በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

እውነተኛ ጓደኞቼ እነማን ናቸው?

እውነተኛ ጓደኞቼ እነማን ናቸው?

“ኮሪ የአስተሳሰብ አድማሴን አስፍታልኛለች። ከእሷ ጋር ስሆን ከሰዎች ጋር እተዋወቃለሁ፤ አዳዲስ ነገሮችን እሞክራለሁ፤ እንዲሁም በምንሄድበት ቦታ ሁሉ ደስ የሚል ጊዜ እናሳልፋለን። ከኮሪ ጋር የመሠረትኩት ጓደኝነት ቃል በቃል ሕይወቴን ለውጦታል!”​—ታራ *

እንዲህ ዓይነት ጓደኝነት መመሥረት የማይቻል ይመስልሃል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ጓደኛህ መሆን የሚችሉ ሰዎች በዙሪያህ ሞልተዋል። ይህ ርዕስ እንዲህ ዓይነት ጓደኞች እንድታገኝ ይረዳሃል።

‘በጓደኛ የተከበብኩ ቢሆንም ጓደኛ ግን የለኝም።’ የ21 ዓመቷ ሼይነ፣ በዙሪያዋ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም የቅርብ ጓደኛ ባለማግኘቷ የተሰማትን ስሜት የገለጸችው እንዲህ በማለት ነበር። ይህ ስሜት በተለይ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በሚጠቀሙ ወጣቶች ዘንድ የተለመደ ነገር ሳይሆን አይቀርም። የ22 ዓመቷ ሴሬና እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ‘የጓደኞች ዝርዝር’ ሲኖራችሁ ተወዳጅና ተፈላጊ መስላችሁ ልትታዩ ትችላላችሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ ዝርዝር ምንም ትርጉም የሌለው ሊሆን ይችላል።” *

በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን አድራሻ የያዘ ‘የጓደኞች ዝርዝር’ ከሚኖርህና ጥቂት እውነተኛ ጓደኞች ከሚኖሩህ የቱን ትመርጣለህ? ሁለቱም የየራሳቸው ጥቅም ቢኖራቸውም እውነተኛ ጓደኛ ግን ችግር ሲያጋጥምህ ሊደርስልህና ጥሩ ሰው እንድትሆን ሊያበረታታህ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 16:17, 18) ከዚህ በታች የተገለጹት መመዘኛዎች፣ ከምታውቃቸው ሰዎች መካከል ከእውነተኛ ጓደኛ የሚጠበቁትን ባሕርያት የሚያሳዩት እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ያስችሉሃል።

እውነተኛ ጓደኛ እምነት ይጣልበታል

“ጓደኛዬ ሚስጥሮቿን ስለምትነግረኝ እኔም ሚስጥሬን ልነግራት እንደምችል ተሰማኝ። ስለዚህ አንድ ቀን አንድን ልጅ እንደወደድኩት ነገርኳት። ይህ ግን በጣም ትልቅ ስህተት ነበር! ልክ ከኔ ተለይታ እንደሄደች ወሬውን ነዛችው!”​ቤቨርሊ

“ለጓደኛዬ ለአለን ምንም ነገር ልነግረው እችላለሁ፤ ደግሞም ለሌላ ሰው እንደማያወራ እርግጠኛ ነኝ።”​ካልቪን

ከላይ ከተገለጹት ወጣቶች መካከል እውነተኛ ጓደኛ ያለው ማን ነው? ከጓደኞችህ መካከል አምነኸው ሚስጥርህን ልትነግረው የምትችለው ለማን ነው? * መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል” በማለት ይናገራል።​—ምሳሌ 17:17 የ1954 ትርጉም

ከዚህ በታች እምነት የሚጣልባቸው ሆነው ያገኘሃቸውን የሁለት ጓደኞችህን ስም ጻፍ።

  1. ․․․․․

  2. ․․․․․

እውነተኛ ጓደኛ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ያደርጋል

“በማንኛውም ጓደኝነት፣ አንዱ ከሌላው ይልቅ ብርቱ የሚሆንበት ጊዜ ማጋጠሙ ያለ ነገር ነው። እውነተኛ ጓደኛ እንደደከምክ ሲመለከት ቅድሚያውን ወስዶ ያበረታታሃል። እርግጥ ነው፣ ጓደኛህ ችግር ሲደርስበት አንተም እንዲሁ እንደምታደርግለት ይተማመንብሃል።”​ኬሊ

“እናቴ በሞተችበት ወቅት የተዋወቅኳት አንዲት ጓደኛ ነበረችኝ። በጊዜው ብዙ ያልተቀራረብን ቢሆንም አብረን ወደ አንድ ሠርግ ለመሄድ አስበን ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የእናቴ የቀብር ሥነ ሥርዓትና ሠርጉ አንድ ቀን ላይ ዋለ። ጓደኛዬ ወደ ሠርግ መሄዷን ትታ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘቷ አስገረመኝ። በዚያን ጊዜ እውነተኛ ጓደኛ እንደሆነች ተረዳሁ!”​ሊና

ከጓደኞችህ መካከል የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የሚያሳዩት የትኞቹ ናቸው? እውነተኛ ጓደኛ “የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም” ያስቀድማል።​—1 ቆሮንቶስ 10:24

ከዚህ በታች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንዳላቸው ያሳዩ የሁለት ጓደኞችህን ስም ጻፍ።

