በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ”

“ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ”

“በሥራችሁ አትለግሙ። . . . ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ።”—ሮም 12:11

1. ብዙዎች ስለ ባርነት ያላቸው አመለካከት በሮም 12:11 ላይ ከተገለጸው ባርነት የሚለየው እንዴት ነው?

ክርስቲያን ስንሆን የገባንበት ባርነት ብዙ ሰዎች ስለ ባርነት ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው ከሚመጣው ሁኔታ በጣም የተለየ ነው። ብዙዎች ባሪያ መሆን ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው በጭካኔ መረገጥ፣ ጭቆናና ግፍ ነው። ይሁን እንጂ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል፣ አፍቃሪ ለሆነ ጌታ ባሪያ ሆኖ በፈቃደኝነት ስለ ማገልገል ይናገራል። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች “ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ” ሲላቸው ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርቡ እያበረታታቸው ነበር። (ሮም 12:11) እንዲህ ዓይነቱ ባርነት ምን ማድረግን ይጠይቃል? የሰይጣን እና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ባሪያ ላለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ይሖዋን እንደ ባሪያ በታማኝነት ማገልገል ምን በረከቶች ያስገኛል?

“ጌታዬን . . . እወዳለሁ”

2. (ሀ) አንድ እስራኤላዊ ባሪያ ነፃ የመውጣት አጋጣሚውን በገዛ ፈቃዱ እንዲተው የሚያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ባሪያው ጆሮውን መበሳቱ ምን ትርጉም አለው?

2 አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ይሖዋ ባሪያዎቹ ስንሆን ምን እንደሚጠብቅብን ለማወቅ ያስችለናል። አንድ ዕብራዊ ባሪያ ሰባት ዓመት ካገለገለ በኋላ ነፃ ይወጣል። (ዘፀ. 21:2) ይሁንና አንድ ባሪያ ጌታውን የሚወድድና እሱን ማገልገሉን መቀጠል የሚፈልግ ከሆነ ይሖዋ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለየት ያለ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ጌታው፣ ባሪያውን ወደ በሩ ወይም ወደ በሩ መቃን ወስዶ ጆሮውን በወስፌ ይበሳዋል። (ዘፀ. 21:5, 6) ጌታው የሚበሳው የባሪያውን ጆሮ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። በዕብራይስጥ፣ ታዛዥነት የሚለውን ሐሳብ ለመግለጽ የተሠራበት ቃል ከመስማት እና ከማዳመጥ ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም ባሪያው ጆሮውን መበሳቱ፣ ጌታውን በታዛዥነት ማገልገሉን ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆኑን የሚጠቁም ነው። ይህ ዘገባ እኛም ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችን ምን ትርጉም እንዳለው እንድንገነዘብ ይረዳናል፤ ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን በፈቃደኝነት ልንታዘዘው እንደምንፈልግ መግለጻችን ነው።

3. ራሳችንን ለአምላክ እንድንወስን የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

3 ክርስቲያኖች ለመሆን ስንጠመቅ ይሖዋን ለማገልገል እንዲሁም  የእሱ ባሪያዎች ለመሆን እንደወሰንን አሳይተናል። ራሳችንን የወሰንነው ይሖዋን የመታዘዝና ፈቃዱን የመፈጸም ፍላጎት ስላለን ነው። ይህንን እንድናደርግ ማንም አላስገደደንም። ትናንሽ ልጆች እንኳ የሚጠመቁት በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን ለይሖዋ ስለወሰኑ እንጂ ወላጆቻቸውን ለማስደሰት ብለው አይደለም። ክርስቲያኖች፣ ራሳችንን ለአምላክ የምንወስነው በሰማይ ላለው ጌታችን ለይሖዋ ፍቅር ስላለን ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው” ሲል ጽፏል።—1 ዮሐ. 5:3

