በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጹሕ አየርና የፀሐይ ብርሃን—የተፈጥሮ “አንቲባዮቲክ”

ንጹሕ አየርና የፀሐይ ብርሃን—የተፈጥሮ “አንቲባዮቲክ”

የሳይንስ ሊቃውንት በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ከኬሚካል የሚዘጋጁ የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን ሲፈለስፉ የሕክምና ባለሙያዎች እነዚህ አዳዲስ መድኃኒቶች አንዳንድ በሽታዎችን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወግዱ ተስፋ አድርገው ነበር። መጀመሪያ ላይ አዳዲሶቹ መድኃኒቶች እንደታሰበው ውጤታማ የሆኑ ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ መድኃኒቶች በሰፊው ጥቅም ላይ መዋላቸው መድኃኒቶቹን መቋቋም የሚችሉ ባክቴሪያዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ኢንፌክሽንን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አዳዲስ መንገዶችን ለማግኘት ሲሉ በቀደሙት ዓመታት የበሽታዎችን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ዘዴዎችን መለስ ብለው ማጥናት ጀምረዋል። ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል አንዱ ንጹሕ አየርና የፀሐይ ብርሃን የሚያስገኙት የጤና ጥቅም ነው።

ከታሪክ የተገኘ ትምህርት

በቀደሙት ዓመታት እንግሊዝ ውስጥ የፀሐይ ብርሃንና ንጹሕ አየር ስላላቸው ፈዋሽነት ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱ በርካታ ሊቃውንት ነበሩ። ጆን ሌትሰም የተባሉ ሐኪም (1744- 1815) የሳንባ ነቀርሳ የያዛቸው ልጆች በባሕር አካባቢ የሚገኘውን አየር እንዲተነፍሱና ፀሐይ እንዲሞቁ ያዝዙ ነበር። በ1840 ጆርጅ ቦዲንግተን የተባሉ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ፣ ከቤት ውጭ የሚሠሩ ሰዎች ለምሳሌ ገበሬዎችና እረኞች በአብዛኛው ሲታይ በሳንባ ነቀርሳ በሽታ እንደማይያዙ ሆኖም ቤት ውስጥ የሚውሉ ሰዎች ለዚህ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ እንደሆኑ አስተውለዋል።

ፍሎረንስ ናይቲንጌል (1820-1910) የተባለችው ነርስ በክራይሜያ ጦርነት የተጎዱትን የብሪታንያ ወታደሮች በምታስታምምበት ጊዜ በሙያዋ ከፍተኛ ዝና አግኝታ ነበር። እንዲህ ብላ ጽፋለች፦ “ማታ ማታ ወይም ጠዋት ላይ መስኮት ከመከፈቱ በፊት . . . ሰው ወደተኛበት ክፍል ገብታችሁ ታውቃላችሁ? በክፍሉ ውስጥ ያለው አየር የታፈነና ጥሩ ሽታ የሌለው እንደሆነ አላስተዋላችሁም?” አንድ ሕመምተኛ ለብርድ መጋለጥ ባይኖርበትም እንኳ በሚተኛበት ክፍል ውስጥ ያለው አየር የውጭውን ያህል ንጹሕ መሆን እንደሚገባው ይህች ነርስ መክራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ከሕሙማን ጋር ባሳለፍኩት የረጅም ጊዜ ተሞክሮ እንዳረጋገጥኩት ሕመምተኞች ከንጹሕ አየር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚያስፈልጋቸው ብርሃን ነው፤ . . . የሚያስፈልጋቸውም ማንኛውም ብርሃን ሳይሆን የፀሐይ ብርሃን ነው።” በተጨማሪም በዚያ ዘመን ብዙ ሰዎች፣ አንሶላዎችንና የመኝታ ልብሶችን ፀሐይ ላይ ማስጣት ለጤና ጠቃሚ እንደሆነ ያምኑ ነበር።

ከ1800ዎቹ ዓመታት ወዲህ ሳይንስ ብዙ እድገት አድርጓል፤ ሆኖም በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች በቀደሙት ዘመናት የነበሩት እነዚህ የሕክምና ዘዴዎች ትክክል መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለምሳሌ፣ በ2011 በቻይና የተደረገ አንድ ጥናት፣ የተጨናነቁና በቂ አየር የማያገኙ የኮሌጅ ማደሪያ ክፍሎች “በመተንፈሻ አካላት ላይ ከሚከሰቱ የተለያዩ የኢንፌክሽን ዓይነቶች” ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አረጋግጧል።

