በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ማስደሰት እንችላለን?

አምላክን ማስደሰት እንችላለን?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው በጥሩ ስለተወሳ ሰዎች ስታነብ ለራስህ ‘እኔ እንደነሱ መሆን አልችልም!’ ብለህ ታውቃለህ? ምናልባት ‘እኔ ጻድቅ አይደለሁም፤ ብዙ ጊዜ ስህተት እንደምሠራ የታወቀ ነው’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበትና ቅን ሰው” ነበር።—ኢዮብ 1:1 የግርጌ ማስታወሻ

ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበትና ቅን ሰው” ተብሏል። (ኢዮብ 1:1 የግርጌ ማስታወሻ) ሎጥ “ጻድቅ ሰው” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ጴጥሮስ 2:8) እንዲሁም ዳዊት በአምላክ ፊት “ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ” እንዳደረገ ተነግሮለታል። (1 ነገሥት 14:8) ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን የእነዚህን ሰዎች የሕይወት ታሪክ በዝርዝር እንመልከት። እንዲህ ስናደርግ (1) ስህተት ሠርተው እንደነበር፣ (2) እነሱ ከተዉት ምሳሌ ብዙ እንደምንማር እና (3) ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች አምላክን ማስደሰት እንደሚችሉ እንመለከታለን።

ስህተት ሠርተው ነበር

“[አምላክ] ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በሚፈጽሙት ዓይን ያወጣ ምግባር እጅግ እየተሳቀቀ ይኖር የነበረውን ጻድቁን ሎጥን አድኖታል።”—2 ጴጥሮስ 2:7

ኢዮብ በሕይወቱ ላይ ብዙ መከራ ተፈራርቆበታል፤ የደረሰበት መከራ ፍትሕ የጎደለው እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ መሆን አለመሆኑ በአምላክ ዘንድ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ አስቦ ነበር። (ኢዮብ 9:20-22) ኢዮብ ስለ ራሱ ጽድቅ በጣም እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሳ ‘እኔ ከአምላክ ይበልጥ ጻድቅ ነኝ’ ብሎ የተናገረ ያህል ነበር።—ኢዮብ 32:1, 2፤ 35:1, 2

ሎጥ የተሰጠውን ግልጽና ቀላል የሆነ መመሪያ ታዞ እርምጃ ለመውሰድ አመንትቶ ነበር። በሰዶምና በገሞራ ሰዎች ያዘቀጠ የሥነ ምግባር አቋም የተነሳ በእጅጉ ይሳቀቅና “ነፍሱን ያስጨንቅ ነበር።” (2 ጴጥሮስ 2:8) አምላክ እነዚያን ክፉ ከተሞች ሊያጠፋ እንዳሰበ ተናገረ፤ እንዲሁም ለሎጥ ቤተሰቡን ይዞ በመውጣት በሕይወት መትረፍ የሚችልበት አጋጣሚ ሰጠው። ሎጥ ይህን ሲሰማ አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁንና ሎጥ በዚህ ወሳኝ ወቅት እርምጃ ለመውሰድ አመነታ። እሱንና ቤተሰቡን ለማዳን የተላኩት መላእክት ሎጥንና ቤተሰቡን እጃቸውን ይዘው ከከተማዋ ማውጣት አስፈልጓቸው ነበር።—ዘፍጥረት 19:15, 16

ዳዊት ‘በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ በማድረግ በሙሉ ልቡ አምላክን ተከትሏል።’—1 ነገሥት 14:8

ዳዊት በአንድ ወቅት ራሱን መግዛት አቅቶት ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ምንዝር ፈጽሟል። ይባስ ብሎ ደግሞ ኃጢአቱን ለመሸፋፈን ሲል የሴትየዋን ባል አስገደለ። (2 ሳሙኤል ምዕራፍ 11) መጽሐፍ ቅዱስ “ዳዊት ያደረገው ነገር ይሖዋን በጣም አሳዝኖት” እንደነበር ይገልጻል።—2 ሳሙኤል 11:27

ኢዮብ፣ ሎጥና ዳዊት ሁሉም ስህተት ሠርተዋል፤ ደግሞም የሠሯቸው አንዳንዶቹ ስህተቶች በጣም ከባድ ነበሩ። ይሁን እንጂ ቀጥሎ እንደምንመለከተው አምላክን በታዛዥነት ለማገልገል ብርቱ ፍላጎት ነበራቸው። በሠሩት ድርጊት ማዘናቸውን ያሳዩ ከመሆኑም ሌላ አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ነበሩ። በመሆኑም አምላክ ሞገሱን አሳይቷቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች ታማኞች ብሎ ይጠራቸዋል።

ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

ፍጽምና የሌለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ስህተት የምንሠራባቸው ጊዜያት አሉ። (ሮም 3:23) ይሁንና ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ከልብ እንዳዘንን ማሳየትና የሠራነውን ስህተት ለማስተካከል አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።

ኢዮብ፣ ሎጥና ዳዊት ከስህተታቸው ለመታረም የሞከሩት እንዴት ነበር? እንደ እውነቱ ከሆነ ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ የተመላለሰ ሰው ነበር። አምላክ ከእሱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ኢዮብ አስተሳሰቡን ከማስተካከሉም በላይ በተናገረው ነገር ተጸጽቷል። (ኢዮብ 42:6) የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ስለነበራቸው ያዘቀጠ ምግባር ሎጥ የነበረው አመለካከት፣ ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ነበር። የሎጥ ችግር ለጊዜውም ቢሆን የጥድፊያ ስሜት ማጣቱ ነበር። እርግጥ ኋላ ላይ ጥፋት ከተፈረደባቸው ከእነዚያ ከተሞች ሸሽቶ በመውጣት ከአምላክ ፍርድ አምልጧል። ትቶት የወጣውን ነገር ወደ ኋላ እንዳይመለከት የተሰጠውን ትእዛዝ በታማኝነት ፈጽሟል። ዳዊትም ቢሆን የአምላክን ሕግ በመጣስ ከባድ ስህተት ቢሠራም ከልብ ንስሐ በመግባትና የአምላክን ምሕረት በመለመን ልቡ ምን ዓይነት ሰው መሆኑን አሳይቷል።—መዝሙር 51

አምላክ ለእነዚህ ሰዎች ሞገስ ማሳየቱ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆኑን የሚያሳይ ነው። አምላክ “እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃልና፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል።” (መዝሙር 103:14) ታዲያ አምላክ ሙሉ በሙሉ ስህተት ከመሥራት መራቅ እንደማንችል የሚያውቅ ከሆነ ከእኛ የሚጠብቀው ነገር ምንድን ነው?

አምላክ “እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃልና፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል።”—መዝሙር 103:14

ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች አምላክን ማስደሰት የሚችሉት እንዴት ነው?

ዳዊት ለልጁ ለሰለሞን የሰጠው ምክር አምላክን ማስደሰት የምንችልበትን ቁልፍ ነገር ይጠቁመናል። “አንተም ልጄ ሰለሞን ሆይ፣ የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በሙሉ ልብ . . . አገልግለው።” (1 ዜና መዋዕል 28:9) ሙሉ ልብ ምንድን ነው? ሙሉ ልብ ሲባል አምላክን የሚወድ እንዲሁም ፈቃዱን ለማወቅና ለመፈጸም የሚጥር ልብ ማለት ነው። እንዲህ ሲባል ግን ፍጹም ነው ማለት አይደለም፤ ይሁንና አምላክን በታዛዥነት ለማገልገል የሚጓጓና ለመታረም ፈቃደኛ የሆነ ልብ ነው። አምላክ ኢዮብን “ነቀፋ የሌለበት፣” ሎጥን “ጻድቅ” እንዲሁም ዳዊትን በአምላክ ፊት ‘ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ የሚያደርግ’ ብሎ የጠራቸው እሱን በመውደዳቸውና ትእዛዙን ለመፈጸም ከልብ በመፈለጋቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ስህተት የሠሩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም እንኳ አምላክን ማስደሰት ችለዋል።

ሙሉ ልብ ሲባል የአምላክን ፈቃድ ለማወቅና ለመፈጸም የሚጥር እንዲሁም አምላክን በታዛዥነት ለማገልገል የሚጓጓ ልብ ማለት ነው

ስለዚህ መጥፎ ሐሳቦች ወደ አእምሯችን ቢመጡብን ወይም በኋላ ላይ የምናፍርበትን ነገር ብንናገር አሊያም ደግሞ በኋላ ላይ የምንጸጸትባቸውን ነገሮች ብናደርግ ከላይ የተመለከትናቸው ሦስት ሰዎች የተውትን ምሳሌ በማሰብ መጽናናት እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ ፍጽምና ልንደርስበት የማንችለው ነገር እንደሆነ አምላክ ያውቃል። ያም ሆኖ እንድንወደውና እሱን ለመታዘዝ ጥረት እንድናደርግ ይጠብቅብናል። በሙሉ ልባችን አምላክን የምንወድና የምንታዘዝ ከሆነ እኛም እሱን ማስደሰት እንችላለን።