ነፃ ሰው ሆኖም ባሪያ

4. “የጽድቅ ባሪያዎች” ለመሆን ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

4 ይሖዋ የእሱ ባሪያዎች እንድንሆን ዝግጅት ስላደረገልን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳደራችን ከኃጢአት ባርነት ነፃ መውጣት ችለናል። ይህም ሲባል፣ ፍጽምና ደረጃ ላይ ባንደርስም እንኳ ይሖዋ እና ኢየሱስ ጌቶቻችን እንዲሆኑ መርጠናል ማለት ነው። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “ለኃጢአት እንደሞታችሁ ሆኖም በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ እንደምትኖሩ አድርጋችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ” ብሏል። ከዚያም እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “ለማንም ቢሆን እንደ ባሪያዎች ሆናችሁ ለመታዘዝ ራሳችሁን ካቀረባችሁ ለእሱ ስለምትታዘዙ የእሱ ባሪያዎች እንደሆናችሁ አታውቁም? በመሆኑም ሞት ለሚያስከትለው ለኃጢአት አለዚያም ጽድቅ ለሚያስገኘው ለታዛዥነት ባሪያዎች ናችሁ። ሆኖም እናንተ የኃጢአት ባሪያዎች የነበራችሁ ቢሆንም በአደራ ለተሰጣችሁ ለእንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ከልብ ስለታዘዛችሁ አምላክ የተመሰገነ ይሁን። አዎ፣ ከኃጢአት ነፃ ስለወጣችሁ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።” (ሮም 6:11, 16-18) ሐዋርያው ‘ከልብ ስለ መታዘዝ’ እንደተናገረ ልብ በል። በመሆኑም ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን “የጽድቅ ባሪያዎች” ሆነናል።

5. ሁላችንም በውስጣችን ምን ዓይነት ትግል አለብን? ለምንስ?

5 ያም ቢሆን፣ ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እንዳንኖር እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። ከሁለት ነገሮች ጋር ትግል መግጠም ያስፈልገናል። የመጀመሪያው፣ ጳውሎስ የገጠመው ዓይነት ትግል ነው። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋና በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” (ሮም 7:22, 23) የወረስነው አለፍጽምና እኛንም ያስቸግረናል። ከሥጋ ምኞቶቻችን ጋር ሁልጊዜ መታገል ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል፦ “እንደ ነፃ ሰዎች ኑሩ፤ ሆኖም ነፃነታችሁን እንደ አምላክ ባሪያዎች ሆናችሁ ተጠቀሙበት እንጂ ለክፋት መሸፈኛ አታድርጉት።”—1 ጴጥ. 2:16

6, 7. ሰይጣን፣ ይህ ዓለም አጓጊ እንዲመስለን የሚያደርገው እንዴት ነው?

6 ሁለተኛው ደግሞ በአጋንንት ተጽዕኖ ሥር ካለው ከዚህ ዓለም ጋር የምናደርገው ትግል ነው። የዚህ ዓለም ገዥ የሆነው ሰይጣን፣ ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለንን ታማኝነት እንድናጓድል ለማድረግ የጥቃት ዒላማውን በእኛ ላይ አነጣጥሯል። በመጥፎ ተጽዕኖው እንድንሸነፍ የሚያደርግ ፈተና በማቅረብ የእሱ ባሪያዎች ሊያደርገን ይጥራል። (ኤፌሶን 6:11, 12ን አንብብ።) ሰይጣን ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ እሱ የሚቆጣጠረውን ዓለም ማራኪና አጓጊ ማስመሰል ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “ማንም ዓለምን የሚወድ ከሆነ የአብ ፍቅር በውስጡ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም።”—1 ዮሐ. 2:15, 16

7 በዓለም ዙሪያ ብዙዎች ቁሳዊ ብልጽግና የማግኘት ምኞት ተጠናውቷቸዋል። ሰይጣን ገንዘብ ከሌለን ደስተኛ እንደማንሆን ለማሳመን ይሞክራል። ትላልቅ የገበያ አዳራሾች በየቦታው ይገኛሉ። የማስታወቂያው ኢንዱስትሪ፣ ንብረት እንድናካብትና ሕይወታችን በመዝናናት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ያበረታታናል። ለምሳሌ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ማራኪ ወደሆኑ ቦታዎች ጉዞዎች ያዘጋጃሉ፤ ብዙውን ጊዜ ግን እንዲህ ዓይነቶቹ ፕሮግራሞች ዓለማዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር እንድንቀራረብ ያደርጉናል። በዙሪያችን የምናያቸው ነገሮች በሙሉ በዓለም መሥፈርት “ምርጥ” የሚባለው ዓይነት ሕይወት እንድንመራ የሚያበረታቱ ናቸው።

8, 9. ለምን ነገር ባሪያ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል? ለምንስ?

