በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ​—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ—ክፍል 5

ለሰው ዘር ሁሉ የሚሆን ምሥራች

መጽሐፍ ቅዱስ​—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ—ክፍል 5

በእነዚህ ስምንት ተከታታይ “የንቁ!” እትሞች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ማለትም በውስጡ ስለያዘው ትንቢት እንመረምራለን። ይህ ተከታታይ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች ናቸው? ወይስ እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፋቸውን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ? እስቲ ማስረጃዎቹን አብረን እንመርምር።

አምላክ ለሰው ልጆች ያስተላለፈው መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህ መልእክት ምሥራች የያዘ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜውንና ጉልበቱን በመጠቀም ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ አውጇል። (ሉቃስ 4:43) ይህ መንግሥት የአምላክ መስተዳድር እንደሆነ፣ ጨቋኝ የሆኑ ሰብዓዊ መንግሥታትን እንደሚያስወግድ ብሎም ሰላም እንደሚያሰፍንና ለሰው ልጆች መከራ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች በሙሉ እንደሚያስወግድ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) በእርግጥም ይህ ታላቅ ምሥራች ነው!

እንዲህ ያለው ምሥራች በስፋት መሰራጨት እንዳለበት ግልጽ ነው። ሆኖም ኢየሱስ በተገደለበት ወቅት የነበሩት ተከታዮች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። ታዲያ ይህ መልእክት ኢየሱስ ሲሞት ተዳፍኖ ይቀር ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው የተከሰተው ነገር ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ትንቢቶች ተናግሮ ነበር፦ (1) ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ ይሰራጫል። (2) ተቃውሞ ቢኖርም ምሥራቹ መሰበኩን ይቀጥላል፤ እንዲሁም (3) አስመሳይ ወይም የሐሰት ክርስቲያኖች ተነስተው ብዙዎችን ያስታሉ። እስቲ እነዚህን ትንቢቶች አንድ በአንድ እንመርምር።

ለብሔራት ሁሉ መታወጅ ያለበት ምሥራች

ትንቢቶች፦

“አስቀድሞም ምሥራቹ ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት።” (ማርቆስ 13:10) “በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 1:8

ፍጻሜ፦ ኢየሱስ ከሞተ ብዙም ሳይቆይ ማለትም በ33 ዓ.ም. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሩሳሌምን በመንግሥቱ መልእክት ሞልተዋት ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በ15 ዓመት ውስጥ በይሁዳና በአጎራባቿ ሰማርያ መልእክቱን ያዳረሱ ከመሆኑም በላይ ወደተለያዩ የሮም ግዛቶች ሚስዮናውያን ተልከው ነበር። በመሆኑም በ61 ዓ.ም. ምሥራቹ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተሰብኳል ሊባል ችሎ ነበር።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

  • ያልተበረዘው ክርስትና በከፍተኛ ፍጥነት ይሰራጭ እንደነበር በሁለተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆኑ ጽሑፎች ይመሠክራሉ። ስዊቶኒየስ የተባለ ሮማዊ የታሪክ ምሁር ክርስቲያኖች በ49 ዓ.ም. እንኳ በሮም እንደነበሩ ጠቅሷል። የቢቲኒያ (የአሁኗ ቱርክ) አገረ ገዥ የነበረው ትንሹ ፕሊኒ፣ የሮም ንጉሠ ነገሥት ለነበረው ለትራጃን በ112 ዓ.ም. ገደማ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ወረርሽኝ” ብሎ ስለጠራው ስለ ክርስትና ሲገልጽ “በከተሞች ብቻ ሳይሆን በየመንደሩና በገጠራማ አካባቢዎች ጭምር ተስፋፍቷል” ብሎ ነበር። አንድ የታሪክ ምሁር ማስረጃዎቹን ከመረመሩ በኋላ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፦ “ከሐዋርያት ዘመን በኋላ፣ ከመቶ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የክርስቲያኖችን የአምልኮ ቦታ በሮም ግዛት ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ማየት የተለመደ ነገር ነበር።”

  • ፕሮፌሰር ሄንሪ ቻድዊክ ዚ ኧርሊ ቸርች የሚል ርዕስ ባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ ‘ክርስትና ሊስፋፋ የቻለው ሊሆኑ የማይችሉ የሚመስሉ በርካታ ክንውኖች በመፈጸማቸው ምክንያት ይመስላል። ክርስትና ይህን ያህል ይሳካለታል ብሎ ማንም ሊጠብቅ አይችልም ነበር።’

ምሥራቹ ያጋጠመው ተቃውሞ

ትንቢት፦

“ሰዎች ለፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኩራብም ትገረፋላችሁ፤ ምሥክርም ይሆንባቸው ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ያቆሟችኋል።”—ማርቆስ 13:9

ፍጻሜ፦ አይሁዳውያንም ሆኑ ሮማውያን ክርስቲያኖችን አሳድደዋል። ክርስቲያኖች እስራት፣ ግርፋትና ድብደባ የደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ ተገድለዋል።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

  • በአንደኛው መቶ ዘመን የኖረው አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር ፍላቭየስ ጆሴፈስ የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ፣ በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች እጅ እንደተገደለ ጽፏል። ገማልያል የተባለ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አባል፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለፍርድ በቀረቡበት ጊዜ ዳኞቹ ጉዳዩን በደንብ እንዲያጤኑ እንዳስጠነቀቃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 5:34-39) አንዳንድ ምሁራን ያዘጋጇቸው ጽሑፎችም ገማልያል የተባለ ሰው በሕይወት እንደኖረና ምክንያታዊ አመለካከት ያለው ሰው እንደነበረ ያረጋግጣሉ።

