በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

4ኛው ቁልፍ—ጤንነትህን ጠብቅ

4ኛው ቁልፍ—ጤንነትህን ጠብቅ

4ኛው ቁልፍ—ጤንነትህን ጠብቅ

“አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል።” (ምሳሌ 22:3) ቀላል የሆኑ የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድህ ከበሽታና ከሥቃይ ያድንሃል፤ እንዲሁም ጊዜህና ገንዘብህ እንዳይባክን ይረዳሃል።

◯ ንጽሕናህን ጠብቅ። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል “እጅን መታጠብ፣ የተላላፊ በሽታዎችን ሥርጭት ለመግታት እንዲሁም ምንጊዜም ጤነኛ ሆነህ ለመኖር ልታደርገው የምትችል እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው” በማለት ዘግቧል። ከተላላፊ በሽታዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የሚተላለፉት እጅ ባለመታጠብ እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ እጅህን ታጠብ። በተለይ ከመብላትህ፣ ምግብ ከማዘጋጀትህ ወይም ቁስል ከማከምህ አልፎ ተርፎም ቁስል ከመንካትህ በፊት እጅህን ታጠብ፤ እንስሳ ከነካህ፣ መጸዳጃ ቤት ከተጠቀምክ ወይም የሕፃን ሽንት ጨርቅ ከቀየርክ በኋላም መታጠብ ይኖርብሃል።

እጅን በውኃና በሳሙና መታጠብ አልኮልነት ባለው የእጅ ማጽጃ ፈሳሽ ከመጠቀም የበለጠ ውጤታማ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው እጃቸውን እንዲታጠቡና ባልታጠበ እጃቸው አፋቸውንና ዓይናቸውን እንዳይነካኩ ካሠለጠኗቸው ይበልጥ ጤነኞች ይሆናሉ። በየቀኑ ገላን መታጠብ፣ ልብሶችህና አንሶላዎችህ ንጹሕ ብሎም ጥሩ ጠረን ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ለተሻለ ጤንነት አስተዋጽኦ ያበረክታል።

◯ ተላላፊ በሽታ እንዳይዝህ ተጠንቀቅ። ጉንፋን ወይም ኢንፍሉዌንዛ ከያዘው ሰው ጋር ንኪኪ እንዳይኖርህ ተጠንቀቅ፤ ወይም የመመገቢያ ዕቃዎችን በጋራ ከመጠቀም ተቆጠብ። በበሽታው የተያዙ ሰዎች ምራቅና የአፍንጫ ፈሳሽ በሽታው ወደ አንተ እንዲተላለፍ ሊያደርግ ይችላል። እንደ ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ እንዲሁም ኤች አይ ቪ/ኤድስ ያሉት በሽታዎች በዋነኝነት የሚተላለፉት በፆታ ግንኙነት፣ ፅፆችን በደም ሥር በመውሰድና ደም በመውሰድ ነው። ክትባት መውሰድ አንዳንዶቹን ተላላፊ በሽታዎች ለመከላከል ሊረዳ ይችላል፤ ሆኖም አስተዋይ ሰው ተላላፊ በሽታ ካለው ሰው ጋር በሚሆንበት ጊዜ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። ነፍሳት እንዳይነድፉህ ጥንቃቄ አድርግ። ትንኞች ወይም ሌሎች በሽታ አስተላላፊ ነፍሳት በሚበዙበት ሰዓት ሰውነትህ ሳይሸፈን ከቤት ውጭ አትቀመጥ ወይም አትተኛ። በተለይ ልጆች የአልጋ አጎበር እንዲኖራቸው አድርግ፤ ወይም ነፍሳት ማባረሪያ መድኃኒቶችን ተጠቀም። *

◯ የቤትህን ንጽሕና ጠብቅ። ቤትህ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ንጹሕ እንዲሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ አድርግ። ውኃ ሊያቆሩና የወባ ትንኞች ሊራቡባቸው የሚችሉ ቦታዎችን አጥፋ። በየቦታው የተዝረከረከ፣ የተበላሸና ያልተሸፈነ ምግብ ብሎም ጥራጊ ነፍሳትንና ተባዮችን ይስባል፤ እነዚህ ነፍሳት ረቂቅ ተሕዋስያን እንዲራቡ አመቺ ሁኔታ በመፍጠር በሽታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። መጸዳጃ ቤት ከሌለህ እንዲሁ በየሜዳው ከመጸዳዳት ይልቅ ሽንት ቤት ቆፍር። የዓይን ሕመምንና ሌሎች በሽታዎችን የሚያስተላልፉ ዝንቦች እንዳይራቡ ለሽንት ቤቱ ክዳን አበጅለት።

◯ በራስህ ላይ ጉዳት እንዳታደርስ ተጠንቀቅ። ሥራ ስትሠራ፣ ብስክሌት፣ ሞተር ብስክሌት ወይም መኪና ስትነዳ የጥንቃቄና የደኅንነት ሕጎችን አክብር። ተሽከርካሪህ አደጋ የማያስከትል መሆኑን አረጋግጥ። የዓይን መከላከያ፣ የራስ መሸፈኛ፣ ለእግርህ ደግሞ ጫማና ካልሲ አድርግ። እንዲሁም ከመጠን ያለፈ ድምፅ ካለ ጆሮህ ላይ መከላከያ አድርግ፤ በተጨማሪም መኪና ስትነዳ ቀበቶ እሰር። የቆዳ ካንሰርና የቆዳ መሸብሸብ ሊያስከትል ስለሚችል ለፀሐይ ብዙ አትጋለጥ። የምታጨስ ከሆነ አቁም። አሁኑኑ ማጨስ ማቆምህ ለልብ በሽታ፣ ለሳንባ ካንሰርና በአንጎል ውስጥ ደም ለመፍሰስ አደጋ የመጋለጥህን አጋጣሚ በእጅጉ ይቀንሰዋል። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 በነሐሴ 2003 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “በሽታ አስተላላፊ ነፍሳት” የሚለውን የሽፋን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.7 በግንቦት 2010 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “ማጨስ ለማቆም ምን ማድረግ ይቻላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።