 8 ጴጥሮስ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩትን የዓለም አመለካከት ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሰዎች በመጥቀስ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ጽፏል፦ “በጠራራ ፀሐይ መፈንጠዝን እንደ ደስታ ይቆጥሩታል። እነዚህ ሰዎች እንደ ቆሻሻና እድፍ ናቸው፤ ከእናንተ ጋር በግብዣ ላይ ሲገኙ አታላይ በሆኑ ትምህርቶቻቸው ሌሎችን በማሳት እጅግ ይደሰታሉ። በከንቱ ጉራ ይነዛሉ፤ በተሳሳተ ጎዳና ከሚመላለሱ ሰዎች መካከል አምልጠው በመውጣት ላይ ያሉትን በሥጋ ምኞትና በብልግና ያማልላሉ። እነሱ ራሳቸው የመጥፎ ሥነ ምግባር ባሪያዎች ሆነው ሳሉ ነፃ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል። ነገር ግን ሰው ለተሸነፈለት ነገር ሁሉ ባሪያ ነው።”—2 ጴጥ. 2:13, 18, 19

9 አንድ ሰው ‘የዓይን አምሮቱን’ ማርካቱ ነፃ እንዲወጣ አያደርገውም። ከዚህ ይልቅ፣ ለማይታየው የዚህ ዓለም ገዥ ይኸውም ለሰይጣን ዲያብሎስ ባሪያ እንዲሆን ያደርገዋል። (1 ዮሐ. 5:19) በእርግጥም ካልተጠነቀቅን የፍቅረ ነዋይ ባሪያ ልንሆን እንችላለን፤ ከዚህ ዓይነቱ ባርነት መላቀቅ ደግሞ ቀላል አይደለም።

እርካታ የሚያስገኝ ሥራ

10, 11. በዛሬው ጊዜ የሰይጣን ጥቃት ዋነኛ ዒላማ እነማን ናቸው? ዓለማዊ ትምህርት እንቅፋት ሊሆንባቸው የሚችለውስ እንዴት ነው?

10 ሰይጣን፣ በኤደን ገነት እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ዒላማውን የሚያነጣጥረው ተሞክሮ በሌላቸው ሰዎች ላይ ነው። በተለይ ወጣቶች የጥቃቱ ዋነኛ ዒላማ ናቸው። ሰይጣን፣ ወጣቶችም ሆኑ ማንኛውም ሰው ራሱን ለይሖዋ ባሪያ አድርጎ ሲያቀርብ ማየት ያበሳጨዋል። ይህ የአምላክ ጠላት፣ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሁሉ የገቡትን ቃል እንዳይጠብቁና ታማኝነታቸውን እንዲያጓድሉ ማድረግ ይፈልጋል።

11 ጆሮውን ለመበሳት ፈቃደኛ የሆነውን ባሪያ ሁኔታ እስቲ በድጋሚ እንመልከት። ይህ ባሪያ ለጊዜው ቁስሉ እንደሚያምመው የታወቀ ነው፤ በእርግጥ ሕመሙ ብዙም ሳይቆይ ይጠፋል፤ ባርነቱን የሚያረጋግጠው ምልክት ግን እስከ ዕድሜው ፍጻሜ አብሮት ይኖራል። በተመሳሳይም አንድ ወጣት ከእኩዮቹ የተለየ አካሄድ መከተል ሊከብደው አልፎ ተርፎም ሊያስጨንቀው ይችላል። ሰይጣን እሱ በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ጥሩ ሥራ መያዝ እርካታ ያለው ሕይወት እንደሚያስገኝ ለማሳመን ይጥራል፤ ክርስቲያኖች ግን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው፣ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንደሆነ አይዘነጉም። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” በማለት አስተምሯል። (ማቴ. 5:3) ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች የሚኖሩት የአምላክን እንጂ የሰይጣንን ፈቃድ ለመፈጸም አይደለም። በአምላክ ሕግ ደስ የሚሰኙ ሲሆን ሕጉን በቀንና በሌሊት ያሰላስሉታል። (መዝሙር 1:1-3ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ የትምህርት ፕሮግራሞች ግን የይሖዋ አገልጋዮች ለማሰላሰልና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን  ለማሟላት የሚያስችላቸው በቂ ጊዜ እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆኑባቸዋል።

12. በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወጣቶች ምን ዓይነት ምርጫዎች አሏቸው?

