በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

Comstock Images/Stockbyte via Getty Images

ነቅታችሁ ጠብቁ!

መሪ አድርገህ የምትመርጠው ማንን ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መሪ አድርገህ የምትመርጠው ማንን ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት፣ በዓለም ላይ ባሉ የተለያዩ አገሮች ውስጥ ምርጫ ይደረጋል። ሰዎች ማን ይምራን የሚለውን ለመምረጥ አስፈላጊ ውሳኔ የሚያደርጉበት ወቅት ነው።

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር አለ?

ሰው ሰውን የመምራት አቅሙ ውስን ነው

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሁሉም መሪዎች ያለባቸውን የአቅም ውስንነት በግልጽ ይናገራል።

  •   “በመኳንንትም ሆነ ማዳን በማይችሉ ሰዎች አትታመኑ። እስትንፋሱ ትወጣለች፤ ወደ መሬት ይመለሳል፤ በዚያው ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።”—መዝሙር 146:3, 4 የግርጌ ማስታወሻ

 አንድ መሪ፣ የፈለገ ያህል ብቃት ቢኖረው ከሞት አያመልጥም። እሱን የሚተኩት ሰዎችም ያስጀመራቸውን መልካም ሥራዎች እንደሚያስቀጥሉ ዋስትና መስጠት አይችልም።—መክብብ 2:18, 19

 እንደ እውነቱ ከሆነ፣ መጀመሪያውኑም ቢሆን ሰው ሰውን እንዲመራ እንዳልተፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።

  •   ‘ሰው አካሄዱን በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።’ —ኤርምያስ 10:23

 ታዲያ በዚህ ዘመን ጥሩ መሪ ከየት ማግኘት ይቻላል?

አምላክ የሾመው መሪ

 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አምላክ ከማንም በላይ ብቁና እምነት የሚጣልበት መሪ ሾሟል፤ እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (መዝሙር 2:6) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ነው፤ ይህ መንግሥት የሚገዛው ከሰማይ ሆኖ ነው።—ማቴዎስ 6:10

 ኢየሱስን መሪህ አድርገህ ትመርጣለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ምርጫ ያለውን አስፈላጊነት ሲያጎላ እንዲህ ብሏል፦

  •   “ልጁን [ኢየሱስ ክርስቶስን] አክብሩ፤ አለዚያ አምላክ ይቆጣል፤ ከመንገዱም ትጠፋላችሁ፤ ቁጣው ፈጥኖ ይነድዳልና። እሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።”—መዝሙር 2:12

 ምርጫ ማድረግ ያለብህ አሁኑኑ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደምንረዳው ኢየሱስ በ1914 መግዛት ጀምሯል፤ በቅርቡ ደግሞ የአምላክ መንግሥት፣ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ አጥፍቶ በምትካቸው ማስተዳደር ይጀምራል።—ዳንኤል 2:44

 ለኢየሱስ አመራር ድጋፍህን ማሳየት ትፈልጋለህ? ይህን እንዴት ማድረግ እንደምትችል ለማወቅ “የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ!” የሚለውን ርዕስ አንብብ።