በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፀሐይ በማትወጣበት ጊዜ

ፀሐይ በማትወጣበት ጊዜ

ፀሐይ በማትወጣበት ጊዜ

ፊንላንድ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

“ፀሓይ ትወጣለች፤ ትጠልቃለችም፤ ወደምትወጣበትም ለመመለስ ትጣደፋለች” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መክብብ 1:5) ይሁን እንጂ ከአርክቲክ ክልል በስተ ሰሜን በሚገኙ ብዙ አካባቢዎች ከኅዳር አጋማሽ ጀምሮ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ የፀሐይ መውጣትም ሆነ መጥለቅ በግልጽ ላይታይ ይችላል። እዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች ሌሊቱ ረጅም የሚሆንበትን ቀዝቃዛውን ወቅት ችለው ከማሳለፍ ሌላ ምርጫ የላቸውም።

ከአርክቲክ ክልል በስተ ደቡብም ቢሆን በተወሰነ መጠን ሌሊቱ ረጅም የሚሆንባቸው ወቅቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከአርክቲክ ክልል በስተ ደቡብ ከ800 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ በሚገኙት በሴይንት ፒተርስበርግ ሩሲያ፣ በሄልስንኪ ፊንላንድ፣ በስቶክሆልም ስዊድን እና በኦስሎ ኖርዌይ በቅዝቃዜው ወቅት አጋማሽ አካባቢ የፀሐይ ብርሃን የሚታየው በቀን ውስጥ ለስድስት ሰዓት ያህል ብቻ ነው።

በስዊድን ላፕላንድ በምትገኘው በኪሩና ከተማ ያደገው አሪ “በቅዝቃዜው ወቅት የአርክቲክ አካባቢ ድቅድቅ ጨለማ እንደሚውጠው ማሰብ ትክክል አይደለም” ይላል። አብዛኛውን የቀኑን ክፍል “ድንግዝግዝታ” በሚል ቃል መግለጽ ይቻላል። በፊንላንድ ላፕላንድ የምትኖረው ፓውላ የተባለች የሥነ ጥበብ ባለሞያ ደግሞ “ላፕላንድ በበረዶ ሲሸፈን አካባቢው ፈዘዝ ያለ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀለም ይኖረዋል” ብላለች።

በጨለማ የተዋጠው ቀዝቃዛ ወቅት አንዳንድ ሰዎችን ይረብሻቸዋል። ታዋቂው ፊንላንዳዊ የሙዚቃ አቀናባሪ ጂን ሲቤሊየስ “የወቅቶችና የአየር ጠባይ መለወጥ ስሜቴ እንዲለዋወጥ ያደርጋል” በማለት ጽፏል። አክሎም “ቀኑ አጭር በሚሆንበት በቀዝቅዛው ወቅት ሁልጊዜ በመንፈስ ጭንቀት እዋጣለሁ” ብሏል። በቀዝቃዛው ወቅት በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃየው ሲቤሊየስ ብቻ አይደለም። ሂፖክራቲዝ (ከ460- 377 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ) የተባለው ግሪካዊ የሕክምና ባለሞያም የወቅቶች መለዋወጥ በሰዎች ስሜት ላይ ለውጥ እንደሚያስከትል ያምን ነበር።

ይሁን እንጂ እስከ 1980ዎቹ ዓመታት ድረስ ቀዝቃዛ በሆነው ወቅት ሰዎች የሚሰማቸው የመረበሽ ስሜት የጤና እክል መሆኑ አልታወቀም ነበር። በሰሜናዊው ጫፍ አካባቢ ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከወቅቶች መለዋወጥ ጋር ተያይዞ በሚመጣ የጤና እክል (ሲዝናል አፌክቲቭ ዲስኦርደር) እንደሚሠቃዩ ጥናቶች ያሳያሉ። በተወሰነ መጠን ቀለል ያለ ሌላ ዓይነት የመንፈስ ጭንቀት ደግሞ ቀደም ሲል ከተገለጸው የጤና እክል በሦስት ወይም በአራት እጥፍ ይከሰታል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የዚህ ዓይነት የመንፈስ ጭንቀት እንደሚያጋጥማቸው ይታመናል።