12 ዓለማዊ ጌታ፣ ለአንድ ክርስቲያን ነገሮችን አስቸጋሪ ሊያደርግበት ይችላል። ጳውሎስ፣ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ “የተጠራኸው ባሪያ እያለህ ነው?” የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር። ከዚያም እንዲህ የሚል ምክር ሰጠ፦ “ይሄ አያስጨንቅህ፤ ሆኖም ነፃ መውጣት የምትችል ከሆነ አጋጣሚውን ተጠቀምበት።” (1 ቆሮ. 7:21) አንድ ሰው ከባርነት ነፃ መውጣት የሚችል ከሆነ ይህ ጥሩ ነገር ነው። በዛሬው ጊዜ፣ በብዙ አገሮች አንድ ሰው የተወሰነ ዕድሜ ላይ እስኪደርስ የመማር ግዴታ አለበት። ከዚያ በኋላ ግን ተማሪዎች የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ ይችላሉ። አንድ ሰው በዚህ ዓለም ውስጥ ጥሩ የሚባል ሥራ ለማግኘት ሲል ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ከወሰነ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመግባት ነፃነቱ ሊገደብበት ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 7:23ን አንብብ።

የማን ባሪያ መሆን ትፈልጋለህ?

ከፍተኛ ትምህርት ወይስ ከሁሉ የላቀ ትምህርት?

13. የይሖዋ አገልጋዮች፣ ከሁሉ የበለጠ የሚጠቅማቸው ምን ዓይነት ትምህርት ነው?

13 ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ጽፏል፦ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።” (ቆላ. 2:8) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ የተማሩ ሰዎች የሚያስፋፉት ዓለማዊ አስተሳሰብ ‘በሰው ወግ ላይ የተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ’ ነው። ከፍተኛ ትምህርት በዋነኝነት የሚያተኩረው በቀለም ትምህርት ላይ ስለሆነ አብዛኛውን ጊዜ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በገሃዱ ዓለም የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች ለመወጣት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ችሎታዎችና ክህሎቶች አይኖሯቸውም። ከዚህ በተለየ መልኩ የይሖዋ አገልጋዮች የሚመርጡት፣ ቀለል ያለ ሕይወት እየመሩ አምላክን ለማገልገል የሚያስችላቸውን ሙያ መማርን ነው። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ፦ “በእርግጥ፣ ባለው ነገር ለሚረካ ሰው ለአምላክ ማደር ትልቅ ትርፍ ያስገኛል። ስለዚህ ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” (1 ጢሞ. 6:6, 8) እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለማዊ ትምህርት ዲግሪና የማዕረግ ስሞችን ለማግኘት ከመጣር ይልቅ ይበልጥ ትኩረት የሚያደርጉት በስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ በመካፈል “የብቃት ማረጋገጫ ደብዳቤ” በማግኘት ላይ ነው።—2 ቆሮንቶስ 3:1-3ን አንብብ።

14. ጳውሎስ፣ በፊልጵስዩስ 3:8 ላይ ከጻፈው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው የአምላክና የክርስቶስ ባሪያ የመሆን መብቱን እንዴት አድርጎ ይመለከተው ነበር?

14 ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ የተማረው ገማልያል በተባለው የአይሁድ የሕግ መምህር እግር ሥር ሆኖ ነው። ጳውሎስ  የቀሰመው ትምህርት በዛሬው ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ከሚሰጠው ትምህርት ጋር የሚስተካከል ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ፣ ይህን ትምህርት የአምላክና የክርስቶስ ባሪያ በመሆን ካገኘው መብት ጋር ሲያወዳድረው ምን ይሰማው ነበር? እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ስለ ጌታዬ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገልጸው የላቀ ዋጋ ያለው እውቀት የተነሳ ሁሉንም ነገር እንደ ኪሳራ እቆጥረዋለሁ።” አክሎም “ለእሱ ስል ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ፤ ያጣሁትንም ነገር ሁሉ እንደ ጉድፍ እቆጥረዋለሁ፤ ይህም ክርስቶስን አገኝ ዘንድ [ነው]” ብሏል። (ፊልጵ. 3:8) ይህ ሐሳብ፣ ወጣት ክርስቲያኖችም ሆኑ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆቻቸው ከትምህርት ጋር በተያያዘ የጥበብ ውሳኔ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። (ሥዕሎቹን ተመልከት።)

ከሁሉ ከላቀው ትምህርት ጥቅም ማግኘት

15, 16. ከይሖዋ ድርጅት ምን ዓይነት ትምህርት እናገኛለን? ይህ ትምህርት በዋነኝነት የሚያተኩረው በምን ላይ ነው?

