በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ዓለም አቀፍ እርዳታ መስጠት

በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ዓለም አቀፍ እርዳታ መስጠት

ሐምሌ 1, 2021

 መጋቢት 2020 የዓለም የጤና ድርጅት፣ ኮቪድ-19⁠ን ወረርሽኝ ብሎ ባወጀበት ወቅት ብዙዎች ወረርሽኙ ይህን ያህል ረጅም ጊዜ ይዘልቃል ብለው አልጠበቁም። የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በወረርሽኙ የተነሳ አካላዊ፣ ስሜታዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ለዚህ ዓለም አቀፍ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የእርዳታ ሥራ ያስተባበሩት እንዴት ነው?

እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው መድረስ

 በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ሥር ባለው የአስተባባሪዎች ኮሚቴ አመራር፣ ለኮቪድ-19 ምላሽ ለመስጠት ሲባል በዓለም ዙሪያ ከ950 የሚበልጡ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። በአንዳንድ ቦታዎች፣ በአካባቢው ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርስ እንዲረዳዱ ዝግጅት ተደርጓል፤ በሌሎች ቦታዎች ደግሞ መንግሥት የሚሰጠውን እርዳታ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ተመቻችቷል። የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች መጠነ ሰፊ የእርዳታ ሥራዎችንም አስተባብረዋል።

 በፓራጓይ የነበረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ጋዜጣ፣ ወረርሽኙ ስላስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ሲዘግብ “ብዙ የፓራጓይ ነዋሪዎች፣ ቤታቸው ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ አጥተዋል” ብሏል። በፓራጓይ ያለው የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ግን ለሁለት ሳምንት የሚበቃ ምግብና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች የያዘ እሽግ አስቀድሞ ማከፋፈል ጀምሮ ነበር፤ አንዱ እሽግ፣ አራት አባላት ላሉት ቤተሰብ በቂ ነው። የእያንዳንዱ እሽግ ዋጋ በገንዘብ ሲሰላ 30 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ይደርሳል።

 እነዚህ የእርዳታ ሠራተኞች፣ ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ከኮቪድ-19 ለመጠበቅ ምን አድርገዋል? ማስክ ያደርጋሉ እንዲሁም አካላዊ ርቀታቸውን ይጠብቃሉ። በተጨማሪም ወንድሞች፣ ምግብ የሚያቀርቡት ድርጅቶች የሥራ አካባቢያቸው ንጹሕ መሆን አለመሆኑን እንዲሁም የደህንነት መመሪያዎችን በጥብቅ እየተከተሉ መሆን አለመሆናቸውን ያጣራሉ። ለምሳሌ ከእሽጎቹ ጋር ንክኪ ያለው ማንኛውም ሰው የደህንነት መጠበቂያ አልባሳትን እንዲለብስ፣ እሽጎቹን የሚያመላልስበትን ተሽከርካሪ በኬሚካል እንዲያጸዳ እንዲሁም እሽጎቹን በኬሚካል በጸዱ ቦታዎች እንዲያስቀምጥ መመሪያ ተሰጥቷል። እሽጎቹን የሚያደርሱትም ቢሆኑ ከሚያደርሱላቸው ወንድሞች ጋር አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ተነግሯቸዋል።

በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በጥበብ መጠቀም

 እስከ ጥር 2021 ድረስ፣ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ ለኮቪድ-19 የሚውል ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ አጽድቋል። ቅርንጫፍ ቢሮዎችና የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች በመዋጮ የተገኘውን ይህን ገንዘብ የሚጠቀሙት በጥንቃቄ ነው፤ ግዢ ሲፈጽሙ የተሻለ ዋጋ ለማግኘት የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቺሊ የእርዳታ ሥራውን የሚያስተባብሩት ወንድሞች 750 ኪሎ ግራም ምስር መግዛት ፈልገው ነበር። ሆኖም የምስር ዋጋ በአንድ ወር ውስጥ በእጥፍ ጨመረ! ወንድሞች በተወደደው ዋጋ ምስሩን ለመግዛት ከተስማሙ ከሁለት ሰዓት በኋላ፣ ነጋዴው ሌላ ደንበኛው ያዘዘውን ምስር እንደመለሰበት ነገራቸው። ስለዚህ ነጋዴው መጀመሪያ በተስማሙበት ዋጋ ሳይሆን ቀደም ባለው ወር ባለው የቅናሽ ዋጋ የተመለሰበትን ምስር ሸጠላቸው።