በሴይንት ፒተርስበርግ ሩሲያ የሚኖረው አንድሬ “በማንኛውም ሰዓት እንቅልፍ እንቅልፍ ይለኛል” በማለት ተናግሯል። በፊንላንድ የምትኖረው አኒካ ደግሞ ቀዝቃዛው ወቅት ሲቃረብ ታዝናለች። አኒካ “ከጨለማው ማምለጥ የሚቻልበት መንገድ ስለሌለ አንዳንድ ጊዜ በጠባብ ቦታ ውስጥ የተዘጋብኝ ያህል ሆኖ ይሰማኛል” ብላለች።

ባለሙያዎች በቅዝቃዜው ወቅት የሚያጋጥመውን የመንፈስ ጭንቀት ለመቋቋም የሚረዱ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ባለሙያዎች የፀሐይ ብርሃን ባለበት ሰዓት አብዛኛውን ጊዜ በተቻለ መጠን ከቤት ውጭ ማሳለፍ ጥሩ እንደሆነ ይመክራሉ። በተጨማሪም በቅዝቃዜው ወቅት ከቤት ውጭ በሚሠራ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በዚህ ወቅት ከሚያጋጥመው የመንፈስ ጭንቀት እንደተገላገሉ ገልጸዋል።

በቅዝቃዜው ወቅት በሰሜናዊውም ሆነ በደቡባዊው ፊንላንድ የኖረው ያርሞ “ድቅድቅ ጨለማ በሚሆንበት ወቅት ተጨማሪ ሻማዎችንና መብራቶችን እናበራለን” ብሏል። አንዳንዶች ከፍተኛ መጠን ያለው ብርሃን በመጠቀም የሚደረግ ሕክምና በመከታተል እፎይታ አግኝተዋል። ሌሎች ደግሞ በስተ ደቡብ ወደሚገኝ አገር ለዕረፍት ይሄዳሉ። ይሁን እንጂ ለዕረፍት ፀሐያማ በሆነ ቦታ ቆይቶ በጨለማ ወደተዋጠው ቀዝቃዛ አካባቢ መመለስ አንዳንድ ሰዎች የሚሰማቸውን መጥፎ ስሜት ሊያባብሰው እንደሚችል አንዳንዶች ያስጠነቅቃሉ።

አመጋገብም ሊታሰብበት የሚገባ ሌላው ነገር ነው። የፀሐይ ብርሃን ሰውነት ቫይታሚን ዲ እንዲሠራ የሚረዳው ሲሆን የፀሐይ ብርሃን ማጣት ደግሞ የቫይታሚን ዲ እጥረት ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም በቅዝቃዜው ወቅት እንደ ዓሣ፣ ጉበትና የወተት ውጤቶች ያሉትን በቫይታሚን ዲ የበለጸጉ ምግቦች በብዛት መመገብ ጥሩ እንደሆነ አንዳንዶች ይመክራሉ።

የቅዝቃዜው ወቅት በጨለማ እንዲዋጥ ያደረጉት ሁኔታዎች በቂ ብርሃን እንዲኖርም ያደርጋሉ። ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ ስትሽከረከር ቀዝቃዛ የሆነው ክፍል ቀስ እያለ ወደ ፀሐይ ይዞራል። ቀስ በቀስም ቀኑ እየረዘመ ይሄዳል። ከዚያም በእኩለ ሌሊትም እንኳ ሳይቀር የፀሐይ ብርሃን የሚኖርበት የአርክቲክ የበጋ ወቅት ይመጣል!

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አብዛኛውን የቀኑን ክፍል “ድንግዝግዝታ” በሚል ቃል መግለጽ ይቻላል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቀዝቃዛው ወቅት በአርክቲክ አካባቢ እኩለ ቀን ላይ

[ምንጭ]

Dr. Hinrich Bäsemann/Naturfoto-Online

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች የፀሐይ ብርሃን በቀጥታ ማግኘት አለመቻላቸው የመንፈስ ጭንቀት ያስከትልባቸዋል