በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

90 ዓመታት የፈጀ መዝገበ ቃላት

90 ዓመታት የፈጀ መዝገበ ቃላት

በ1621 አንድ ጣሊያናዊ አሳሽ ፐርሴፖሊስ በምትባል በጥንቷ ፋርስ የምትገኝ ከተማ ፍርስራሽ ውስጥ በማይታወቁ ፊደላት የተጻፈ ጽሑፍ አገኘ። በ1800ዎቹ ዓመታት ደግሞ በኢራቅ የመሬት ቁፋሮ ያካሄዱ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች፣ በሸክላ ጽላቶችና በቤተ መንግሥት ግድግዳዎች ላይ የተቀረጹ በርካታ ጽሑፎች አገኙ፤ እነዚህ ጽሑፎች ጣሊያናዊው አሳሽ ካገኘው ጋር በሚመሳሰሉ ፊደላት የተጻፉ ነበሩ። ጽሑፎቹ የተዘጋጁት እንደ ዳግማዊ ሳርጎን፣ ሃሙራቢና ዳግማዊ ናቡከደነፆር ያሉ ገዥዎች ይጠቀሙባቸው በነበሩ የሜሶጶጣሚያ ቋንቋዎች ነው። የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉት ፊደላት ኪዩኒፎርም የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

የጥንቷን ሜሶጶጣሚያ ታላላቅ ሥልጣኔዎች ለማወቅ እነዚህን ጽሑፎች መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህም ምክንያት የእነዚህን ሰነዶች ትርጉም ለማወቅ የሚጥሩት ምሁራን፣ የአካድ ቋንቋ አጠቃላይ መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘቡ፤ ይህ ቋንቋ ከአሦርና ከባቢሎን ቋንቋዎች ጋር በጣም ይቀራረባል።

ይህንን ተፈታታኝ ሥራ ያከናወነው በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የምሥራቃዊ አገሮች ጥናት ተቋም ነው፤ ሥራው የተጀመረው በ1921 ሲሆን ከ90 ዓመታት በኋላ ማለትም በ2011 ተጠናቅቋል። በ26 ጥራዞች የተዘጋጀውና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ የአሦር ቋንቋ መዝገበ ቃላት 9,700 ገጾች አሉት። መዝገበ ቃላቱ ከ2500 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከ 100 ዓ.ም. በሶርያ፣ በቱርክ፣ በኢራቅና በኢራን ይነገሩ የነበሩትን ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ያካትታል።

በ26 ጥራዞች የተዘጋጀው የአሦር ቋንቋ መዝገበ ቃላት ከ9,700 የሚበልጡ ገጾች አሉት!

ይህ መዝገበ ቃላት ይህን ያህል ሰፊ የሆነው ለምንድን ነው? ለማዘጋጀት ይህን ሁሉ ዓመት የፈጀው ለምንድን ነው? የተዘጋጀውስ ማን እንዲገለገልበት ታስቦ ነው?

መዝገበ ቃላቱ ያካተታቸው ነገሮች

በቺካጎ የሚገኘው የምሥራቃዊ አገሮች ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ጊል ስታይን “መዝገበ ቃላቱ የቃላት ዝርዝር የያዘ መጽሐፍ ብቻ አይደለም” ብለዋል። ከዚህ ይልቅ “ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መጽሐፍ የእያንዳንዱን ቃል አመጣጥና ጥቅም ላይ ይውል የነበረባቸውን መንገዶች በዝርዝር የሚያብራራ በመሆኑ በሜሶጶጣሚያ ስለነበረው ታሪክ፣ ማኅበረሰብ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሕግና ሃይማኖት የሚያወሳ የባሕል ኢንሳይክሎፒዲያ ነው ማለት ይቻላል። የሜሶጶጣሚያን ሥልጣኔ የሚያሳዩ የጽሑፍ ሰነዶችን ለመመርመር የሚፈልግ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖር ምሁር ሊኖረው የሚገባ የምርምር መሣሪያ ነው።”