የዓለም የጤና ድርጅት፣ ከውጭ የሚመጣ አየር በሕንፃዎች ውስጥ እንዲዘዋወር ማድረግ ኢንፌክሽንን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ አረጋግጧል። የሕክምና ተቋማት በሕንፃዎቻቸው ውስጥ ንጹሕ አየር እንዲናፈስ ማድረጋቸው ለኢንፌክሽን የመጋለጥ አጋጣሚን በእጅጉ እንደሚቀንስ የዓለም የጤና ድርጅት በ2009 ባወጣው መመሪያ ላይ ገልጿል። *

ሆኖም እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘ሐሳቡ ጥሩ ነው። ግን ለዚህ ምን ሳይንሳዊ ማስረጃ አለ? የፀሐይ ብርሃንና አየር ኢንፌክሽንን የሚከላከሉት እንዴት ነው?’

ተፈጥሯዊ ፀረ ጀርሞች

በዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች አንዳንድ መልሶች ይሰጡናል። በዚያ የሚሠሩ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ጎጂ ባክቴሪያ የተጫነ አንድ ባዮሎጂያዊ የጦር መሣሪያ ለንደን ላይ ቢፈነዳ አየሩ ለምን ያህል ጊዜ አደገኛ ሆኖ እንደሚቆይ አጥንተው ነበር። ተመራማሪዎቹ አየር ወለድ የሆኑ ተሕዋስያን ለምን ያህል ጊዜ በሕይወት እንደሚቆዩ ለማወቅ ኢ ኮላይ ተብለው የሚጠሩትን ባክቴሪያዎች በሸረሪት ድር ላይ አንጠልጥለው አየር ላይ እንዲቆዩ አደረጉ። ሙከራው የተደረገው በማታ ነበር፤ ምክንያቱም የፀሐይ ብርሃን ባክቴሪያዎቹን እንደሚገድላቸው ይታወቃል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ?

ከሁለት ሰዓት ገደማ በኋላ ባክቴሪያዎቹ በሙሉ ሞቱ። ባክቴሪያዎቹ እዚያው ቦታ በተመሳሳይ የሙቀትና የእርጥበት መጠን በተዘጋ ሣጥን ውስጥ በተደረጉ ጊዜ ግን ሁለት ሰዓት ካለፈ በኋላም እንኳ አብዛኞቹ አልሞቱም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ጀርሞቹ ለአየር ሲጋለጡ በሆነ መንገድ ይሞታሉ ማለት ነው። አየር ጀርሞችን የሚገድልበት ትክክለኛ ምክንያት በግልጽ አልታወቀም። ይሁን እንጂ ተመራማሪዎች “በአየር ውስጥ የሚገኙ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን ወይም ጀርሞችን የሚገድል ተፈጥሯዊ ፀረ ጀርም የሆነ ኬሚካላዊ ውህድ” በአየር ውስጥ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የፀሐይ ብርሃንም ተፈጥሯዊ ፀረ ጀርም ነው። ዘ ጆርናል ኦቭ ሆስፒታል ኢንፌክሽን የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “አየር ወለድ ኢንፌክሽን ከሚያመጡት ተሕዋስያን መካከል አብዛኞቹ የፀሐይ ብርሃንን መቋቋም አይችሉም።”

ከእነዚህ ነገሮች ተጠቃሚ ልትሆን የምትችለው እንዴት ነው? ከቤትህ ወጣ ብለህ ፀሐይ ለመሞቅና ንጹሕ አየር ለመተንፈስ የተወሰነ ጊዜ መመደብ ትችላለህ። ይህም ለጤንነትህ ጠቃሚ መሆኑ አይካድም።

^ አን.8 በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሳ መስኮት ክፍት አድርጎ መተው አመቺ ላይሆን ይችላል። ከእነዚህ መካከል በውጭ ያለው አየር መበከል፣ አካባቢው ድምፅ የሚበዛበት መሆኑ፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ሕጎችና የደኅንነት ሁኔታ ይገኙበታል።