

     ትዕግሥት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው? ከግል ስሜትህ ይልቅ ለትዳርህ ቅድሚያ ስጥ። ‘መበሳጨቴ ወይም ስለዚህ ጉዳይ ከባለቤቴ ጋር መጨቃጨቄ በትዳሬ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። በተጨማሪም ‘ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንደምንሰናከል’ አትርሳ። (ያዕቆብ 3:2) ስለዚህ አንተም ብትሆን ማሻሻል ያለብህ ነገር ይኖራል።

     “አንዳንድ ጊዜ ከባለቤቴ ይልቅ ጓደኞቼን በትዕግሥት ማለፍ ይቀለኛል። ይህ የሚሆነው ከባለቤቴ ጋር ብዙ ጊዜ ስለማሳልፍና ድክመቶቹን ስለማይ ይመስለኛል። ግን ትዕግሥት የፍቅርና የአክብሮት መገለጫ ነው፤ ስለዚህ በትዳሬ ውስጥ ትዕግሥት ማሳየት ያስፈልገኛል።”—ኒያ

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦

    •  የትዳር ጓደኛህን ድክመቶች በትዕግሥት ታልፋለህ?

    •  ወደፊት ይበልጥ ትዕግሥት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?