አዘጋጆቹ ገና ሥራውን ሲጀምሩ እንደተገነዘቡት “የአንድ ቃል ትርጉም በሚገባ እንዲገለጽ ከተፈለገ ቃሉ የሚገኝባቸውን ቦታዎች በሙሉ ለቅሞ ማግኘት ያስፈልጋል፤ ከዚህም ሌላ ቃሉ በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ ከአገባቡና ጥቅም ላይ ከዋለበት መንገድ አንጻር ትርጉሙን ለማወቅ እንዲቻል በዙሪያው ያለውን ሐሳብም መመልከት ያስፈልጋል።” በዚህም የተነሳ መዝገበ ቃላቱ፣ ፍቺ የተሰጣቸው ቃላት ከሚገኙባቸው የጥንቶቹ የኪዩኒፎርም ጽሑፎች ላይ የተወሰዱ ክፍሎችንና ትርጉማቸውን አካትቶ የያዘ መጽሐፍ ሆነ።

ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ ስለ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የሚያወሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኪዩኒፎርም ጽሑፎች ተገኝተዋል። የአካድ ቋንቋ (የአሦርና የባቢሎን ቋንቋ) በጥንቶቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሙሉ የጋራ መግባቢያ ነበር። በዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ያዘጋጁ፣ በንግድ እንቅስቃሴዎች ይካፈሉ እንዲሁም እንደ ሒሳብ፣ ሥነ ፈለክና አስማት ስላሉት መስኮች ምርምር ያደርጉ ነበር፤ ከዚህም ሌላ ሕግ ያረቅቁ፣ ሙያዎችን ይፈጥሩና ያዳብሩ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ያከናውኑ ነበር። በዚህ ምክንያት በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ያሰፈሯቸው ጽሑፎች በርካታ መረጃዎች የያዙ ናቸው።

እነዚህ ጽሑፎች የያዙት መረጃ እንግዳ ስለሆነ ሥልጣኔ የሚገልጽ አይደለም። በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የአሦራውያን ባሕልና ቋንቋ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑትና ለ30 ዓመታት ያህል በተለያዩ ጊዜያት በዚህ ፕሮጀክት የተካፈሉት ማቲው ስቶልፐር እንዲህ ብለዋል፦ “በጽሑፎቹ ላይ የተንጸባረቀው አብዛኛው ሐሳብ አዲስ አይደለም። ሰዎች የተሰማቸውን ፍርሃትና ቁጣቸውን እንዲሁም የፍቅር ጥያቄዎችንና መግለጫዎችን አስፍረዋል።” ፕሮፌሰሩ አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “በእነዚህ ጽሑፎች ላይ አንዳንድ ነገሥታት ታላቅነታቸውን የገለጹ ሲሆን ሌሎች ሰዎች ደግሞ ነገሥታቱ ያን ያህል ታላቅ የሚባሉ እንዳልሆኑ የሚገልጽ ሐሳብ አስፍረዋል።” በዘመናዊቷ ኢራቅ በምትገኘው በኑዚ ደግሞ ባሏ የሞተባት ሴት ስለነበራት የውርስ ክርክር እንዲሁም የመስኖ እርሻን፣ በውሰት የተወሰደ አህያንና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት ስለተነሱ ውዝግቦች የሚገልጽ 3,500 ዓመት ዕድሜ ያለው ሰነድ ተገኝቷል።

በእርግጥ ሥራው ተጠናቅቋል?

በመላው ዓለም የሚኖሩ የአሦራውያንን ባሕልና ቋንቋ የሚያጠኑ ምሁራን ለዚህ ሥራ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የተቋሙ ሠራተኞች ባለፉት አሥርተ ዓመታት ስለተለያዩ ቃላት መረጃ የያዙ ወደ 2,000,000 የሚጠጉ ካርዶችን ሲያዘጋጁ ቆይተዋል። ከዚያም የመጀመሪያው ጥራዝ በ1956 ታተመ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ 25 ተጨማሪ ጥራዞች ከሥር ከሥር ታትመዋል። ሙሉው መጽሐፍ የሚሸጠው በ2,000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ቢሆንም ኢንተርኔት ላይ ሙሉውን መረጃ በነፃ ማግኘት ይቻላል።

ይህን መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት 90 ዓመታት ፈጅቷል። እንደዚያም ሆኖ በዚህ መጠነ ሰፊ ሥራ የተካፈሉት ምሁራን መዝገበ ቃላቱ ያላሟላቸው ነገሮች እንዳሉ አይክዱም። በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፈ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ምሁራኑ አሁንም ቢሆን የአንዳንድ ቃላትን ትርጉም አያውቁም፤ ከዚህም በላይ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮች ስለሚገኙ ሥራው . . . በሂደት ላይ ነው።”