  • የሮም ንጉሠ ነገሥት የነበረው ኔሮ በ64 ዓ.ም. በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት እንዳስነሳና ከእሱ በኋላ የተነሱ ሌሎች ንጉሠ ነገሥታትም ተመሳሳይ ነገር እንዳደረጉ የታሪክ ጸሐፊዎች ይናገራሉ። የሮም ንጉሠ ነገሥት ትራጃንና ትንሹ ፕሊኒ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች እምነታቸውን ለመካድ እምቢተኛ በሆኑ ክርስቲያኖች ላይ ስለሚፈጸሙ ቅጣቶች ይናገራሉ።

  • ‘ስደት፣ ክርስቲያኖች እንቅስቃሴያቸውን በድብቅ እንዲያከናውኑ ከማስገደድ ይልቅ ተቃራኒ የሆነ ውጤት አስገኝቷል’ በማለት ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፕሮፌሰር ቻድዊክ ተናግረዋል። በስደት ምክንያት የሸሹ ክርስቲያኖች፣ በደረሱበት ቦታ ሁሉ መልእክታቸውን ያሰራጩ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 8:1) እነዚህ ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ቢያገሏቸውም በታማኝነት ጸንተዋል። የኢየሱስ ተከታዮች ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ማሳደር የማይችሉ እንዲሁም “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” ሆነው እንዲህ ማድረግ መቻላቸው በጣም የሚያስደንቅ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 4:13) የታሪክ ምሁራን ‘ወንጌሉ በአነስተኛ ነጋዴዎችና በባለ ሱቆች ዘንድ በቀላሉ እንደተስፋፋ’ ያምናሉ።

ምሁራን፣ የጥንት ክርስቲያኖችን ታሪክ ሲመረምሩ እዚህ ግቡ የማይባሉ ጥቂት ሰዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እየደረሰባቸውም እንኳ ክርስትናን እንዲህ ባለ ፍጥነት ማሰራጨት በመቻላቸው ይደነቃሉ። ይሁንና ኢየሱስ እነዚህ ሊሆኑ የማይችሉ የሚመስሉ ክንውኖች እንደሚፈጸሙ አስቀድሞ ተናግሯል። ቅዱሳን መጻሕፍት የስብከቱ ሥራ የሚቋረጥበት ጊዜ እንደሚመጣም ተንብየዋል።

አስመሳይ ክርስቲያኖች ይነሳሉ

ትንቢቶች፦

“ጨካኝ ተኩላዎች በመካከላችሁ እንደሚገቡና መንጋውን በርኅራኄ እንደማይዙ አውቃለሁ፤ ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) “በእናንተም መካከል ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ። እነዚህ ሰዎች ጥፋት የሚያስከትል ኑፋቄ በስውር ያስገባሉ፤ . . . በእነሱም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል።”—2 ጴጥሮስ 2:1, 2

ፍጻሜ፦ የክርስቲያን ጉባኤ ጨካኝ፣ አታላይና የሥልጣን ጥመኛ በሆኑ ግለሰቦች ተበክሎ ነበር።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

  • በእውነተኛው ክርስትና ውስጥ የነበሩና ትልቅ ቦታ የተሰጣቸው ሰዎች፣ የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች ከሞቱ በኋላ የክርስትናን ትምህርት በግሪካውያን ፍልስፍና መበረዝ ጀመሩ፤ በመሆኑም እውነተኛው ክርስትና ቀስ በቀስ መዳፈን ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ የቀሳውስት ቡድን ብቅ ያለ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ባላቸው ሥልጣንና ሀብት የፖለቲካ ገዥዎችን መምሰል ጀመሩ። የታሪክ ምሁራን “ክርስትና” በሮም ግዛት የመንግሥት ሃይማኖት ሲሆን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው እውነተኛ ጉባኤ ርዝራዡ እንኳ እንደጠፋ ይናገራሉ።

  • ባለፉት መቶ ዘመናት ይህ የተበረዘ ክርስትና በርካታ የግፍና የስግብግብነት ድርጊቶችን ፈጽሟል። ቀሳውስት፣ የኢየሱስ ተከታዮች መሆናቸውን በተግባር ከማሳየት ይልቅ የኢየሱስን የስብከት ዘዴ የሚከተሉትንና መጽሐፍ ቅዱስን ብዙኃኑ በሚናገረው ቋንቋ ለመተርጎም ጥረት የሚያደርጉትን ሰዎች አሳድደዋል።

የሐሰት ክርስትና ከፍተኛ ሥልጣን ጨብጦ በቆየባቸው ዘመናት ሁሉ ምሥራቹ ሙሉ በሙሉ የጠፋ ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ ምሥራቹ በመጨረሻው ዘመን እንደገና እንደሚያንሰራራ ኢየሱስ ተንብዮአል። ኢየሱስ ይህን ጊዜ ከመከር ወቅት ጋር አመሳስሎታል፤ በዚህ ወቅት፣ በስንዴ የተመሰሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች በእንክርዳድ ከተመሰሉ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ይለያሉ። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43) በዚያ ጊዜ ምሥራቹ እንደሚሰበክ የተነገረው ትንቢት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል። (ማቴዎስ 24:14) በሚቀጥለው እትም ላይ ስለዚህ አስደናቂ ትንቢት እንመለከታለን።