በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ ሴሲሊያ አልቫሬዝ በአሥር ዓመቷ ለ17ኛ ጊዜ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ፎቶግራፏ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር፤ በስተ ቀኝ፦ ግንቦት 2019፣ ሴሲሊያ ከወላጆቿና ከታናሽ እህቷ ጋር

ነሐሴ 7, 2019
አርጀንቲና

እህት ሴሲሊያ አልቫሬዝ በ25 ዓመታት ውስጥ 43 ጊዜ ያለደም ቀዶ ሕክምና አድርጋለች

እህት ሴሲሊያ አልቫሬዝ በ25 ዓመታት ውስጥ 43 ጊዜ ያለደም ቀዶ ሕክምና አድርጋለች

በአርጀንቲና የምትኖረው እህት ሴሲሊያ አልቫሬዝ ዕድሜዋን በሙሉ ከከባድ የጤና እክሎች ጋር ስትታገል ኖራለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዶ ሕክምና የተደረገላት የ16 ቀናት ጨቅላ እያለች ነበር። ግንቦት 18, 1994 በአርጀንቲና የሚገኙ ሐኪሞች ስትወለድ ጀምሮ በአከርካሪው ላይ የነበረውን ችግር ለማስተካከል ቀዶ ሕክምና አደረጉላት። በዚያ ቀን የተደረገውን ቀዶ ሕክምና ጨምሮ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ 43 ጊዜ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል፤ አብዛኛው ቀዶ ሕክምና የተደረገላት ገና ልጅ እያለች ነው። ለመጨረሻ ጊዜ ቀዶ ሕክምና የተደረገላት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሲሆን ሕክምናው የተደረገው በግራ ዳሌዋ ላይ ነበር። ቀደም ሲል እንደተደረጉላት ቀዶ ሕክምናዎች ሁሉ ይኼኛውም ያለደም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

1999፦ የአምስት ዓመቷ ሴሲሊያ በሁዋን ፒ ጋራሃን የልጆች ሆስፒታል

ሴሲሊያ “ይህን ሁሉ ቀዶ ሕክምና በሰውነቴ ላይ ማድረግ በጣም አስጨናቂ ነበር” በማለት በሐቀኝነት ተናግራለች። ሆኖም አዎንታዊ ለመሆን ጥረት አድርጋለች፤ እንዲሁም በይሖዋ ትታመን ነበር። ከዚህም ሌላ እሷም ሆነች ወላጆቿ ሐኪሞች የሰጧቸውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ሴሲሊያ እንዲህ ብላለች፦ “ከቀዶ ሕክምናው በፊት ሰውነቴን ማዘጋጀቴ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህም የብረት ማዕድን፣ ፎሊክ አሲድና ኤሪትሮፖየቲን መውሰድን እንዲሁም በብረት ማዕድን የበለጸጉ ምግቦችን በብዛት መመገብን ይጨምራል፤ ይህን ማድረጌ ሰውነቴ ብዙ ቀይ የደም ሴሎችን እንዲያመርት ይረዳዋል።”

ሴሲሊያ ባለፉት ዓመታት ስለረዷት የሕክምና ባለሙያዎች ስትናገር “ሥራቸውን በጣም አደንቃለሁ፤ እንዲህ የምለው ሕይወቴን ስላተረፉልኝ ብቻ ሳይሆን ደም ላለመውሰድ ያደረግኩትን ውሳኔ ስላከበሩልኝም ጭምር ነው” ብላለች።

