በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በጉግል የመረጃ መፈለጊያ ድረ ገጽ አማካኝነት የብልግና ምስሎችን የሚያመለክተውን ቃል በመጠቀም የተደረጉት ፍለጋዎች ከ2004 ወዲህ በሦስት እጥፍ ጨምረዋል።”—ዚ ኢኮኖሚስት፣ ብሪታንያ

“አንዲት [ሩሲያዊት] ወጣት ስታገባ ማወቅ ያለባት ነገር አለ፤ ይኸውም በባለቤቷ የመደብደቧ ወይም በመካከላቸው ግጭት በሚኖርበት ጊዜ ባለቤቷ በእሷ ላይ አካላዊ ጥቃት የመሰንዘሩ አጋጣሚ 60 በመቶ ገደማ እንደሆነ ነው።” —መስኮቭስኪ ኖቨስቲ፣ ሩሲያ

“በዩናይትድ ኪንግደም ካሉት የሳይንስ ሊቃውንት ወይም ሐኪሞች መካከል ከሰባቱ አንዱ፣ የሥራ ባልደረቦቹ ምርምር ሲያደርጉ ወይም ጽሑፍ ሲያዘጋጁ መረጃዎችን ሆን ብለው አዛብተው አሊያም አጭበርብረው እንደሚያቀርቡ ተመልክቷል።”—ብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል፣ ብሪታንያ

“ከ1971 ወዲህ በዩናይትድ ስቴትስ ከካንሰር በሽታ መዳን የቻሉ ሰዎች ቁጥር በአራት እጥፍ በመጨመር 12 ሚሊዮን ገደማ ደርሷል። . . . ብዙ ሰዎች መዳን እንዲችሉ በአብዛኛው አስተዋጽኦ ያደረገው በሽታው ቶሎ መታወቁ፣ ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የሕክምና ዘዴዎች መኖራቸውና ሕመምተኞች ሕክምናቸውን መከታተላቸው ነው።”—ዩሲ በርክሌይ ዌልነስ ሌተር፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በ2011 የገና በዓል ከመከበሩ ትንሽ ቀደም ብሎ በቤተልሔም በሚገኘው ቸርች ኦቭ ኔቲቪቲ በተባለው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ 100 የሚያህሉ የተቀናቃኝ ቡድኖች ቀሳውስትና መነኮሳት ተደባድበው ነበር። የፖሊስ አዛዡ ስለዚህ ግጭት ሲናገር “በየዓመቱ የሚፈጠር . . . ተራ ችግር ነው” ብሏል። አክሎም “በግጭቱ ውስጥ የነበሩት በሙሉ የአምላክ ሰዎች ስለሆኑ ማንም አልታሰረም” በማለት ተናግሯል።—ሮይተርስ የዜና አገልግሎት፣ ዩናይትድ ስቴትስ

አፍሪካን የሚያቋርጥ ረጅም አረንጓዴ ግንብ

የአፍሪካ ኅብረት በረሃማነትን ለመቀነስ እንዲሁም አካባቢውን አረንጓዴና ለምለም ለማድረግ በማሰብ በ2007 አንድ ፕሮጀክት ጀምሮ ነበር። በስተ ምዕራብ ከምትገኘው ከሴኔጋል ጀምሮ በስተ ምሥራቅ እስካለችው እስከ ጅቡቲ ድረስ ያሉ 11 አገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተስማሚ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን እየተከሉ ነው፤ ዓላማቸው 7,600 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 15 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውን አካባቢ በደን መሸፈን ነው። በዳካር፣ ሴኔጋል የሚገኘው የቼክ አንታ ዲኦፕ ዩኒቨርሲቲ የዕፅዋት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት አሊዩ ጊሴ “ደን የሚመነጥሩ ሰዎች የማይፈልጓቸው ዓይነት የዕፅዋት ዝርያዎችን መትከል አለብን” ብለዋል። በዚህ መንገድ በደን የተሸፈኑት አካባቢዎች፣ ተፈጥሮ ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ የሚያስችሉ ከመሆኑም ሌላ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከዚህ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋሉ።

የምናዛጋው ለምንድን ነው?

የሳይንስ ሊቃውንት፣ በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው አብዛኛውን ጊዜ በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ የሚያዛጋው ለምን እንደሆነ መረዳት አልቻሉም። በማህፀን ውስጥ ያሉ ሕፃናት እንኳ ያዛጋሉ። ጃርቶች፣ ሰጎኖች፣ እባቦች እንዲሁም ዓሦችም ጭምር ያዛጋሉ። በዚህ ረገድ እርስ በርስ የሚጋጩ የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች ያሉ ቢሆንም አንዳቸውም ሁሉንም ተመራማሪዎች የሚያሳምኑ አይደሉም። በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት፣ አብዛኛውን ጊዜ በአማካይ ለስድስት ሴኮንዶች ያህል በሚቆየው በዚህ ክንውን አማካኝነት የሚገባው አየር አንጎላችን ተጨማሪ ኦክስጅን እንዲያገኝ እንደሚያደርግ ሐሳብ አቅርበዋል። ይሁንና ሳይንስ ኒውስ እንደገለጸው “ተመራማሪዎች ይህን ሐሳብ የሚደግፍ ማስረጃ እስካሁን ድረስ አላገኙም።” በአይጦች ላይ የተካሄዱ አዳዲስ ጥናቶች ደግሞ “ማዛጋት፣ አንጎል በጣም ሲሞቀው ሰውነታችን ሙቀትን ለማመጣጠን የሚጠቀምበት መንገድ” እንደሆነ የሚጠቁሙ ይመስላል። ይሁንና ትክክለኛ ምክንያቱን ማንም አያውቅም።