 ወንድሞች ምስሩን ለመውሰድ ሲሄዱ ግን ነጋዴው ውሉን መሰረዝ ፈለገ፤ እንደ ሌሎቹ ድርጅቶች ሁሉ እነሱም ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ምግብ እያከፋፈሉ እንደሆነ በመግለጽ ወነጀላቸው። አንደኛው ወንድም በልቡ ከጸለየ በኋላ ለነጋዴው ሁኔታውን አስረዳው፤ በእርግጥ እርዳታ የሚያስፈልገው ማን እንደሆነ ለማወቅ በእያንዳንዱ ጉባኤ ጥናት እንደተካሄደ ነገረው። በተጨማሪም እርዳታው የሚደርሳቸው ሰዎች ከተለያየ ባሕል የመጡ እንደሆኑና እያንዳንዱ የእርዳታ እሽግ የሚዘጋጀው የእያንዳንዱን ቤተሰብ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ወንድሞች ለነጋዴው አብራሩለት። በመጨረሻም የይሖዋ ምሥክሮች ገንዘባቸውንም ሆነ ጉልበታቸውን የሚሰጡት በፈቃደኝነት እንደሆነ አስረዱት። ነጋዴው ይህን ሲያውቅ በጣም ተገረመ። በመሆኑም ቃል በገባላቸው የቅናሽ ዋጋ ምስሩን ለመሸጥ ተስማማ፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ግን በቀጣዩ ትእዛዛቸው ላይ 400 ኪሎ ግራም ተጨማሪ ምስር በነፃ ሰጣቸው።

“እውነተኛ ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ”

 በላይቤሪያ የሚኖሩ ሉሱ የሚባሉ አንዲት በዕድሜ የገፉ መበለት ከአምስት የቤተሰባቸው አባላት ጋር ይኖራሉ። አንድ ቀን ጠዋት ቁርስ እየበሉ በዕለት ጥቅሱ ላይ ሲወያዩ፣ የሰባት ዓመት የልጅ ልጃቸው ቤት ውስጥ ምንም ምግብ እንደሌለ አስተዋለ። “ምን ልንበላ ነው?” ብሎ ጠየቀ። ሉሱም ይሖዋ እንዲረዳቸው እንደጸለዩና እሱም ጸሎታቸውን ሰምቶ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚሰጣቸው እርግጠኛ እንደሆኑ ነገሩት። በዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ፣ ሉሱ ከጉባኤያቸው ሽማግሌዎች ተደወለላቸው፤ መጥተው የምግብ እርዳታ እንዲወስዱ ነገሯቸው። ሉሱ እንዲህ ብለዋል፦ “የልጅ ልጄ ‘አሁን ይሖዋ ጸሎት እንደሚሰማና እንደሚመልስ አውቄያለሁ’ ብሏል፤ ይህን ያለው ይሖዋ የእኔን ጸሎት እንደመለሰ ስላየ ነው።”

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሚኖሩ ልጆች ለተደረገላቸው የምግብ እርዳታ ወንድሞቻቸውን ለማመስገን የሣሏቸው ሥዕሎች

 በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የምትኖር አንዲት ሴት ጎረቤቶቿ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ይህ ቤተሰብ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው እርዳታ ሲደርሳቸው ስታይ እንዲህ ብላለች፦ “ከወረርሽኙ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ነው የምንሆነው፤ ምክንያቱም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው እንደሚያስቡ ያሳዩት እነሱ ናቸው።” በዚህ ጊዜ ባለቤቷ “ለአንድ ከረጢት ሩዝ ብለሽ ነው የይሖዋ ምሥክር የምትሆኚው?” አላት። እሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት፦ “እሱማ አይደለም፤ ይህ ሩዝ ግን እውነተኛ ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ ነው።”

 እናንተ በልግስና በምታደርጉት መዋጮ የተነሳ በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በአፋጣኝ ማግኘት ችለዋል። በ​donate.isa4310.com ላይ የተገለጹትን የተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅማችሁ መዋጮ ስለምታደርጉ ከልብ እናመሰግናችኋለን!