ዶክተር ኤርነስቶ ቤርሱስኪ፣ ጡረታ የወጡ የአከርካሪ ሕክምና ባለሙያ

ለሴሲሊያ እንክብካቤ ሲያደርጉ የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎችም ለእሷም ሆነ እርዳታ ሲያደርጉላት ለነበሩ ወንድሞች ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል። ለሴሲሊያ በተደረጉላት በአብዛኞቹ የአከርካሪ ቀዶ ሕክምናዎች ላይ የተሳተፉት በቦነስ አይረስ የሚገኘው የሁዋን ፒ ጋራሃን የልጆች ሆስፒታል የአከርካሪ ሕክምና ክፍል የቀድሞ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ኤርነስቶ ቤርሱስኪ እንዲህ ብለዋል፦ “ለሴሲሊያ ሕክምና ባደረግኩበት ወቅት ያላትን ቁርጠኝነትና የምታምንበትን ነገር በግልጽ የማስረዳት ችሎታዋን አስተውያለሁ። ብዙ ጊዜ ተነጋግረናል፤ ሕክምናው ምን እንደሚመስልና በምንም ዓይነት ደም እንደማይሰጣት ከቀዶ ሕክምናዎቹ በፊት እነግራት ነበር።”

ዶክተር ሱዛና ሲሩዚ፣ ጠበቃና የሕክምና ሥነ ምግባር ባለሙያ

ጠበቃና የሁዋን ፒ ጋራሃን የልጆች ሆስፒታል የሕክምና ሥነ ምግባር ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶክተር ሱዛና ሲሩዚ እንዲህ ብለዋል፦ “በይሖዋ ምሥክሮችና በሕክምና ባለሙያዎች መካከል ያልተቋረጠ ትብብር ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስንሠራ አስተሳሰባችንንና የምንጠቀምባቸውን ዘዴዎች ለመቀየር ተስማምተናል። ይህም ያለደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ዘዴዎችን ለማግኘት አስችሎናል።”

ሴሲሊያ ከሕክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ ለእምነት ባልንጀሮቿም አድናቆቷን ገልጻለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ እና በሕሙማን ጠያቂ ቡድን ውስጥ የሚሠሩትን ወንድሞች በእጅጉ አደንቃለሁ። የቤተሰብ ኃላፊነትና ሌሎች ኃላፊነቶች ቢኖሩባቸውም የሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስና በማንኛውም ሰዓት ለመገኘት ያላቸው ፈቃደኝነት በጣም ያስገርመኛል።”

የ25 ዓመቷ ሴሲሊያ ከባድ አካላዊ ሕመም ያለባት ከመሆኑም ሌላ ያለተሽከርካሪ ወንበር እርዳታ መንቀሳቀስ አትችልም፤ ሆኖም የምትታወቀው አዎንታዊ በመሆኗ ነው። እንዲያውም “ያጋጠመኝ ከባድ ችግር ባሕርዬን ለማስተካከልና ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማዳበር እንደረዳኝ ይሰማኛል” ብላለች።

ሐምሌ 2019፦ ሴሲሊያ ከሌላ አቅኚ እህት ጋር ስታገለግል

አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት ቀዶ ሕክምና ከተደረገልኝ በኋላ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባል የሆነ ወንድም ሊጠይቀኝ መጥቶ ምሳሌ 10:22ን ጠቅሶልኝ ነበር፤ ጥቅሱ ‘የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ እሱም ከበረከቱ ጋር [ዘላቂ] ሥቃይን አይጨምርም’ ይላል። ይህ ጥቅስ በልቤና በአእምሮዬ ላይ ታትሟል።”

ግንቦት 1, 2019 እህታችን ሴሲሊያ አንድ ልዩ በረከት አግኝታለች፤ የዘወትር አቅኚ ሆና እንድታገለግል ተሹማለች። ይሖዋ ውድ እህታችንን እንዳጽናናትና እንዳበረታታት በግልጽ ማየት ይቻላል። በውጤቱም እሷም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን አጽናኝ መልእክት ለሌሎች በደስታ ትናገራለች።

ይሖዋ ሴሲሊያን እንዳጽናናት ሁሉ ሁላችንንም በሚደርስብን መከራ ሁሉ እንደሚያጽናናን እንተማመናለን።—2 ቆሮንቶስ 1:4