15 በዚህ ዓለም ባሉ በብዙዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሰፈነው መንፈስ ምን ዓይነት ነው? አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ፖለቲካዊም ሆነ ማኅበራዊ ዓመፅ ይቀሰቀስ የለም? (ኤፌ. 2:2) ከዚህ በተለየ መልኩ ሰላም በሰፈነበት የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሁሉ የላቀው ትምህርት በይሖዋ ድርጅት አማካኝነት ይቀርብልናል። ሁላችንም በየሳምንቱ ከሚካሄደው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ትምህርት የመቅሰም አጋጣሚ አለን። ከዚህም ሌላ ነጠላ ለሆኑ አቅኚ ወንድሞች (ለነጠላ ወንድሞች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት) እና ላገቡ አቅኚዎች (ለባለትዳሮች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት) የሚቀርቡ ለየት ያሉ ሥልጠናዎች አሉ። እንዲህ ዓይነቱ ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና በሰማይ ያለውን ጌታችንን ይሖዋን ለመታዘዝ ይረዳናል።

16 ከዚህም በተጨማሪ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫን (እንግሊዝኛ) ወይም በሲዲ የተዘጋጀውን ዎችታወር ላይብረሪ በመጠቀም እንደ ውድ ሀብት የሆነ መንፈሳዊ እውቀት ለማግኘት ምርምር ማድረግ እንችላለን። በዚህ መንገድ የምናገኘው ትምህርት በዋነኝነት የሚያተኩረው ይሖዋን እንድናመልክ በመርዳት ላይ ነው። ይህ ሥልጠና ሌሎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ እንዴት መርዳት እንደምንችል ያስተምረናል። (2 ቆሮ. 5:20) እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር የሚያስችል ሥልጠና ያገኛሉ።—2 ጢሞ. 2:2

ባሪያው የሚያገኘው ሽልማት

17. ከሁሉ የላቀውን ትምህርት ለመከታተል መምረጥ ምን በረከቶች ያስገኛል?

17 ኢየሱስ ስለ ታላንቶቹ በተናገረው ምሳሌ ላይ፣ ሁለቱ ታማኝ ባሪያዎች ምስጋናን ያተረፉ ሲሆን የበለጠ ኃላፊነት በመቀበል ወደ ጌታቸው ደስታ ገብተዋል። (ማቴዎስ 25:21, 23ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜም ከሁሉ የላቀውን ትምህርት ለመከታተል መምረጥ ደስታ እና በረከት ያስገኛል። ማይክልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ማይክል በትምህርቱ ጎበዝ ስለነበረ አስተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ስለ መማር አነጋገሩት። ማይክል የአጭር ጊዜ የሙያ ሥልጠና መውሰድ እንደሚፈልግ ሲነግራቸው ተገረሙ፤ ብዙም ሳይቆይ ማይክል ባገኘው ሥልጠና ተጠቅሞ ራሱን እያስተዳደረ የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ይህ ወጣት የቀረበት ነገር እንዳለ ተሰምቶታል? እንዲህ ብሏል፦ “አቅኚ፣ ውሎ አድሮ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌ ስሆን ያገኘሁት ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና በዋጋ ሊተመን አይችልም። በቁሳዊ ረገድ ላገኝ እችል የነበረው ነገር፣ አሁን ካሉኝ በረከቶችና መብቶች ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከፍተኛ ትምህርት ላለመከታተል በመወሰኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

18. ከሁሉ የላቀውን ትምህርት ለመከታተል እንድትመርጥ የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

18 ከሁሉ የላቀው ትምህርት፣ የአምላክን ፈቃድ የሚያስተምረን ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን እንደ ባሪያ እንድናገለግል ይረዳናል። “ከመበስበስ ባርነት ነፃ [የመውጣት]” ውሎ አድሮ ደግሞ “የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት [የማግኘት]” ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋል። (ሮም 8:21) ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ በሰማይ ያለውን ጌታችንን ይሖዋን ከልብ እንደምንወደው ማሳየት የምንችልበትን የላቀ መንገድ ያስተምረናል።—ዘፀ. 21:5