በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኝ ልጃችሁ መመሪያ ማውጣት

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኝ ልጃችሁ መመሪያ ማውጣት

ተፈታታኙ ነገር

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ በጣም ጥብቅ እንደሆናችሁ ይነግራችኋል። እናንተ ግን ልጃችሁን ከአደጋ ለመጠበቅ ስለምትፈልጉ እንዲህ አይሰማችሁም። እንዲያውም ‘መመሪያዎቹን ካላላኋቸው ልጄ ችግር ውስጥ መግባቱ አይቀርም!’ ብላችሁ ታስባላችሁ።

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኘው ልጃችሁ ምክንያታዊ ሕጎችን ማውጣት ትችላላችሁ። በመጀመሪያ ግን ልጃችሁ ያወጣችሁለትን መመሪያ ገሸሽ እንዲያደርግ የሚያነሳሳውን ምክንያት መረዳት ያስፈልጋችኋል።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

የተሳሳተ አመለካከት፦ ሁሉም ልጅ ሲጎረምስ መመሪያ አያከብርም፤ ይህ በጉርምስና ዕድሜ ውስጥ የተለመደ ነገር ነው።

እውነታው፦ አንድ ልጅ ወላጆቹ ምክንያታዊ መመሪያዎችን አውጥተው ከእሱ ጋር የሚወያዩ ከሆነ የማመፅ አጋጣሚው በጣም ይቀንሳል።

ምንም እንኳ አንድን ልጅ እንዲያምፅ የሚያደርጉት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ወላጆች የሚያወጧቸው መመሪያዎች ድርቅ ያሉ ወይም የልጁን ዕድሜ ያላገናዘቡ ከሆኑ ወላጆች ሳይታወቃቸው ልጁን በሕጎች ላይ እንዲያምፅ እያበረታቱት ነው። እስቲ ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከቱ፦

  • ድርቅ ያሉ ሕጎች። ወላጆች ሕግ አውጥተው ስለ ሕጎቹ ወይም መመሪያዎቹ ለመወያየት ላይፈልጉ ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ መመሪያዎቹ ለልጁ ከአደጋ እንደሚጠብቀው የደኅንነት ቀበቶ ሳይሆን ጥፍር አድርጎ በማሰር መፈናፈኛ እንደሚያሳጣ ካቴና ይሆኑበታል። በዚህም የተነሳ ወላጆቹ የከለከሉትን ነገር በድብቅ ማድረግ ሊጀምር ይችላል።

  • ዕድሜን ያላገናዘቡ ሕጎች። አንድ ትንሽ ልጅ ለሚያደርገው ነገር ምክንያት ቢጠይቅ “ዝም ብለህ የታዘዝከውን አድርግ!” የሚለው መልስ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል፤ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ግን ከዚያ ያለፈ ነገር ማለትም ለሚያደርገው ነገር ምክንያት እንዲነገረው ይፈልጋል። ደግሞም ልጃችሁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ራሱን ችሎ መኖር ሲጀምር ከባድ ውሳኔዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል። ስለዚህ በእናንተ ቁጥጥር ሥር እያለ ማመዛዘንና ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ ቢማር የተሻለ ነው።

ይሁን እንጂ ልጃችሁ ባወጣችኋቸው መመሪያዎች ሁልጊዜ የሚበሳጭ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

በመጀመሪያ ደረጃ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ገደብ ሊቀመጥላቸው ያስፈልጋል፤ እነሱም ቢሆኑ አይናገሩት እንጂ ገደብ መቀመጡን በውስጣቸው ይፈልጉታል። በመሆኑም መመሪያ አውጡላቸው፤ እንዲሁም መመሪያውን እንዲረዱት አድርጉ። ሌቲንግ ጎ ዊዝ ላቭ ኤንድ ኮንፊደንስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ግልጽ የሆኑ ገደቦች ሲቀመጡላቸውና ወላጅ ምክንያታዊ የሆነ ቁጥጥር እንደሚያደርግላቸው ሲሰማቸው ለችግር በሚዳርጓቸው ምግባሮች የመካፈል አጋጣሚያቸው ይቀንሳል።” በአንጻሩ ደግሞ ለልጆቻቸው ገደብ የሌለው ነፃነት የሚሰጡ ወላጆች እንዲህ ማድረጋቸው በልጆቻቸው ላይ ለሚደርሰው ነገር ደንታ ቢስ እንደሆኑ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ማመፅን ማስከተሉ አይቀርም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 29:15

ታዲያ ሚዛናዊ መሆን የምትችሉት እንዴት ነው? በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ስላወጣችኋቸው መመሪያዎች የሚሰማቸውን እንዲናገሩ አድርጉ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጁ ቤት እንዲገባ የተወሰነለት ሰዓት እንዲሻሻል ከጠየቀ ምክንያቱን ሲናገር አዳምጡት። አንድ ልጅ በደንብ እንዳዳመጣችሁት ከተሰማው በውሳኔያችሁ ባይስማማም እንኳ ውሳኔያችሁን የማክበሩና የመታዘዙ አጋጣሚ ከፍ ያለ ይሆናል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ያዕቆብ 1:19

ይሁንና ውሳኔ ከማድረጋችሁ በፊት የሚከተለውን ሐሳብ ማስታወስ ይኖርባችኋል፦ በጉርምስና ዕድሜ ያሉ ልጆች ማግኘት ከሚገባቸው በላይ ነፃነት እንዲሰጣቸው መጠየቅ ይቀናቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ ለልጆቻቸው መስጠት የሚገባቸውን ያህል ነፃነት አይሰጡም። ስለዚህ ልጃችሁ የሚያቀርበውን ጥያቄ በጥሞና አስቡበት። ልጃችሁ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንደሆነ ያሳያል? የጠየቀውን ነገር ለመፍቀድ ሁኔታዎች ያስገድዳሉ? አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ልጃችሁ የጠየቀውን ነገር ለመፍቀድ ፈቃደኞች ሁኑ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ዘፍጥረት 19:17-22

ልጃችሁ አመለካከቱን ሲገልጽ ከማዳመጥ በተጨማሪ እናንተ የሚያሳስቧችሁን ነገሮች እንዲያውቅ አድርጉ። እንዲህ በማድረግ ልጃችሁ እሱ የሚፈልገውን ነገር ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ስሜት ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ልታስተምሩት ትችላላችሁ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ 1 ቆሮንቶስ 10:24

በመጨረሻም ውሳኔ አድርጉ እንዲሁም ምክንያታችሁን ግለጹ። ልጃችሁ በውሳኔያችሁ ባይደሰትም እንኳ ስሜቱን ሲገልጽ የሚያዳምጡት ወላጆች ያሉት በመሆኑ መደሰቱ አይቀርም። በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለ ልጃችሁን አዋቂ ሰው እንዲሆን እያሠለጠናችሁት እንደሆነ አስታውሱ። ምክንያታዊ መመሪያዎችን ማውጣታችሁና ስለ መመሪያዎቹ መወያየታችሁ ልጃችሁ ወደፊት ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንዲሆን ይረዳዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 22:6