በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እዚህ ምድር ላይ የምንኖረው ለምንድን ነው?

እዚህ ምድር ላይ የምንኖረው ለምንድን ነው?

እዚህ ምድር ላይ የምንኖረው ለምንድን ነው?

ሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች ዘወትር ከሚያነሷቸው ከላይ ከተጠቀሱት ጥያቄዎች በተጨማሪ የሚጠይቁት ሌላው ጥያቄ ‘ለ70 ወይም ለ80 ዓመታት ብቻ ከኖርን በኋላ ከመሞት ያለፈ ተስፋ ሊኖረን ይችላል?’ የሚል ነው።—መዝሙር 90:9, 10

ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች በጣም የሚከነክኑን ዕድሜያችን ምን ያህል አጭር እንደሆነ በሚሰማን ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። እርግጥ እዚህ ምድር ላይ የምንኖረው ለምን እንደሆነ ለመጠየቅ የግድ ለሕይወት አስጊ በሆኑ ችግሮች ውስጥ ማለፍ አያስፈልገንም። የጠበቅነው ነገር ሳይፈጸም መቅረቱ ይህ ጥያቄ እንዲፈጠርብን ሊያደርግ ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ አኗኗራቸውን መለስ ብለው ሲቃኙት ይህን ጥያቄ ይጠይቃሉ።

ዴቭ ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራና ምርጥ ቤት የነበረው ሲሆን ከብዙ ጓደኞቹ ጋር ሆኖ ጊዜ ማሳለፍ ይወድ ነበር። እንዲህ ይላል፦ “አንድ ቀን ማታ ግብዣ ላይ አምሽቼ በእግሬ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ ሳለ ‘ሕይወት ማለት በቃ ይኸው ነው?—ለጥቂት ጊዜ ኖሬ ከዚያ በኋላ መሞት? ወይስ ሌላም ነገር ይኖራል?’ የሚለው ጥያቄ ድንገት መጣብኝ። በወቅቱ ሕይወቴ ትርጉም የለሽ የነበረ መሆኑ አእምሮዬን መታው።”

ቪክቶር ፍራንከል፣ ማንስ ሰርች ፎር ሚኒንግ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በጀርመን ከተካሄደው ጭፍጨፋ አብረዋቸው በሕይወት የተረፉ ሰዎች ከማጎሪያ ካምፖች ከተለቀቁ በኋላ እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይፈልጉ እንደነበር ገልጸዋል። አንዳንዶቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሚወዷቸው ሰዎች በሞት አልቀው ጠበቋቸው። ፍራንከል “ሲያልመው የነበረው ቀን በመጨረሻ ደርሶ የተመኘው ነገር ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖ ለጠበቀው ለዚያ ሰው ወዮለት!” ሲሉ ጽፈዋል።

ጥያቄውን የሚያነሱ ሰዎች

‘እዚህ ምድር ላይ የምንኖረው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ በየትኛውም ዘመን የኖሩ ትውልዶች ሲያነሱት የነበረ ጥያቄ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወታቸው ዓላማ ምን እንደሆነ ስለጠየቁ ሰዎች ይናገራል። ኢዮብ የተባለው ሰው ሀብቱንና ልጆቹን ካጣ በኋላ እንዲሁም በአሠቃቂ በሽታ ሥቃይ ላይ እያለ “በማኅፀን ሳለሁ ስለ ምን አልሞትሁም? ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ፈጥኜ ስለ ምን አልጠፋሁም?” ሲል ጠይቆ ነበር።—ኢዮብ 3:11 የ1954 ትርጉም

ነቢዩ ኤልያስም ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት ነበር። አምላክን የሚያመልከው ብቻውን እንደሆነ በተሰማው ጊዜ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ . . . ነፍሴን ውሰዳት” ብሎ በምሬት ተናግሯል። (1 ነገሥት 19:4) ይህ ብዙ ሰዎች የሚሰማቸው ስሜት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኤልያስን “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው” በማለት መግለጹ የተገባ ነው።—ያዕቆብ 5:17 NW

የተሳካ የሕይወት ጉዞ

ሕይወት አብዛኛውን ጊዜ ከጉዞ ጋር ይመሳሰላል። የጉዞህን መጨረሻ ሳታስብ ጉዞ ልትጀምር እንደምትችል ሁሉ እውነተኛውን የሕይወት ዓላማ ለይተህ ሳታውቅም ኑሮህን ልትገፋ ትችላለህ። ይህ ከሆነ ደግሞ እውቁ ጸሐፊ ስቲቨን ከቪ “በሥራ የተጠመደ ሕይወት” በማለት የገለጹት ነገር ሊደርስብህ ይችላል። ስቲቨን በጽሑፋቸው ላይ ስለ አንዳንድ ሰዎች ሲገልጹ “ያገኟቸው ድሎች ከንቱ እንደሆኑ እንደሚያስተውሉ፣ ስኬት ለማግኘት ሲሉ መሥዋዕት ያደረጓቸው ነገሮች ደግሞ ለእነሱ እጅግ ዋጋማ እንደነበሩ በድንገት እንደሚገነዘቡ” ጠቅሰዋል።

እየተጓዝን ያለነው በትክክለኛው አቅጣጫ ካልሆነ በጉዞው ላይ ፍጥነት መጨመራችን ምንም ትርጉም አይኖረውም ቢባል አትስማማም? በተመሳሳይም ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ በሥራ በመጠመድ የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት መሞከር የሚያመጣው ነገር ቢኖር እውነተኛ እርካታ ሳይሆን ባዶነት ብቻ ነው።

እዚህ ምድር ላይ የምንኖርበትን ዓላማ ለማወቅ መፈለግ የባሕልና የዕድሜ ልዩነት አይገድበውም። ይህ ሁኔታ የሚከሰተው ሁላችንም ካለን አንድ ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ ሲሆን ይህም ቁሳዊ ፍላጎቶቻችን ከተሟሉ በኋላም እንኳን ሳይሟላ የሚቀር መንፈሳዊ ፍላጎት ያለን መሆኑ ነው። አንዳንድ ሰዎች የሕይወትን ዓላማ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ይህን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማርካት የሞከሩት እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ በሥራ በመጠመድ የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት መሞከር የሚያመጣው ነገር ቢኖር እውነተኛ እርካታ ሳይሆን ባዶነት ብቻ ነው

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ የተወለደው ለምን እንደሆነ ጠይቋል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልያስ “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” ነበረው