  1. ․․․․․

  2. ․․․․․

እውነተኛ ጓደኛ ጥሩ ሰው እንድትሆን ይረዳሃል

“አንዳንድ ሰዎች የምመራበትን የሥነ ምግባር መመሪያ የሚያስጥሰኝ ወይም ከሕሊናዬ ጋር የሚጋጭ ነገር ማድረግ የሚጠይቅብኝ ቢሆንም እንኳ ለእነሱ ታማኝ እንድሆን ወይም ከእነሱ ጋር እንድስማማ ይጠብቃሉ። እነዚህ እውነተኛ ጓደኞች አይደሉም።”​ናዲን

“እህቴ የልብ ጓደኛዬ ናት። አቅሜ የሚፈቅደውን ሁሉ እንዳደርግ የምታበረታታኝ ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ተግባቢ እንድሆን ትረዳኛለች። መስማት የማልፈልገው ነገር ቢሆንም እንኳ እውነቱን ትነግረኛለች።”​ኤሚ

“የልብ ጓደኞቼ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ ችግሬን እንድረሳ ከመንገር ይልቅ በሐቀኝነት ምክር ይሰጡኛል። ሌሎቹ ግን አንድም በራሴ እንድወጣው ይተዉኛል አሊያም ችግሩን እንድረሳው ለማድረግ ይሞክራሉ። የደረሰብኝን ችግር አይተው እንዳላዩ ይሆናሉ።”​ሚኪ

“ጓደኛዬ በውስጤ ያለውን ሊዳብር የሚችል ችሎታ ከማንም በላይ ስለምትረዳ ግቦቼ ላይ እንድደርስ ታበረታታኛለች። አስፈላጊ ሲሆን ጉድለቴን ፍርጥርጥ አድርጋ ትነግረኛለች፤ እኔም ይህን እወድላታለሁ!”​ኢሌን

ጓደኞችህ ችሎታህን ሙሉ በሙሉ እንድትጠቀምበት ይረዱሃል? ወይስ በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስትል አቋምህን ለማላላት ትገደዳለህ? ምሳሌ 13:20 “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” ይላል።

ከዚህ በታች ጥሩ ሰው እንድትሆን የረዱህን የሁለት ጓደኞችህን ስም ጻፍ።

  1. ․․․․․

  2. ․․․․․

ከላይ በተገለጹት ሦስት መመዘኛዎች ሥር የጻፍካቸውን ስሞች ተመልከት። በሦስቱም መመዘኛዎች ሥር ስሙን የመዘገብከው ሰው ካለ እሱ እውነተኛ ጓደኛ ነው! ከጓደኞችህ መካከል ከላይ የተገለጹትን መመዘኛዎች የሚያሟላ ሰው ማግኘት ከተቸገርክ ግን ተስፋ አትቁረጥ። እውነተኛ ጓደኛ መሆን የሚችሉ ሰዎች በዙሪያህ አሉ። እነሱን ማግኘት ግን ጊዜ ሊወስድብህ ይችላል። * እስከዚያ ድረስ ግን ጥሩ ጓደኛ ለመሆን የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። የ20 ዓመቷ ኤለን እንዲህ ብላለች፦ “ምንጊዜም ከጓደኞቼ ጎን ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ። የሚሠራ ሥራ ሲኖራቸው እረዳቸዋለሁ። ማውራት ሲፈልጉ አዳምጣቸዋለሁ። የሚያስለቅስ ነገር ሲያጋጥማቸው ደግሞ አጽናናቸዋለሁ።”

እርግጥ ነው፣ ብዙ የምትቀርባቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሌሎችን አግልሎ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ብቻ ከመወዳጀት የተሻለ ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:13) ይሁን እንጂ ‘ለክፉ ቀን የሚወለዱ’ ጥቂት እውነተኛ ጓደኞች ቢኖሩህ ደስ አይልህም? (ምሳሌ 17:17) የ20 ዓመቷ ጂን “ብዙ ሰዎችን ማወቅ ጥሩ ነው” በማለት ትናገራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ግን ተሰቅለው ሲታዩ የሚያምሩ፣ ስትለብሳቸው ግን ልክህ ያልሆኑ ብዙ ልብሶች የሞሉበት ቁም ሣጥን ባለቤት ከመሆን ጋር ይመሳሰላል። ደጋግመህ የምትለብሰው የሚስማሙህን ጥቂት ልብሶች ብቻ ነው። ከቅርብ ጓደኞችህ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።”

 

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.5 ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌና በነሐሴ 2011 ንቁ! መጽሔት ላይ በወጣው “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው ዓምድ ሥር ያሉትን ርዕሶች ተመልከት።

^ አን.10 አንዳንድ ጊዜ ምስጢር መጠበቅ ጥበብ ላይሆን ይችላል፤ ለምሳሌ ያህል ጓደኛህ ከባድ ጥፋት ቢፈጽም፣ ራሱን የመግደል ሐሳብ ቢኖረው ወይም ራሱን በሚጎዳ አንድ ዓይነት ልማድ የተጠመደ ቢሆን ይህን ጉዳይ ሚስጥር አድርጎ መያዝ ጥበብ አይደለም። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የታኅሣሥ 2008 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 19-21 እና የግንቦት 2008 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 26-29⁠ን ተመልከት።

^ አን.30 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በመጋቢት 2009 ንቁ! ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . . የተሻሉ ጓደኞች ያስፈልጉኝ ይሆን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።